Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

​​​​​​​ዓባይን  እየገራ ያለው ትውልድ አገሩን ከግጭት አዙሪት ውስጥ ያውጣ!

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት መከናወኑ በጣም ያስደስታል፡፡ የግድቡ የመጀመርያውና የሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት እንዲሳካ ያደረጉ ወገኖች በሙሉ፣ ታላቅ ክብርና ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ ለዘመናት በቁጭትና በብሶት ስሙ ይነሳ የነበረው ዓባይ ወንዝ ተገርቶ፣ ለሁለተኛ ጊዜ የድል ብሥራት ሲሰማ ይህ ትውልድ ትርጉሙ ምን ማለት እንደሆነ መረዳት አለበት፡፡ ከደስታ ባሻገር ኢትዮጵያን ከድህነት ወደ ባለፀጋነት ለሚያሸጋግሩ የወደፊት ታላላቅ ፕሮጀክቶች በብቃት መዘጋጀት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሚያምርባቸው በአንድነት ቆመው አገራቸውን ሲያለሙና ሲያሳድጉ እንጂ፣ የከፋ ድህነት ውስጥ ሆነው እርስ በርስ ሲተላለቁ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን የሚያጠፋ የጦረኝነት አስተሳሰብ መቆም አለበት፡፡ የአስተሳሰብ ልዩነት ለጋራ ዕድገት የሚበጁ የተሻሉ ሐሳቦች የሚፈልቁበት እንጂ፣ ንፁኃን ለዕልቂት የሚዳረጉበትና የደሃ አገር አንጡራ ሀብት የሚወድምበት የመሰሪዎች መሣሪያ መሆን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያውያን ከዘግናኝ ድህነት ውስጥ መንጥቆ የሚያወጣቸው፣ በእኩልነትና በነፃነት የሚያኖራቸው ሥርዓት ግንባታ ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡ ለዘመኑ አስተሳሰብ የማይመጥን የጦረኝነት አባዜን አዲሱ ትውልድ መፀየፍ አለበት፡፡ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍፃሜ አድርሶ አገሩን በኩራት አንገቷን ቀና ለማድረግ የተነሳው ትውልድ፣ ለዘመኑ አስተሳሰብ የማይመጥኑ ጦረኞች መቀለጃ መሆን የለበትም፡፡ ትውልዱ አገሩን ይታደግ፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል አይቀሬ የሚመስለው ጦርነት አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሥልጣኔ ፋና ወጊነት፣ በቀደምት ምድርነት፣ በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ  ቅርሶች ባለቤትነት፣ በአስደማሚ ታሪኮችና በበርካታ አንፀባራቂ ታሪኮቿ የምትታወቅ ድንቅ አገር ብትሆንም እንደገና የግጭት አዙሪት ውስጥ እየገባች ነው፡፡ ይህች ታሪካዊት አገር የበርካታ ማንነቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና እምነቶች ባለቤት ከመሆኗም በላይ፣ በተለያዩ ዘመናት ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው የጠበቋት ልጆቿ ዳግም እርስ በርስ ሊፋጁ ነው፡፡ በየዘመኑ በተነሱ ገዥዎች ሥር በጭቆና ብትተዳደርም አንድም ጊዜ ለውጭ ወረራ ያልተንበረከከች፣  በተፈጥሮ በታደለችው መልክዓ ምድሯ ውስጥ የሚመነጩ በርካታ ወንዞች ያሏት፣ ተዝቀው የማያልቁ የተለያዩ ማዕድናት የታቀፈች፣ መጠነ ሰፊ ለም መሬት፣ ለኑሮና ለግብርና የሚመቹ የተለያዩ የአየር ፀባዮች፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፍ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ስጦታዎችን የታደለች አገር የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመባት ነው፡፡ እናት አገሩን ወደር በሌለው ፍቅርና ጀግንነት ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበለ የጠበቀ ኩሩ ሕዝብ ጦርነት አይገባውም ነበር፡፡ ታላቁን ግድብ ገንብቶ ሁለት ዙር ውኃ በመሙላት ታሪክ እየሠራ ያለ ጀግና ሕዝብ፣ ለልማት በኅብረት መነሳት እንጂ በጀብደኞች ምክንያት የግጭት አዙሪት ውስጥ መግባት የለበትም፡፡

