Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ የሕይወት ጉዞና አዲሱ ሥራቸው

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ የሕይወት ጉዞና አዲሱ ሥራቸው

ቀን:

በቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የግል ሕይወትና ሥራን የተመለከተው ‹‹ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ዊርቱ እና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ከ1949 ዓ.ም. እስከ…›› በሚል ርዕስ ታትሞ የወጣው መጽሐፍ ለምረቃ በቅቷል፡፡ ‹‹ሴንተር ፎር ኢንቨስትመንት ኔትወርኪንግ ኢን ኢትዮጵያ›› (ሳይን) በሚል መጠሪያ ያቋቋሙትም ድርጅት ሥራ መጀመሩም በይፋ ተገልጿል፡፡

በኢሊሊ ሆቴል የሰብሰባ አዳራሽ ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ መጽሐፉን የመረቁትና የቀድሞ ፕሬዚዳንት ያቋቋሙትን ድርጅት ሥራ መጀመሩን ያስታወቁት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ናቸው፡፡

በዚህ ጊዜ ፕሬዚዳንቷ ‹‹የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ካወቅኳቸው ብዙ ጊዜ ሆኖኛል፡፡ የዲፕሎማቲክ ስብስብ አባላትም ነን፡፡ ይህ ዓይነቱ ስብስብ ደግሞ ዕይታን ያሰፋል፡፡ መነጋገርንና መተሳሰብን ያስተምራል፡፡ የሚለያዩ ጉዳዮች እንዲጠቡ ይጥራል፡፡ ሁኔታዎችን የሚመለከተው በተለያየ መንገድ ከመሆኑ ባሻገር መፍትሔ ፈላጊ፣ አስታራቂ ሐሳብን የሚያፈልቅና የሚያቀራርብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የዲፕሎማሲን ሙያ የተቀላቀሉት ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው እንደሆነ፣ ከዛን ጊዜ ጀምሮ በከፍተኛ የኃላፊነት ዕርከኖች ላይ እንደደረሱ፣ በዚህም ሕዝባቸውንና አገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት እንዳገለገሉ፣ በተለይም በዲፕሎማሲ መስክ ለኢትዮጵያ ታላቅ ግምት የሚሰጠው አስተዋጽኦ እንዳበረከቱና በዚህም ፍሬያማ ውጤት ለማስገኘት እንደቻሉ ነው ርዕሰ ብሔሯ የተናገሩት፡፡

‹‹የሚረጋገጥና የሚታዩ ስኬቶች እያሉን ስለ ራስ አለመጻፍና አለመነጋገር የሚቀጥለውን ትውልድ ደሃ የምናደርግ ይመስለኛል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ፣ ማንም ሰው በኃፊነት ዕርከኖች በቆየባቸው ዓመታት ስኬቱን፣ ያጋጠመውን ተግዳሮትና ይህንንም ተግዳሮት በአሸናፊነት ለመወጣት ያበቃውን አካሂድ በሕይወት ዘመኑ በጽሑፍ ማስቀመጥና ዘግቦ ማቆየት እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ከ‹‹ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ዊርቱና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ›› መጽሐፍ የአሁኑና መጪው ትውልድ ብዙ ተሞክሮዎችን፣ ልምዶችና ዕውቀቶችን ሊቀስሙ እንደሚችሉና ለወደፊቱም ሥራቸው ቀናውን አቅጣጫ እንደሚቀይስላቸው ነው ያመለከቱት፡፡

‹‹ሴንተር ፎር ኢንቨስትመንት ኔትወርኪንግ ኢን ኢትዮጵያ›› (ሳይን) በኢንቨስትመንት ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በማበረታታትና የውጭ ባለሀብቶችንም በመሳብ ረገድ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፣ ከዚሁ ድርጅት መመሥረት የምንማረው ነገር ቢኖር ከከፍተኛ ሥልጣን በኋላ ሕይወት እንደሚቀጥል፣ አገርንና ሕዝብን በድጋሚ ማገልገል የሚቻል መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መጽሐፉ ከልጅነታቸው ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለውን የሕይወት ጉዞአቸውን ደረጃውን በጠበቀና በቀላል ቃላት ለአንባቢ በሚመች መልኩ መተረኩን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ቀን ከሌሊት ሲሠሩ የቆዩትን የመጽሐፉን ደራሲ ከልብ አመስግነዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ከተገኙት ታዳሚያን መካከል

