Monday, May 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ውዥንብሮች ይጥሩ!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ምስቅልቅል ችግሮች እንደገጠሟት የታወቀ ነው፡፡ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት ለጊዜው በመንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ጋብ ብሎ የነበረ ቢመስልም፣ ነገር ግን በአማራና በአፋር ክልሎች በኩል ውጊያው ተጠናክሮ መቀጠሉ ሲሰማ የችግሩን ግዝፈት ያሳያል፡፡ በመንግሥት በኩል ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት በመፈጠሩና ኃላፊነት የማይሰማቸው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተዋንያን አደናጋሪ መረጃዎች በመብዛታቸው፣ በአራቱም ማዕዘናት ያለው ሕዝብ ጭንቀትና ሥጋት ውስጥ ይገኛል፡፡ በአንድ በኩል የክተት ጥሪ ተደርጎ ወጣቶች በብዛት ወደ ማሠልጠኛ ጣቢያዎች እየገቡ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡን ግራ የሚያጋቡ መረጃዎች እየተለቀቁ የተደበላለቁ ስሜቶች ይንፀባረቃሉ፡፡ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ከሙያ ሥነ ምግባር አፈንግጦ የሐሰት ወሬዎችን ሲያዥጎደጉድ፣ ከበስተጀርባው ያለው ፍላጎት ምን እንደሆነ ለማወቅ ነብይ መሆን አይጠበቅም፡፡ መንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን አጠናክሮ ስለወቅታዊ ሁኔታዎች ተከታታይና ተዓማኒነት ያላቸው መረጃዎችን ማሠራጨት ሲገባው፣ ሚናውን ለሌሎች አካላት ስለወሰዱበት ውዥንብሩ እየበረታ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ምሁራንና ልሂቃን ሳይቀሩ የተሟላ መረጃ ማግኘት ባለመቻላቸው፣ ለሚዲያዎችም ሆነ ለሕዝቡ ጠቃሚ ሐሳቦቻቸውን ማካፈል አልቻሉም፡፡ ይህ አጋጣሚ ደግሞ ምንጫቸው የማይታወቅ ወሬዎችና አጓጉል ትንተናዎች አየሩን እንዲቆጣጠሩ ትልቅ ዕገዛ እያደረገ ነው፡፡ የመረጃ እጥረት ውዥንብሩን አባብሶታል፡፡

ሌላው አደናጋሪ ጉዳይ ደግሞ በአገር ውስጥ ለሰላም መስፈን በግልጽ የሚታይ አንዳችም እንቅስቃሴ ሳይኖር፣ በውጭ ኃይሎች አማካይነት እየሾለኩ የሚደርሱ መረጃዎች ውዥንብሩን የበለጠ እያወሳሰቡት ነው፡፡ ከእነዚህም በመንግሥትና በሕወሓት አመራሮች መካከል ኮሽታ ሳይሰማ ድርድር እንደሚካሄድ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ያለውን አስተዳደር በማስወገድ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ እንቅስቃሴ እንዳለ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ቅርፅና ይዘት ሊለውጥ የሚችል ዕቅድ ተይዞ ሴራ እንደሚጎነጎንና ሌሎች መያዣ መጨበጫ የሌላቸው መረጃዎች እየተሰሙ ነው፡፡ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት የሚጋብዙ ትርምሶች እንዲፈጠሩም፣ ውዥንብሩ በየአቅጣጫው ተባብሷል፡፡ በሌላው ወገን ደግሞ በቅድመ ሁኔታዎች የታጠረ መደራደሪያ ሲቀርብ በግልጽ ይሰማል፡፡ እነዚህን ግራ የሚያጋቡ መረጃዎች የሚደርሷቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸው ዕጣ ፈንታ ቢያሳስባቸው አይገርምም፡፡ ይህ ሁሉ አሳሳቢ ሁኔታ ተፈጥሮ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማው በመቀጠሉ፣ የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔው ተቀልብሶ ውጊያው የሚፋፋም ከሆነ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም፡፡ የአገር ህልውና ጉዳይ እንዲህ አደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ በወደቀበት በዚህ ጊዜ፣ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው መልካሙን ከመመኘት ጀምሮ የሚበጀውን መፍትሔ ተረባርበው የማመላከት ኃላፊነት እንዳለባቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ የአገር ጉዳይ ሰፊ ዕይታና ዕሳቤ ያስፈልገዋልና፡፡

