Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

​​​​​​​‹‹በገጠር ያለችዋንና የተረሳችዋን ሴት አስታውሶ ወደፊት ማምጣት ያስፈልጋል›› ወ/ሪት ዝምድና አበበ፣ ስትራቴጂክ ኢኒሼቲቭ ፎር ውሜን ኢን ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ የኢትዮጵያ ቢሮ ፕሮግራም አስተባባሪ

ስትራቴጂክ ኢኒሼቲቭ ፎር ውሜን ኢን ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ (ሲሐ ኔትወርክ) በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚንቀሳቀስ፣ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት የሚያስከብርና ለሴቶች የሚሟገት ድርጅት ነው፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሶማሌላንድ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በአባልነት ታቅፈዋል፡፡ ወ/ሪት ዝምድና አበበ በድርጅቱ የኢትዮጵያ ቢሮ ፕሮግራም አስተባባሪ ናቸው፡፡ የሴቶችን ማኅበራዊ ተሳትፎ ለማበረታታትና መብቶቻቸውንም ለማስከበር ‹‹ሲሐ›› የሚያከናውናቸውን ሥራዎች አስመልክቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስትራቴጂክ ኢኒሼቲቭ ፎር ውሜን ኢን ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ (ሲሐ ኔትወርክ) መቼ ተቋቋመ? ኢትዮጵያ ውስጥ መንቀሳቀስ የጀመረው መቼ ነው? ሴቶችን በምን መልኩ ይረዳል?

ወ/ሪት ዝምድና፡- ‹‹ሲሐ›› ኔትወርክ በአፍሪካ ቀንድ የተቋቋመው በ1987 ዓ.ም. ሲሆን ዋና መሥሪያ ቤቱም ካምፓላ ኡጋንዳ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መንቀሳቀስ ከጀመረ አሥር ዓመት ሆኖታል፡፡ ለጊዜው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሶማሌ ላንድ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ውስጥ ሴቶችን የሚያሳትፍ አምስት ፕሮጀክቶች አሉት፡፡ ከፕሮጀክቶቹም መካከል የተደበቁ ወይም የተረሱ ሴቶችን ማውጣት፣ ለሴቶች ነፃ የሕግ አገልግሎት መስጠት፣ በኢኮኖሚ አቅማቸው ደከም ያሉ ሴቶችን በሁለንተናዊ መልኩ መርዳትና ማገዝ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ አቅማቸውን የሚያድገው የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ሲሆን፣ የራስ አገዝ ሥራ ማከናወን እንዲያስችላቸው ለሚያዘጋጁት ፕሮጀክት ዕውን መሆን የፋይናንስ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡ ለዚህም ፕሮጀክቶቻቸው አዋጭነት ቀድሞ ያረጋግጣል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕግ አገልግሎት የሚሰጣቸው ምን ሲያጋጥማቸው ነው?

ወ/ሪት ዝምድና፡- የሕግ አገልግሎት በዋነኝነት የሚሰጠው ፆታዊና አካላዊ ጥቃት ሲፈጸምባቸው ነው፡፡ ከትዳር አጋራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ወይም ጋብቻ ሲያፈርሱ በንብረት ክፍፍል ወቅት ለሚያጋጥማቸው ችግር አቅም በፈቀደ መጠን ድጎማ በማድረግ ይተባበራል፡፡ ይህንንም የሚያደርገው ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ጋር በመቀናጀት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ እስካሁን ለስንት ሴቶች የሕግ አገልግሎት ሰጥቷል?

ወ/ሪት ዝምድና፡- በቁጥር ለመተመን በጣም ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ‹‹ሲሐ›› በዚህ ዙሪያ ከሌላው ለየት የሚያደርገውን አካሄድ ነው የሚከተለው፡፡ ለየት የሚያደርገውም በሚንቀሳቀስባቸው አገሮች ከሚገኙና ሴት ተኮር ከሆኑ ተቋማት ጋር በመቀናጀት መንቀሳቀስ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ያበረከተውን ድጋፍ በትክክል ለማስቀመጥ ቢያስቸግረኝም በተጠቀሰው ነጥብ ዙሪያ በርካታ ቁጥር ላላቸው ሴቶች አገልግሎት ሰጥቷል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ሲሐ›› የሚንቀሳቀሰው አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ በሌሎች ክልሎች መንቀሳቀስ ለምን ተሳነው?

ወ/ሪት ዝምድና፡- አገልግሎቱን ወደ የክልሎች የማስፋፋት ሐሳብ አለው፡፡ ዋነኛው ዓላማው ማንኛዋም ሴት ወደኋላ እንዳትቀር ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የከተማ ሴቶች ላይ ብቻ ማተኮር እንደማይፈልግ መገንዘብ ይገባል፡፡ በገጠር ያለችዋንና የተረሳችውንም ሴት አስታውሶ ወደፊት ማምጣት ይፈልጋል፡፡ ይህም ደረጃ በደረጃ የሚከወን ሒደት ቢሆንም በአጋሮቻችን አማካይነት በጋምቤላና በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከትኩረት አቅጣጫችሁና ከአነጋገርዎ መገንዘብ እንደቻልኩት በገጠር ላሉ ሴቶች ብዙም ያደረጋችሁ አይመስለኝም?