‹‹ሴንተር ፎር ኢንቨስትመንት ኔትወርኪንግ ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል መጠሪያ ያቋቋሙትም ድርጅት ለትርፍ ያልቆመ ከመሆኑም ባሻገር የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች በሚያከናውናቸው ተግባራት ለአገሪቱ ኢንዱስትሪ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ፣ ለወጣቱ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉና የዓለም አቀፍ ገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ለማድረግ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንደሚወጣ ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ጋር ያላትን የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ትስስርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንዲቻል በመንግሥትና በግል ባለሀብቶች መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ እንደሚያገለግልም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ለማ ደገፋ፣ በአገሪቱ የሚገኙ ኢንቨስትመንቶች ቀጣይነትና ዘላቂነት ባለው መልኩ መከናወን እንዲችሉ ለማድረግ የሚረዱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ በተለይ አገር በቀል ኢንቨስተሮችን ማበረታታት፣ ጤናማና ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንቨስትመንት ሐሳቦችን ይዘው በዓለም ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማብቃት፣ መረጃን መሠረት ያደረገ ኢንቨስትመንትን የማስተዋወቅ ሥራ ማከናወን ድርጅቱ ከያዛቸው ዓላማዎቹ መካከል ተጠቃሾች እንደሆኑ ነው የተናገሩት፡፡

እነዚህንም ዓላማዎች ለመተግበር ከኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር ስምምነት መፈራረሙን ከድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የንግድ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ዮሴፍ አደም ኑሩ፣ ከሳይን ጋር አብሮ ለመሥራት የአጋርነት ስምምነት እንደተፈራረሙ ገልጸዋል፡፡ በስምምነቱም መሠረት በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ዕድል በጋራ የመለየትና የማስተዋወቅ፣ በሥራ ላይ ያሉ ኢንቨስትመንቶች ዘላቂ እንዲሆኑ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንዲገቡና እንዲስፋፉ፣ ለዚህም የአቅም ግንባታና ምቹ የአካባቢ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው እንደሚደረግ ነው ያመለከቱት፡፡

ከዚህም ሌላ ለንግድና ኢንቨስትመንት ዕድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን የመለየት፣ የፖሊሲ ማሻሻያ ምክረ ሐሳቦችን ለመንግሥት በማቅረብ ላይ አትኩረው እንደሚሠሩ በስምምነቱ መጠቀሱን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የመጽሐፉ ደራሲ አቶ ዓለምነህ ረጋሳ መጽሐፉ በ440 ገጾችና በ11 ምዕራፎች ተቀነባብሮ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው የቀድሞ ፕሬዚዳንት አገር ወዳድነት በተጨባጭ ትረካዎች መገናዘቡን፣ አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም ጥሩ የሥራ ዕድልና ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝላቸውን የውጭ አገር ኑሮ ትተው ወደ አገር ቤት ተመልሰው አገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገልገል መብቃታቸውንም በመጽሐፉ እንደተብራራ ነው የተናገሩት፡፡  

ባገኟቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የዲፕሎማሲ ዕውቀታቸውን በመጠቀም አገራቸውን የሚጠቅሙ በርካታ ሥራዎችን እንዳከናወኑ፣ ካከናወኗቸውም ሥራዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር በርካታ የልማትና የፋይናንስ ድጋፍ በማግኘት ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻላቸውን በመጽሐፉ ውስጥ መካተቱን አመልክተዋል፡፡

መጽሐፉ ውስጥ ሰፊ ቦታ የያዘው የዲፕሎማሲ አበርክቷቸው ሲሆን ይህም ከውጭ አገር መሪዎችና ባለሀብቶች ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች፣ በዓለምና በአገር አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ካሰሟቸው ታሪካዊ ንግግሮች ጋር መቅረቡን ደራሲው ገልጸዋል፡፡

ታቦር ገብረመድህን (ዶ/ር) በቀረቡት አጭር ምልከታ ምዕራፍ አንድ የባለታሪኩን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የልጅነት ዘመንና በውጭ አገር የነበራቸውን የትምህርት ቆይታ፣ ምዕራፍ ሁለት ደግሞ ከውጭ አገር ትምህርት ቆይታ በኋላ ወደ አገር ተመልሰው ለአገር ያበረከቷቸውን አስተዋጽኦ እንደሚዳስስ ጠቁመዋል፡፡

ከምዕራፍ ሦስት እስከ 11 ያሉት የመጽሐፉ ክፍሎች ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በዲፕሎማትነት ብቻ ሳይሆን በፕሬዚዳንትነታቸው ዘመን ለአገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በስፋት እንደሚዳስስ ገልጸው ደራሲው ባለታሪኩን ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምሮ መጽሐፉ ለሕትመት እስከተላከበት ጊዜ ድረስ ያለውን እንቅስቃሴ እግር በእግር እየተከታተለና ከራሳቸውም አንደበት ቀድቶ ለትውልድ ለማቆየት ያደረገው አድካሚ ጥረት ሊደነቅ እንደሚገባው ነው ያመለከቱት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...