አገር ችግር ውስጥ ሆና ውዥንብር በመብዛቱ ከጦርነት በመለስ ያሉ መልካም አማራጮችን ማሳየት የሚችሉ የእምነት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ልሂቃን፣ እንዲሁም የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ድምፅ ጭምር እየታፈነ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የአገር ህልውና አደጋ ውስጥ ሲገባ ተባብሮ አደጋውን መቀልበስ በየትም አገር የሚደረግ መልካም ተግባር ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን በተቻለ መጠን የሰላም አማራጭን መጠቀም ደግሞ ወደፊት ሊያጋጥም ከሚችል ፀፀት ይከላከላል፡፡ በአገሮች መካከልም ሆነ በውስጥ ተቀናቃኞች መካከል ችግሮች ተባብሰው ቀውስ ሲፈጠር፣ የሰላም አማራጭ ከምንም ነገር በፊት ተቀዳሚ ተመራጭ ነው፡፡ ጦርነት ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ከመቅጠፍ ጀምሮ የአገር ሀብት በማውደም ብቻ ሳይሆን፣ ለረዥም ዓመታት የሚቆይ ጠባሳ ትቶ ነው የሚያልፈው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት የገጠማት ፈተና እጅግ በጣም ከመክበዱ የተነሳ፣ ጦርነትን ወደ ጎን በመግፋት ሰላም ለማስፈን የሚደረግ ጥረት ቢኖር እንኳን አሰልቺና አድካሚ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ አንዱ ወገን ለሰላም እጁን ቢዘረጋ ሌላው ስለመቀበሉ ማስተማመኛ ባለመኖሩ የችግሩን ክብደት በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ አሸናፊና ተሸናፊ የማይኖርበት አዙሪት ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራ እየተጋባ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የቂመኞችና የባላንጣዎች ሒሳብ ማወራረጃ ሆኖ የዘለቀው፣ ለሕዝብ ነፃ ፈቃድና ይሁንታ ሥፍራ ስላልነበረው ነው፡፡ ለውይይትና ለድርድር ባዕድ የነበረው የፖለቲካ ምኅዳር ምሁር ጠል፣ ለመካሪና ለዘካሪ ያስቸገረ፣ ለማኅበረሰቦች ተሳትፎ ቦታ ያልነበረው፣ የአስመሳዮችና የአድርባዮች መፈልፈያና ራዕይ አልባ ነበር፡፡ ክፋት፣ ሴራ፣ አሻጥርና ኋላቀርነት የተፀናወቱት ከመሆኑም በላይ አርቆ አስተዋይነት ያልፈጠረባቸው ደካሞችና ሰነፎች ስለሚተውኑበት ለአገር ሰቆቃ እንጂ ተስፋ አልነበረውም፡፡ እርስ በርስ መጋደል፣ መሳደድ፣ ስም መጠፋፋት፣ ወጣቱን ትውልድ መበከልና የአገርን ሚስጥር ለባዕዳን ማቀበል አሳፋሪ ልማዶች የሰፈነበት በመሆኑ፣ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ያለ ኃጢያታቸው ፍዳቸውን ዓይተዋል፡፡ ያንን የተሰነካከለ አስተሳሰብና ጎዳና አንለቅም ብለው የሚንገታገቱ ኃይሎች፣ ዛሬም እሱን ሙጭጭ ብለው ነጋ ጠባ ሲያስተጋቡት ይሰማሉ፡፡ እስቲ እንነጋገር፣ እንደራደር፣ የጎደለ ካለ አብረን እንሙላ፣ ወዘተ መባባል ሲገባ ጠላትነት የበላይነቱን ይዟል፡፡ ውዥንብሩም በዚያው መጠን ቀጥሏል፡፡

