Saturday, May 18, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

​​​​​​​ኢትዮጵያን ከገጠማት ፈተና ለመታደግ መፍትሔ ላይ ይተኮር!

በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት ካደረሰው ዕልቂትና ውድመት በተጨማሪ፣ የተለያዩ ፍላጎቶች ያሉዋቸውን የውጭ ኃይሎች ትኩረት ከመሳብ ባለፈ ለጣልቃ ገብነት መጋበዙ ይታወቃል፡፡ በተለይ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት በርካታ ልዑካኖቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ፣ ከመንግሥትና ከተለያዩ አካላት ጋር ተነጋግረዋል፡፡ ብዙዎችም ወደ አገራቸው ሲመለሱ የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚወነጅሉ ሪፖርቶች አቅርበዋል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የልዑካኑን ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና ውይይት ማድረግ፣ እንዲሁም ተመልሰው ሲሄዱ የሚያቀርቡትን ሪፖርት ከማስተባበል የዘለለ የውጭ ኃይሎች ምን እንደሚፈልጉ የተብራራ መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ተመድን ጨምሮ ምዕራባውያን ኃይሎችና ሚዲያዎቻቸው ለምን ከመንግሥት በተፃራሪ እንደቆሙ ምክንያቱ አለመታወቁ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው፡፡ መንግሥት ፍላጎታቸውን ተረድቶ የኢትዮጵያን ውስብስብ ሁኔታ በማማከል፣ በሁለቱም በኩል ምን መስተካከል እንዳለበት መታወቅ ነበረበት፡፡ አንድ ጉዳይ በፍርድ ቤት ክርክር ሲደረግበት የዳኛው ዋነኛ ሥራ፣ ክርክሩ ጭብጡን ሳይስት በሕጉ መሠረት እንዲከናወን ማድረግ ነው፡፡ ከጭብጥ ውጭ የሚደረግ የቃላት ምልልስ ፍትሕ ለማስፈን ስለማይጠቅም፣ ተከራካሪዎች ወደ ጭብጡ እንዲመለሱ ይገደዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ የገባችበት ውስብስብ ፈተናም ከጭብጥ እየወጣ ተጨማሪ ዕልቂትና ውድመት እንዳይደገም፣ በዚህ መንገድ ለማስተካከል መሞከር ተገቢ ይሆናል፡፡ መፍትሔ ላይ ይተኮር፡፡

መንግሥት ምዕራባውያን ጣልቃ የገቡበት ውስጣዊ ችግር እንደገና ደም ሳያፋስስ በሰላም እንዲፈታ፣ የእምነት መሪዎችን ጨምሮ የአገር ሽማግሌዎችንና ታዋቂ ሰዎችን አሁንም ማንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ አሜሪካ መራሹ የምዕራባውያን ኃይል ከፍተኛ የሆነ የእጅ ጥምዘዛ ውስጥ ገብቶ የአገር ህልውና ሥጋት ውስጥ በገባበት ወቅት፣ ኢትዮጵያዊያን በኅብረት ሆነው ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በብልኃት መሻገር ይኖርባቸዋል፡፡ ማንም አሸናፊ የማይሆንበት የእርስ በርስ ጦርነት የሚጎዳው አገርን ነው፡፡ በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ዓላማቸውን ለማስፈጸም የተነሱ ወገኖችም ቆም ብለው ድርጊታቸውን ሊመረምሩ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን ለግል ወይም ለቡድን ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሣሪያ በማድረግ ቀውስ ከመፍጠር ይልቅ፣ በሠለጠነ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት የመፍትሔ አካል መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ እርግጥ ነው የአገሪቱ ፖለቲከኞች ታሪክ እንደሚያሳየው እልህ፣ ቂም በቀልና ጥላቻ መታወቂያቸው ቢሆንም በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ለዚህ ዘመን ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በቀላሉ ሊፈቱዋቸው የሚችሉ ችግሮችን ከመጠን በላይ በመለጠጥ አገር ለማፍረስ መረባረብ፣ በመጪው ትውልድና በታሪክ የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሴራ ፖለቲካ ያተረፈችው ከውድቀት በስተቀር ምንም ነገር የለም፡፡ በሴራ ፖለቲካ ጥርሳቸውን የነቀሉም ቢሆኑ ከውርደት በስተቀር ምንም አላተረፉም፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለዕድገት በማነሳሳት ከድህነት ውስጥ ማውጣት ሲገባ፣ እንደገና ጦርነት ውስጥ መማገድ ነውረኝነት ነው፡፡ ይህም መፍትሔ ይሻል፡፡