ኢትዮጵያን የሰላም፣ የፍትሕና የነፃነት አገር ማድረግ የሚቻለው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንጂ፣ አሁን እንደሚታየው ጦርነት ቀስቅሰው ሕዝቡን ደም በሚያቃቡ  ጀብደኞች ፍላጎት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት ነው፡፡ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማፈንገጥ አገርን የጦርነት አውድማ ማድረግ ከጥፋት በስተቀር ትርፍ የለውም፡፡ ሕዝቡን ከድህነት ማጥ ውስጥ ለማውጣት የሚያስፈልገው ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ሥርዓት ብቻ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት የሚገነባው በሠለጠነ አስተሳሰብ እንጂ ዘመን ባለፈበት አስተሳሰብና በጠመንጃ አምላኪነት አይደለም፡፡ ለአገር የሚበጅ ሥርዓት ዕውን ሊሆን የሚችለው በሕዝብ ፍላጎት እንጂ በጀብደኝነት አይደለም፣ ሆኖም አያውቅም፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በማይመጥን ኋላቀር አስተሳሰብና በጀብደኝነት መንፈስ በሕዝብ ስም የሚቆምሩ ሊበቃቸው ይገባል፡፡ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ በሕዝብ ስም መነገድ የለየለት ቁማርተኝነት ነው፡፡ የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት አደጋ ውስጥ በመክተት የረከሰ ዓላማን ለማሳካት የሚደረግ አደገኛ ሙከራ በፍጥነት መቀልበስ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የምታድገው የተፈጥሮ ፀጋዎቿን በመጠቀም እየለማች እንጂ፣ ጀብደኞች በሚቆሰቁሱት አውዳሚ ጦርነት አይደለም፡፡

ይህ ታላቅ ሕዝብ በየዘመኑ የተነሱበት ገዥዎች ያደረሱበትን መከራና ሥቃይ ችሎ፣ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን ዕቅዳቸውን በማክሸፍ አገሩን ሳያስደፍር ኖሯል፡፡ በገዛ አገሩ ባይተዋር ተደርጎ የኖረ ሕዝብ እንደ ገዥዎቹ ሳይሆን እርስ በርስ ተከባብሮና ተስማምቶ ከመኖር በላይ፣ ተጋብቶና ተዋልዶ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ በደጉም ሆነ በክፉ ጊዜ ከልዩነቶቹ ይልቅ አንድነቱን አጉልቶ ይህችን ኅብረ ብሔራዊት አገር ታድጓል፡፡ በታጋሽነቱ፣ በአርቆ አሳቢነቱና በአስተዋይነቱ ዘር፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ባህልና የተለያዩ ልዩነቶች አንድነቱን አልሸረሸሩትም፡፡ የእናት አገሩን ሰንደቅ ዓላማ ከፊት አስቀድሞ በደሙ መስዋዕትነት ሲከፍል ኖሯል፡፡ ይህችን ታላቅ አገር እያስከበረ የኖረ ታላቅ ሕዝብ አደራ ምንጊዜም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ በተለይ አገራቸውን በተለያዩ ዘርፎች እንቅልፍ አጥተው አገልግለው ያለፉ ወገኖችም ሆኑ፣ በዓለም አደባባይ ስሟን ያስጠሩ ታዋቂዎች አገራቸው ታላቅ ትሆን ዘንድ ብርቱ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ ይህንን ተጋድሎ የበለጠ እያደመቀ ያለው ይህ ትውልድ አገሩን ታላቅ ከማድረግ በላይ የሚያኮራ ተግባር ስለሌለው፣ በጀብደኞች የሚቀሰቀስ ግጭት እንዲቆም በአንድነት መነሳት የግድ ይለዋል፡፡

በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን ከመቼውም በበለጠ ታላቅ ለማድረግ ጥረቶች ቢኖሩም፣ እነዚህን ጥረቶች የሚፈታተኑ ችግሮች በስፋት ይታያሉ፡፡ የአገሪቱ ሕዝብ አሁንም ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ባለው ሰፊ መልክዓ ምድር ውስጥ እየኖረ ሥነ ልቦናው ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ከሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ውጪ ልዩነት በማራገብ የአንድ አገር ልጆችን የሚያፋጁ ኃይሎች በቃችሁ መባል አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ልማት እንጂ ዕልቂትና ውድመት አይፈልጉም፡፡ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለስምንት ወራት የተካሄደው ጦርነት ያደረሰው ዕልቂትና ውድመት አልበቃ ብሎ፣ እንደገና መጠነ ሰፊ ጦርነት ለማከናወን በግራም በቀኝም ዝግጅቱ እየተጧጧፈ ነው፡፡ ለሌላ ዙር ፍጅት ዝግጅት ሲደረግ ጦሱ ከባድ እንደሚሆን መገንዘብ ይገባል፡፡ ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ አይቀሬው ጦርነት እየተቃረበ ይመስላል፡፡ ዳግም ዕልቂትና ውድመት በመደገስ ለታሪካዊ ጠላቶች አገርን ማመቻቸት ወንጀል ነው፡፡ ለኢትዮጵያዊያን የሚያዋጣው ተባብሮ በመሥራት አገራቸውን ማልማትና ከድህነት አዘቅት ውስጥ መውጣት ነው፡፡ ጦርነት ከዕልቂትና ከውድመት በስተቀር ምንም አይገኝበትም፡፡ ጦርነት ለዚህች ታላቅ አገር አይመጥንም፡፡

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ከእያንዳንዱ ዜጋ ጀምሮ የቡድኖች መብት መከበር አለበት፡፡ በተለይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን መታገል ተገቢ ነው፣ መብትም ነው፡፡ ነገር ግን የትግሉ መነሻና መድረሻ አገርና ሕዝብ መሆን አለበት፡፡ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ሕዝብ የማያምንበትንና ለዘመናት ሲፀየፍው የኖረውን ዘረኝነት ማቀንቀንና አገርን ለማተራመስ መሞከር ሊታሰብ አይገባም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በዚህ መንገድ ተገንብቶ አያውቅም፡፡ በሕዝብ ስም እየማሉ ከሕዝብ ፍላጎት ማፈንገጥ ለአገር አይበጅም፡፡ ይህች ታላቅ አገር የምትሻው ወደ ነበረችበት ታላቅነቷ ከፍ ማለት ነው፡፡ ከድህነት አዘቅት ውስጥ እንድትወጣና ዜጎቿን በእኩልነት የምታስተናግድ እንድትሆን፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ልጆቿ የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ጦርነት መመለስ የለባትም፡፡ አስመራሪ ከሆነው ድህነት መገላገል አለባት፡፡ ፍትሕ ሊነግሥባት ይገባል፡፡ ዴሞክራሲ ሰፍኖ ልጆቿ በነፃነት ኮርተው መኖር አለባቸው፡፡ የጀመረቻቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከግብ ደርሰው በረከታቸው በፍትሐዊነት የሚዳረሱባት አገር መሆን አለባት፡፡ እውነተኛው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን እንዲሆን፣ ልጆቿ ልዩነቶቻቸውን በሠለጠነ መንገድ አስታርቀው እጅ ለእጅ ሊያያዙ ይገባል፡፡ ያኔ ኅብረ ብሔራዊት አገር ዕውን ትሆናለችወደ ታላቅነትም ትገሰግሳለች፣ ይህንን ማሳካትም አያቅትም፡፡ ዓባይን እየገራ ያለው ትውልድ ኢትዮጵያን ከግጭት አዙሪት ውስጥ ማውጣት ግዴታው መሆን አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...