ኢትዮጵያ ሁሌም ከመከራ ጋር የምትታገል አስገራሚ አገር ናት፡፡ አንድም ጊዜ በማንም ላይ ወረራ የመፈጸም ታሪክ ባይኖራትም፣ ታሪኳ ግን እሷን ለመከላከል ከተደረጉ በርካታ ጦርነቶች ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በደህና ጊዜ እርስ በርሳቸው መስማማት የማይችሉት ልጆቿ፣ ወራሪና ተስፋፊ ሲመጣ ለመተባበር ወደር የላቸውም፡፡ ክህደት በመፈጸም ለጠላት የሚያድሩ ባንዳዎችም አፍርታለች፡፡ ዛሬም መልካቸውን እየቀያየሩ ይከሰታሉ፡፡ አብሮ ለመብላት እንጂ አብሮ ለመሥራት ከባድ በሆነባት አገር ውስጥ፣ በትንሹም ሆነ በትልቁ ለመጣላት ወይም ለመጋጨት ያለው ፍጥነት ያስደንቃል፡፡ ከምክንያታዊነት በላይ ስሜታዊነት እየገነነ በሰላም ጊዜ የተገኙ ወርቃማ ዕድሎች በተደጋጋሚ ባክነዋል፡፡ የሀብትም ሆነ የጉልበት ምንጭ በሆነው ተጠያቂነት የሌለበት ሥልጣን ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የፈሰሰው ደም ሲታሰብ ይዘገንናል፡፡ ከሕግ ይልቅ ጉልበት ገዝፎ የደረሰው መከራ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ለቂምና ለበቀል መወጫ በመዋሉ፣ አሁን ያለውን ትውልድ ጭምር ደም እያቃባ ነው፡፡ በዚህ መሀል ግን መከረኛው ሕዝብ አሳሩን ይበላል፡፡ እንደ መርግ በሚከብዱት ችግሮች ላይ የፖለቲካው አተካሮ ከግጭት ጋር ሲጨመርበት ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ደግሞ ከነገ ተመራጭ እያደረገ ከብሩህ ተስፋ ይልቅ ድቅድቅ ጨለማ ነው የሚታየው፡፡ ለአገር አደገኛ የሆኑ ችግሮች ሲያጋጥሙ ለመፍታት የሚኬድበት መንገድ ዙሪያ ጥምጥም እየሆነ፣ በቀላሉ ተነጋግሮ መፍትሔ መፈለግ እየከበደ ነው፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ውዥንብር አገር እያተራመሰ ነው፡፡ 

የዘመናት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመቀነስ የተረጋጋች አገር እንድትሆን ድጋፍ ያስፈልጋታል፡፡ ድጋፉም ለአገር ከሚያስቡ ኢትዮጵያዊያንና ከውጭ ወዳጆች መገኘት እንዳለበት አያጠራጥርም፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን አገራቸውን ሲታደጉም ሆነ ሐሳብ ሲለዋወጡ፣ ባዕዳንን ለማስደሰት ሲሉ ከሆነ ግን ያሳዝናልም፣ ያሳፍራልም፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብን የማይጠቅሙ ውስብስብ አጀንዳዎችን የበለጠ እያጠላለፉ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለመልማት የሚደረገውን ቀና ጉዞ በባዕዳን ለማስባረክ መሯሯጥ ያተረፈው ውርደት ብቻ ነው፡፡ እርስ በርስ በጋራ ብሔራዊ ጉዳይ ላይ መግባባት እያቃተ በመተናነቅ የባዕዳን መሳቂያ መሆን ካላከተመ በስተቀር፣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መከራ በሰፊው ይቀጥላል፡፡ ችግሩ ሲባባስም ለመፍትሔ ርብርብ ማድረግ ሲገባ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ መፈታት የሚችል መናኛ ችግር ለሕዝብ ዕልቂት መደገሻ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ከዋነኛ ተዋንያን እስከ አራጋቢዎች ድረስ የሚስተዋለው ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ውዥንብር፣ ቀውስ ከመፍጠር ባሻገር አገር እንደሚያፈርስ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ አገርን ከዕለት ወደ ዕለት ቀውስ ውስጥ በመዝፈቅ ውዥንብሩን ማስፋፋት ለማንም አይጠቅምም፡፡ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ውዥንብሩ ጠርቶ ትክክለኛውን ጎዳና ለመያዝ መረባረብ የግድ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...