Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​​​​​​​በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የሚረዳ የ100 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

​​​​​​​በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የሚረዳ የ100 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ቀን:

ኮቪድ-19 በዓለማችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ መቼም ሁላችንም ያየነውና የተረዳነው ሐቅ ነው፡፡ የቫይረሱን ከፍተኛ መዛመት ተከትሎ በተወሰዱ የመከላከል ዕርምጃዎች የበርካታ አገሮች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለወራት እንዲቆሙ አድርጓል፡፡ በዝቅተኛ የዕለት ገቢ የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይም ከፍተኛ የሆነ የኑሮ መዛባት ፈጥሯል፡፡ እንዲሁም ከፍተኛ ማኅበራዊ ምስቅልቅል ያስከተለና እስካሁኗ ሰዓት ድረስ ዓለማችንን እየፈተነ የሚገኝ ወረርሽኝ ነው፡፡

የጆንስ ሆፕኪንስ የኮሮና ቫይረስ ሪሶርስ ሴንተር የሐምሌ 27 ቀን 2013 እኩለ ቀን መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዚህ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ198 ሚሊዮን በላይ የሆነ ሲሆን፣ ከ4.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ቫይረሱ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከተነገረበት ቀን አንስቶ ወደ 280,833 ሰዎች በዚህ ቫይረስ መያዛቸውን ወቅታዊው መረጃ ያሳያል፡፡ 4,391 የሚሆኑ ዜጎቻችም ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ለዚህ ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ለማግኘት የተደረገው ጥረት ውጤት አምጥቶ በዓለም ጤና ድርጅት ዕውቅና የተሰጣቸው ክትባቶች እንዲዳረሱ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እስካሁኗ ቀን ድረስ ባለው መረጃ ወደ 3.5 ቢሊዮን የሚጠጋ የክትባት ዶዝ እንደደረስ ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ክትባቱ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እንዲደርስ በተደረገ ጥረት እስካሁን 2.2 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ተዳርሷል፡፡ በአጋሮች ድጋፍና በመንግሥት ጥረት ክትባቱን ለማዳረስ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚል ተስፋ ቢኖርም ይህ ራሱን በየጊዜው የሚቀያይር ቫይረስ ሥርጭቱን ቀጥሎ የጤናውን ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ፈተና ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡

እንደ ቀሪው ዓለም ሁሉ የቫይረሱን ፈጣን ሥርጭት ለመግታትና ለመቀነስ በተወሰዱ ዕርምጃዎች በተለይ በዕለት ገቢ ላይ በተመሠረተ ሥራ የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የደረሰው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫና እጅግ ከባድ ነው፡፡ እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዛሬም ድረስ ከደረሰባቸው የኢኮኖሚ ጉዳት ለማገገም እየታገሉ እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ ይህንንም ትግላቸውን አንዳንድ ዓለም አቀፍና አገር በቀል የሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቴክኒክ፣ በባለሙያና በበጀት የታገዘ ድጋፍ ለማበርከት ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላሉ፡፡

በዚህ መልኩ ከሚንቀሳቀሱት መካከል ትኩረት የተነፈጋቸውና ለአደጋ ወይም ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመታደግ የሚያስችላቸውን የ100 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ቀርጸው ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በኅብረት የሚያከናውኑ ስድስት ዓለም አቀፍና አገር በቀል የሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ድርጅቶቹ ‹‹ኮቪድ-19 ሪስፖንስ አክሮስ ዘ ሒውማኒቴሪያን ዴቨሎፕመንት ኒክሰስ ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል መጠሪያ የሚታወቀውን ይህንኑ ፕሮጀክታቸውን ሐምሌ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አድርገዋል፡፡ ፕሮጀክት ሥራ ላይ የሚቆየው ከ2013 ዓ.ም. እስክ 2015 ዓ.ም. ድረስ ሲሆን በበላይነት የሚመራውም በዓለም አቀፋዊው ተቋም ላይት ፎር ዘ ወርልድ በተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡

የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳዲቅ ሐሰን እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ፕሮጀክቱ እናቶች፣ ሴቶች፣ ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞች የሥነ ልቦና ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ከዚህም ሌላ እንደ ኮቪድ-19 ያሉ ወረርሽኞችና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያስከትሉትን አደጋ የሚያመላክት በቂ መረጃ በማዳረስ የመከላከል፣ ከግልና አካባቢ ንፅህና ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን የማዳረስ ተግባር እንደሚያከናውን፣ እንዲሁም ታላሚ ያደረጋቸውን ተጠቃሚዎች በኢኮኖሚ ራስን ማስቻልን የሚረዱ ዕቅዶችን እንዳካተተ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱን ያዘጋጀውና ለተግባራዊነቱም የሚውለውን ገንዘብ የሸፈነው የኦስትሪያ ልማት ኤጀንሲ ሲሆን፣ በዚህም 1,162,000 ሰዎች በቀጥታና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ፕሮጀክቱን እንደ የሥራ ባህሪያቸው የሚተገብሩት የኢትዮጵያና የኦስትሪያ ቀይ መስቀል ማኅበራት፣ ኬር ኦስትሪያ፣ የኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲዚአብሊቲስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት፣ ሐርሜ ኢጁኬሽን ፎር ዴቨሎፕመንት ናቸው፡፡

ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች መካከልም 2,600 ሰዎች የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው፣ 1,560 ሰዎች በየመንደሩ በተቋቋሙት የቁጠባና የብድር ማኅበራት ውስጥ እንደሚሳተፉ፣ ሌሎች 52 አካል ጉዳተኞች ደግሞ ተቀጣሪ እንደሚሆኑ ከአቶ ሳዲቅ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አህመዲን፣ ክትባቱን ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ አሁንም የቫይረሱን ሥርጭት የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ይህም ማለት ሰዎች ዛሬም ርቀታቸውን ጠብቀውና የፊት ማስካቸውን አድርገው መንቀሳቀስ፣ የእጃቸውን ንፅህና መጠበቅ እንደሚኖርባቸው፣ በአንጻሩም ስለቫይረሱ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች የሚጠቁሙ መረጃዎች ሊደርሳቸው እንደሚገባ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የኦስትሪያ ልማት ኤጀንሲ በዋነኛነት ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ድህነትን በመዋጋት፣ በሰላም መረጋገጥና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም በታዳጊ አገሮች ያለውን የኑሮ ሁኔታ ለሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ትግበራ 550 ሚሊዮን ዩሮ መበጀቱን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...