Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል​​​​​​​‹‹ያልታሰበው የሕይወቴ…›› መጽሐፍ ተመረቀ

​​​​​​​‹‹ያልታሰበው የሕይወቴ…›› መጽሐፍ ተመረቀ

ቀን:

በቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ሥርዓት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን የነበሩት ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ ‹‹ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ትዝታና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዬ›› በሚል ርዕስ የደረሱት መጽሐፍ ሐምሌ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ተመርቆ ገበያ ላይ ዋለ፡፡

በደራሲው የግል ሕይወት ዙሪያ ያጠነጠነውና በ700 ገጾች ተደራጅቶ የወጣውን ይህንኑ መጽሐፍ ያሳተመው በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የኢትዮጵያ አካዳሚክ ፕሬስ ነው፡፡

የአካዳሚው ሥራ አስፈጻሚ ተከተል ዮሐንስ (ፕሮፌሰር) በምረቃው ሥነ ሥርዓት እንደ ተናገሩት፣ በቅርቡ የተቋቋመው አካዳሚክ ፕሬሱ እስከዛሬ ጥራታቸውን በከፍተኛ ደረጃ በጠበቀ መልኩ ካሳተማቸው ስምንት መጽሐፍት መካከል የሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ መጽሐፍ አንዱ ነው፡፡

መጽሐፉ ከሌሎች መጻሕፍት በተለየ ለህትመት ረዥም ጊዜ የወሰደ፣ በአንጻሩም የብዙ ባለሙያዎችን ተሳትፎ የጠየቀ፣ የአንድ ግለሰብ ሳይሆን የአገር ታሪክ የተዘገበበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በማኅበራዊና በፖለቲካዊ እንዲሁም በዲፕሎማሲያዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሚሞላቸው ክፍተቶች እንዳሉት፣ ከተመሳሳይ ግለ ታሪኮች በተሻለ ሁኔታ ከ1966 ዓ.ም. የአብዮት ዋዜማ እስከ ደርግ ፍጻሜ ድረስ ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን መንገዶች በስፋት ያሳየና በበቁ ሊቃውንት የተመሰከረለት መጽሐፍ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ አስታውሰዋል፡፡

እንደ ሥራ አስፈጻሚው፣ ኢትዮጵያ 100 ዓመታትን ያስቆጠረ የመጽሐፍ ታሪክ ቢኖራትም፣ የአሳታሚነት ተግባር ግን ገና በወጉ ያልተያዘ፣ በጥራትም በብዛትም ከአገሪቱ ቀደምት የጽሕፈት ታሪክ ጋር የማይመጣጠን ደረጃ ላይ ነው፡፡

የመጽሐፍ ፖሊሲ አለመኖር፣ የወረቀት ውድነት፣ በገበያው ስሜት የሚመራ አሳታሚና ሌሎች ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ በውስን የፋይናንስ አቅም ተቋቁሞ እየሠራና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ለምርምርና ለዕውቀት መስፋፋት የላቀ ማዕከል የመሆን ራዕይ ሰንቆ የሚንቀሳቀሰው የአካዳሚው ፕሬስ፣ ሥራውን የሚመራበት የራሱ የሆነ ፖሊሲ እንዳለው፣ የላቀ የሥራ ፈጠራ ችሎታ ላላቸው ፀሐፊዎችና ተመራማሪዎች የህትመት ዕድሎችን በመስጠት፣ የሳይንስ ባህልን ለመትከልና ያለውን የምርምር ክፍተት ለመሙላት  ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የደራሲው ተወካይ ሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር)፣ መጽሐፉ በረቂቅ ደረጃ ላይ በነበረበት ጊዜ ከ2300 በላይ ገጾች እንደነበሩት፣ ይህም ለህትመትም ሆነ ለንባብ አስቸጋሪ ሆኖ በመገኘቱ ወደ 700 ዝቅ ተደርጎ እንዲታተም መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ሳይታተሙ በቀሩት ገጾች ላይ ያሉት ጽሑፎች ግን በሚገባ በአንድ ላይ ከተጠረዙ በኋላ በሁለት ኮፒ ተዘጋጅቶ አንደኛው ቅጂ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ቤተ መጻሕፈት፣ ሌላኛው ቅጂ ደግሞ በኢትዮጵያ ጥናት ድርጅት እንዲቀመጥ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ተመራማሪዎቹ በፈለጉ ሰዓት ከሁለቱ በአንደኛው ድርጅት እየቀረቡ ጽሑፉን እንደወረደ ሊያገኙ እንደሚችሉ፣ ጽሑፍ በቅጂ ተባዝቶ በተጠቀሱት ድርጅቶች እንዲቀመጡ የተደረጉት ደራሲው ፈቃደኛ ሆነው በመገኘታቸው ነው፡፡

በመጽሐፉ ላይ አጠር ያለ ዳሰሳ ያደረጉት ያየህራድ ቅጣው (ዶ/ር)፣ መጽሐፉ በደራሲው የግል ታሪክ ዙሪያ ያተኮረ ይምሰል እንጂ በአገር ደረጃ የተከወኑ ወይም ኢትዮጵያ ለ17 ዓመት ያህል ምን እንደምትመስል ፍንትው ተደርጎ የተገለጸበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ደራሲው ከፍተኛ ዲፕሎማት፣ የሕግ ባለሙያና የጠነከረና የማያወላውል አቋም ያላቸው መሆኑን በመጽሐፉ ከሰፈሩት ጽሑፎች ለመረዳት እንደቻሉ ጠቁመው፣ በተለይ ደርግን በትክክል ለማዋቀርና አባላቱንም በየሥራ መስኩ ለማስቀመጥ የተከናወነውን ሥራ በበጎነት እንዳስቀመጡት በዚህም እንቅስቃሴ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም የተጫወቱትን ሚና በአዎንታዊ ጎን እንደሚያነሷቸው አስረድተዋል፡፡

የዕድገት በሕብረት፣  የዕውቀትና ሥራ ዘመቻ ከሐሳብ መጠንሰሱ ጀምሮ እስከ አፈጻጸሙ ያጋጠሙትን ፈተናዎችንና የተመዘገቡ ውጤቶች በዝርዝር የቀረበበት መጽሐፍ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር የነበራቸውንም ግንኙነት በተመለከተ እንደተብራራው፣ አልፎ አልፎ በአንዳንድ ቃላት ደራሲውን ቢወርፏቸውም ጥሩ ግንኙነት እንደበራቸው፣ ቀስ በቀስም ፕሬዚዳንቱ ወደ አምባገነንነት ባህሪ እንዴት እንደተዘፈቁ፣ በጥሩ የቃላት አጠቃቀም ለማስረዳት ጥረት ማድረጋቸውን (ዶ/ር) ያየህራድ ጠቁመዋል፡፡

ኤርትራን በተመለከተም በሥራ ለብዙ ዓመታት የቆዩበት ከመሆኑም ባሻገር ባለቤታቸው የዛው አገር ተወላጅ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ልጆች ማፍራታቸውን፣ ይህም ሆኖ ግን ሥርዓቱ በፈጸማቸው ስህተቶች የተነሳ ሳንጠቀምባቸው የቀሩ ዕድሎች መኖራቸውን ከደራሲው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ደራሲው ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፣ መጽሐፉን ያዘጋጁት ለ30 ዓመታት ያህል አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ በጥገኝነት በኖሩበት ዘመን መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም የተባበሯቸውን ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ሁሉ አመስግነዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...