ኢትዮጵያ የሚያዋጣት ከግጭት ፀድታ ለልማት መነሳት ነው፡፡ በርካታ ለምና ጠፍ መሬቶች ፆማቸውን እያደሩና ብዙኃኑ ሕዝብ እየተራበ ጦርነት ውስጥ መግባት መገታት አለበት፡፡ ሠርተው አገር የሚያሳድጉ እጆችን ጠመንጃ ተሸካሚ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ጠቃሚ ሐሳቦች ታፍነውጦርነት መፈክር ማስተጋባት አይጠቅምም፡፡ ኢትዮጵያዊያን እንደ ቤተሰብ በአንድነት ተባብረው መነሳት አለባቸው፡፡ የአገር ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሆኖ የየዕለት ተግባርን ማከናወን የሚቻለው፣ ከሸፍጥና ከሴራ በመፅዳት ለወጣቱ ትውልድ አርዓያነት የሚሆን ቅርስ በማኖር ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ብትሆንም፣ ሰላም በማስፈን መሥራት ከተቻለ ተዝቀው የማያልቁ የተፈጥሮ ፀጋዎች አሏት፡፡ 110 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶ በላይ ወጣት ያላት አገር የተፈጥሮ በረከቶቿ ከተሠራባቸው፣ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ኃያል ከመሆን የሚያግዳት የለም፡፡ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ግን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በተዘረጋው መልክዓ ምድር ውስጥ የሚኖሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንደ አንድ ቤተሰብ መተያየት አለባቸው፡፡ በተልካሻ ምክንያቶች ሊከፋፍሏቸውና ሊያጋድሉዋቸው የሚፈልጉ ኃይሎች መገታት ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሚያምርባቸው ሲተባበሩና መሰናክሎችን በአንድነት ሲያልፉ እንጂ፣ የውጭ ጣልቃ ገቦችን በሚጋብዝ ጦርነት እርስ በርስ ሲፋጁ ስላልሆነ መፍትሔ ይፈለግ፡፡

የኢትዮጵያ የታሪክ ገጾች የሚናገሩት በርካቶችን ወደ ትቢያነት የለወጡ ለቁጥር የሚያታክቱ ጦርነቶች መካሄዳቸውን ነው፡፡ ከጦርነቶቹ የተገኙ ትሩፋቶች ደግሞ ድህነት፣ ኋላቀርነትና ማይምነት ናቸው፡፡ ከውጭ ወራሪዎችናተስፋፊዎች ጋር ከተከናወኑት ጦርነቶች ውጪ ያሉት የእርስ በርስ ትንቅንቆች፣ ለኢትዮጵያ ያተረፉት አምባገነኖችንና ዘራፊዎችን ነው፡፡ ኢትዮጵያን በሥርዓት ለመምራት የሚያስችሉ ጠንካራ የሲቪልና የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማፍራት ባለመቻሉ፣ ኢትዮጵያ ዛሬም ከሐሳብ ልዕልና ይልቅ ለጉልበት የሚያደሉ ፉክክሮች ይስተዋሉባታል፡፡ ከቃላት ጦርነት ታልፎ ከፍተኛ ደም መፋሰስ የተደረገበት አውዳሚ ጦርነት አልበቃ ብሎ፣ እንደገና ለሌላ ዙር ደም መፋሰስ የሚደረገው ትንቅንቅ እንዲገታ መደረግ አለበት፡፡ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት በጉልበት የመሞካከር አባዜ ለዚህ ዘመን አይመጥንም፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ፋይዳ የሌላቸው የእልህ፣ የሴራና የቂም በቀል እንቅስቃሴዎች መምከን ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን በሁሉም መስኮች ወደፊት የሚያራምዱ የጋራ ጉዳዮች ላይ ለመግባባት መፈላለግ ሲገባ፣ ጦር እያደራጁና የውጭ ጣልቃ ገብነትን እየጋበዙ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት የሚደረገው ዳግም ትንቅንቅ ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊያንን ውድ ሕይወትና የአገር ሀብት እሳት ውስጥ ለመክተት መራኮት መቆም አለበት፡፡ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት አደገኛ ድርጊት አገርን የማትወጣበት ቀውስ ውስጥ ስለሚከተል መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ 

