Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል​​​​​​​ዒድ አል አድሃ- ‹‹የመስዋዕት ክብረ በዓል››

​​​​​​​ዒድ አል አድሃ- ‹‹የመስዋዕት ክብረ በዓል››

ቀን:

በእስላማዊው የጨረቃ አቀማመርዙልሂጃህ ወር (ለዘንድሮ ሐምሌ) 10ኛው ቀን ላይ የሚውለው ዒድ አል አድሃ፣ ‹‹የመስዋዕት ክብረ በዓል›› ይባላል፡፡ ማክሰኞ ሐምሌ 13 ቀን 2013 ዓም ላይ ውሏል፡፡

የአረፋን በዓል አስመልክቶ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በዓሉ ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ለኢትዮጵያ አንድነትና አብሮነት ‹‹ዱአ›› በማድረግ መሆን አለበት ብለዋል። የአረፋ በዓል እርድ የሚከናወንበት ለጎረቤትና የተቸገሩ ወገኖች በማካፈል የሚከበር መሆኑን ገልጸዋል። 

በኢስላሚክ ካላንደር አሥራ ሁለተኛና የመጨረሻ ወር የሚከበረው ዒድ አልአድሃ ወደ መካ የሐጅ ጉዞ ይደረግበታል፡፡ የወሩ መጠርያ ‹‹ዙልሂጃህ›› ጥሬ ትርጉሙ የሐጅ ወር ነው፡፡ በዚህ ወር ሙስሊሞች ወደ መካ ካባ የሚዘልቁበት ነው፡፡

- Advertisement -

ዒድ አልአድሃ መነሻው ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ኢስማኤልን ለመሰዋት ለአላህ ያሳዩት ታዛዥነትና ታማኝነት ነው፡፡ ኢብራሂም ልጃቸውን ለመስዋዕት  ሲያዘጋጁ  በምትኩ በግ  ለመስዋዕትነት የቀረበበት ነው፡፡ ይህንኑ ድርጊት ተከትሎ ለአረፋ ሕዝበ ሙስሊሙ በግ አርዶ ማዕዱን ይቋደሳል፡፡ የተዘጋጀውን ምግብ ከፊሉን ለደሃና ለሚያስፈልጋቸው፣ ሌላውን ለቤተሰብና ቀሪውን ለቤተዘመድ እንዲከፋፈል ይደረጋል፡፡

የአረፋ አከባበር ሌላ ታሪካዊ ዳራ እንዳለው ይወሳል፡፡ 

‹‹አደምና ሃዋ የፈጣሪያቸውን ትዕዛዝ በማጉደላቸው የተነሳ ከገነት ወደ ምድራዊ ዓለም ተባረው 

ተለያይተው ከኖሩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት  አርዱል አረፋ ተብሎ በሚጠራው 

የአረፋ ኮረብታ ላይ በመሆኑ ረፍኪኒ፣ አረፍቲኒ መባባላቸው ይታሰብበታል፡፡›› ይላል አንድ ሰለ በዓሉ የሚገልጽ ድርሳን፡፡

የአረፋ ነባር አከባበር

የአረፋ በዓል ከሚከበርባቸው አካባቢዎች በደቡብ ክልል የሚገኘው የጉራጌ ዞን  ይጠቀሳል፡፡ ስለ ዒድ አል አድሃ አከባበር  ያገኘነውን መረጃ እንዲህ አቀናብረነዋል፡፡

ጉራጌና የባህል እሴቶቹበሚል ርዕስ  በዞኑ የባህል ጥናትና ልማት የሥራ ሒደት  በተዘጋጀው መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው፣ በጉራጌ ከሚከበሩት ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት መካከል የአረፋ በዓል አንዱ ነው፡፡ ይህ በዓል የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በሆኑት የብሔሩ ተወላጆች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ደምቆ ይከበራል፡፡

 ለአረፋ በዓል የሚደረገው ዝግጅት በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብለው ባሉት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ በዚህም እናቶች ለበዓሉ የሚሆን መጪ (ምርጥ) ቆጮ፣ ቅቤ፣ ሚጥሚጣወዘተ ሲያዘጋጁ ሴቶች ልጆቻቸው ደግሞ የመኖሪያ ቤቶችን በማስዋብ፣ የመመገቢያ ቁሶችን በማጽዳትና ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ቅድመ መሰናዶዎችን በማሟላት ሥራ ይጠመዳሉ፡፡

ልክ እንደ ሴቶቹ ሁሉ ወንዶቹም ለአረፋ በዓል የሚያከናውኗቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ፈልጦ ማዘጋጀት፣ ለእርድ የሚሆን ከብት ማቅረብ በአባቶችና በወንድ ልጆቻቸው የሚከወን ይሆናል፡፡

አረፋ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው የጉራጌ ተወላጅ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ ከየሚኖርበት የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ የትውልድ ቀዬው የሚመለስበትና በዓሉን ከወላጆች፣ ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ ከአብሮ አደግ ጓደኛወዘተ ጋር በመሆን የሚያከብርበት ታላቅ በዓል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የአረፋ በዓል በሥራ ምክንያት ተራርቆ የቆየውንም ሙስሊም የጉራጌ ተወላጅ ከያለበት አሰባስቦ የሚያገናኝም በዓል ነው ለማለት ይቻላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአረፋ በዓል ቀደም ሲል ተጫጭተው የቆዩ የሚሞሸሩበት፣ ሌሎች ደግሞ በቀጣዩ ሦስት ጉልቻ ለመመሥረት የትዳር ጓደኛቸውን የሚመርጡበትና በባህሉ መሠረት የሚያጩበትም ጭምር መሆኑን የብሔረሰቡ ተወላጆች ያስረዳሉ፡፡ ሌላው የአረፋ በዓል ያለው ማኅበራዊ ፋይዳ በተጣሉ ሰዎች መሀል እርቀሰላም እንዲወርድ የማስቻል ብቃቱ ይሆናል፡፡ ከበዓሉ በፊት የተቀያየሙ ባልና ሚስት፣ ልጅና ወላጅ፣ ጎረቤታሞችወዘተ በአረፋ ሰሞንይቅርተባብለው ሰላምን ያወርዳሉ፡፡ ለበዓሉ የተዘጋጀውን አብረው በመብላትና በመጠጣት ይደሰታሉም፡፡

የአረፋ በዓል ሌላው ማኅበራዊው ፋይዳው ከአራቱም ማዕዘናት በዓሉን ለማክበር ወደ ትውልድ አካባቢው የመጣው ሙስሊሙ የጉራጌ ተወላጅ በቤተሰባዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ መክሮ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሔዎችን የሚሻበት መሆኑ ይሆናል፡፡ የቤተሰብ ሕይወት እንዲሻሻልምን ይደረግ?” በአካባቢው ልማት እንዲስፋፋምን እንሥራ?” ብለው ለበዓሉ እትብታቸው ወደ ተቀበረበት ምድር የተመለሱት በአንድነት ከቤተሰብ እና ከማኅበረሰቡ ጋር ይመክራሉ፡፡ መፍትሔዎችንም ያበጃሉ፡፡

በአጠቃላይ የአረፋ በዓል ሙስሊም በሆነው የጉራጌ ተወላጅ ዘንድ ሁሉ ከፍተኛ ግምት ሰጥቶት የሚከበር በዓል ሲሆን ከመብላትና መጠጣቱ ባሻገር ሌሎች ብዛት ያላቸው ቤተሰባዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎችም ጭምር ያሉት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...