ወ/ሪት ዝምድና፡- በደንብ አለ እንጂ!! በጣም ብዙ ያደረግነው አለ! አዲስ አበባ ላይ የምናተኩረው ‹‹ሲሐ›› በቀጥታ ድጋፍ ለሚያደርግላቸው ነው፡፡ በተረፈ በአጋሮቻችን አማካይነት ያልገባንበት ክልል የለም፡፡ እንዳውም በአፋርና በሶማሌ ክልሎች አዳዲስ የ‹‹ሲሐ›› ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን ለመክፈት አጋሮቻችን ከሆኑ ድርጅቶች ጋር እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ያጋጠማችሁ ችግርና ችግሮቹንም ለመፍታት ያደረጋችሁትን እንቅስቃሴ እንዲሁም ከመንግሥት ሊደረግልን ይገባል የምትሉትን ድጋፍ በተመለከተ ሊያብራሩልን ይችላሉ?

ወ/ሪት ዝምድና፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ የምንሠራው ሥራ በጣም ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ሥራ ራሱን የቻለ ችግሮች አብረውት ይመጣሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በአንድ አካባቢ ለዘመናት አብሮ የኖረውን የማኅበረተስ ባህል፣ አስተሳሰብና ልምድ ለመቀየር ረዘም ያለ ጊዜ ከመጠየቁ አልፎ በርካታ ተግዳሮቶች ይኖሩታል፡፡ ገና ከጅምሩ ማኅበረሰቡን ለማደራጀት ወደ እንቅስቃሴ ሲገባ መጥፎ አጀንዳ ይዘውብን መጡ በሚል የተነሳ ማጉረምረምና ወደኋላ መንሸራተትን ያስከትላል፡፡ ጉዳዩ ሳይገባቸው የማጥላላት ሥራን ያጧጡፉብሃል፡፡ ስለዚህ እንደነዚህ ዓይነቶችን እንቅፋቶች በአሸናፊነት ለመወጣት ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል ይገባል፡፡ በዚህም የማኅበረሰቡን ዕውቀት መቀበል በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በዚህ መልኩ አብረህ ከሠራህ ተቀባይነትን ለማግኘት ይረዳል፡፡ ከዛም ቀጥሎ በእንቅስቃሴያቸው ውጤታማ የሆኑ ሴቶችን በመሸለምና ያልታዩ ሴቶችን እንዲታዩ በማድረግ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ እኛም በዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተን በመሥራታችን ውጤታማ ልንሆንና አሁን ያለንበት ደረጃ ልንደርስ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- በያዙት ሥራ ላይ ውጤታማ ለሆኑ ሴቶች ያበረከታችሁት ማበረታቻ በተመለከተ ቢገልጹልን?

ወ/ሪት ዝምድና፡- አዲስ አበባ ውስጥ ከ4035 በላይ ሴቶችን በአባልነት ያቀፈና የራስ አገዝ ቡድን ሕብረት የሆነው ‹‹ይታወቅ ሕብረት›› ሰብሳቢ ለሆኑ ወ/ሮ ጠይባ ያሲን የተበረከተላቸውን ድጋፍ ማንሳቱ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ‹‹ይታወቅ ሕብረት›› ከማንኛውም ፖለቲካ፣ ሃይማኖትና ጎሳ ነፃ የሆነ የጥምረቱ ሕብረት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአብዛኞቹ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የሴቶች ራስ አገዝ ቡድኖች የተደራጁ ሴቶች በኢኮኖሚና በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ውጤታማ እንዲሆኑና መልካም አስተዳደርም እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ ወ/ሮ ጠይባ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በአጠቃላይ የ2013 ዓ.ም. የ‹‹ሲሐ›› ሴቶች ተሟጋች አሸናፊ በመሆናቸው ልዩ ልዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል፡፡ ካገኙትም ሽልማቶች መካከል 600 ዩሮ በኢትዮጵያ ብር ተመንዝሮ፣ ዋንጫና ‹‹ሲሐ›› በሚያዘጋጃቸው መድረኮች ሁሉ የመሳተፍ ዕድል ይገኝበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ወ/ሮ ጠይባ አሸናፊ ለመሆን ያበቃቸው ምን ዓይነት ግምገማ ወይም መለኪያ በማለፋቸው ነው?

ወ/ሪት ዝምድና፡- በመጀመርያ ሴቶችን በማብቃት ዙሪያ በልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተሳተፉ አምስት ሴቶች ለውድድር ቀረቡ፡፡ ከእነዚህም መካከል ለውድድር የቀረቡትን ልዩ ልዩ መስፈርቶች ወ/ሮ ጠይባ በአጥጋቢ ሁኔታ በማለፋቸው ለሽልማት በቅተዋል፡፡ ለሌሎቹም የተሳትፎ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ጤናማ ውድድር ወደፊትም ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...