በተደጋጋሚ ለማስገንዘብ እንደተሞከረው ኢትዮጵያ ያጋጠሟት መልካም ዕድሎች የተበላሹት፣ ከአገር በላይ የግልና የቡድን ፍላጎቶች በመቅደማቸው ነው፡፡ በዚህ ዘመን እያስቸገሩ ያሉት ደግሞ ማገናዘብ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ልሂቃን ናቸው፡፡ ቢያንስ በታሪክ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮችን ተገንዝበዋል ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከታሪካዊ ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ አይመስሉም፡፡ ሥልጣን ላይ ሆነው አገርና ሕዝብ ሲያተራምሱ የነበሩ ኃይሎች ዛሬ የማያውቁበትን ተቃዋሚ ሆነው ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡ በዚያው ሒደት ውስጥ አልፈው የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሰዋል የተባሉ ሳይቀሩ መለወጥ አቅቷቸዋል፡፡ በአንድ ወቅት የተገኘን መልካም አጋጣሚ በጋራ ከመንከባከብና ወደ ተሻለ ደረጃ ከማድረስ ይልቅ፣ የተለመደው የእልህና የሴራ ፖለቲካ ውስጥ ተገብቶ ዕልቂት እየተደገሰ ነው፡፡ አንድም ቀን ስለሕግ የበላይነት፣ ስለእኩልነት፣ ስለፍትሐዊነት፣ ስለነፃነት ሲያቀነቅኑ የማይሰሙ ጀብደኞች አሉባልታ፣ ሐሜት፣ ጥላቻ፣ ሁከትና አገር ስለማተራመስ ነው የሚደሰኩሩት፡፡ ይህ ግን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥፋት በስተቀር መልካም ነገር ጠብ ስለማያደርግለት መፍትሔ የግድ ነው፡፡

ኢትዮጵያን የሰላም፣ የፍትሕና የነፃነት አገር ማድረግ የሚቻለው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ፉክከር እንጂ፣ አሁን እንደሚታየው በጦርነት ነጋሪት ጉሰማ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም የምትነግዱ ከሰላም አፈንግጣችሁ የማንን ዓላማ ነው የምታሳኩት? ሕዝቡን ከድህነት ማጥ ውስጥ ለማውጣት የሚያስፈልገው ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት የሚገነባው በሠለጠነ አስተሳሰብ እንጂ በጠመንጃ አምላኪነት አይደለም፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በማይመጥን ፀባይ ለሕዝብ ቆሜያለሁ ማለት ቀልድ ነው፡፡ በሕዝብ ስም እየማሉ አገርን ማፍረስ የለየለት ቁማርተኝነት ነው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የሚያስቡ የቡድን ፍላጎትና ጥቅም አያማልላቸውም፡፡ የእነሱ ፍላጎት ከአገር ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት በታች እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እያነሳሱ አያጋድሉም፡፡ የአገርን ሰላም እያደፈረሱ ቀውስ አይፈጥሩም፡፡ ከሴራና ከአሻጥር የፀዱ በመሆናቸው ተግባራቸው ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ከእሳቱ ርቀው መሽገው አገር አይበጠብጡም፡፡ ከእንዲህ ዓይነት የማይረባ ድርጊት ነፃ ነን የምትሉ አገር አረጋጉ፡፡ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ተያይዞ ከመጥፋት የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ይታወቅ፡፡ የሚያዋጣው መፍትሔ ፍለጋ ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፖለቲካዊም ይሁን ኢኮኖሚያዊ ትግል መቀዛቀዝ ምክንያቱ የጠራ ርዕዮተ ዓለም አለመኖር ወይስ የምሁራን መዳከም?

መሬት ላራሹ ብለው በተነሱ ተማሪዎችና ምሁራን ድምፅ የተቀጣጠለው የመጀመሪያው...

በአዲስ አበባ ለሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሰጡ ድጋፎችንና መሥፈርቶችን ያካተተ አዲስ መመሪያ ወጣ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው ወስጥ ለሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች...

የዘንድሮ የወጭ ንግድ ገቢ ከዕቅዱም ሆነ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ

የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ ገቢ በተያዘው የበጀት ዓመትም የታቀደውን ያህል...

ሕይወትም እንዲህ ናት!

ከዊንጌት ወደ አየር ጤና ነው የዛሬው የጉዞ መስመራችን፡፡ አንዳንዴ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ቅንጦት አይደለም!

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ በወሰነው መሠረት በየዓመቱ እ.ኤ.አ. ሜይ 3 የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀን የሚዘከርበት ምክንያትም የፕሬስ ነፃነትን...