Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ሰከን ማለት ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ከ110 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን የሚኖሩባት የብዙኃን አገር ናት፡፡ የተለያዩ ሐሳቦችና ፍላጎቶች ቢንፀባረቁም የፌዴራል ሥርዓቱን በሚገባ ማደራጀት ከተቻለ፣ ኢትዮጵያን በልጆቿ ፅኑ አንድነትና ጥረት ማሳደግ አያቅትም፡፡ ራስን ከማስተዳደር፣ በራስ ከመዳኘት፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ከመማር፣ ቋንቋና ባህልን ከማሳደግ ጀምሮ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሕጋዊ ዋስትና እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በዴሞክራሲያዊና በሰላማዊ መንገድ መመራት እንዳለበት ግንዛቤ በመያዝ፣ በሕግ የበላይነት ሥር መተዳደርን የአገር ባህል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በሕግ ዋስትና ያላቸው መብቶች ተግባራዊ ሆነው የመነጋገርና የመደራደር ባህል ሲዳብር ጦረኛና አውዳሚ አስተሳሰብ አፍላቂ ሳይሆን፣ አጥብቆ ጠያቂና ሞጋች ትውልድ መፍጠር ይቻላል፡፡ ለጦረኝነትና ለአውዳሚነት ቅድሚያ የሚሰጠው ለንግግርና ለድርድር ቦታ ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡ በቅርቡ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተደረገው ጦርነት የበርካታ ወገኖቻችንን ሕይወት አሳጥቷል፡፡ የጦርነት አባዜ ባለቀቃቸው ኃይሎች ምክንያት አሁንም ደም እየፈሰሰ ነው፡፡ ለአገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ህልውና ሲባል የጦርነት ነጋሪነት ጉሰማ ማስቆም ተገቢ ነው፡፡ ይህ በተግባር ይረጋገጥ ዘንድ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን በሰከነ ሁኔታ ያጋጠሙ ችግሮችን መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡ ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የሚበጁ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ ጦርነት ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ከመቅጠፍና የአገር አንጡራ ሀብት ከማውደም የዘለለ ጠቀሜታ የለውም፡፡ ሰከን ብሎ መፍትሔ ላይ ማተኮር ይበጃል፡፡

አገሪቱን ወደ ብተና፣ ሕዝቡን ደግሞ ወደ ዕልቂትና ስደት የሚያመቻቹ አጓጉል ድርጊቶች በመላ ኢትዮጵያዊያን መወገዝ አለባቸው፡፡ በእልህና በጦረኝነት ስሜት ወደ ቀውስ የሚያንደረድሩ አላስፈላጊ ድርጊቶች ይቁሙ፡፡ በተለይ ብሔርንና መሰል ልዩነቶችን እያቀነቀኑ ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ ለማለያየት፣ አገሪቱንም ቀውስ ውስጥ ለመክተት ሌት ተቀን እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ከድርጊታቸው ይቆጠቡ፡፡ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች በአገር ባለቤትነት ስሜት ተንቀሳቅሰው እሳት ለማቀጣጠል የሚፈልጉ ወገኖችን ማስቆም አለባቸው፡፡ ከጦርነት በመለስ በርካታ ሰላማዊ አማራጮች እንዳሉ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ያ ሁሉ ዕልቂትና ውድመት ከደረሰ በኋላ፣ በርካታ ዓመታት በከንቱ ነጉደው የተገኘው ትርፍ ፀፀት እንደነበር ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ ኤርትራዊያንም ያለፉበት ሀቅ ነው፡፡ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ መፈታት የሚችሉ ችግሮች፣ ኃላፊነት በማይሰማቸው ወገኖች እየተጠለፉና አቅጣጫቸውን እየሳቱ ደም መፍሰስ የለበትም፡፡ የጥላቻ ንግግሮች አገር መፍታት የለባቸውም፡፡ በሕግ የበላይነት አማካይነት ያጋጠሙ ችግሮች እንዲፈቱ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ሁሉ ድምፃቸው ይሰማ፡፡ አገርን ከጥፋት መጠበቅ የዜጎች ሁሉ ኃላፊነት ነውና፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ምሁራን፣ አርሶ አደሮች፣ ሠራተኞች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ. ከስሜታዊነት ይልቅ በምክንያታዊነት የሚመራ የአስተሳሰብ ልዕልና ይፈጠር ዘንድ ድምፃቸው ጎልቶ ሊሰማ ይገባል፡፡ ሰከን ማለት ተገቢ ነው፡፡

ሕዝብ ለማገልገል ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ስላለበት ስለአገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ እውነታውን ለሕዝብ ማስረዳት አለበት፡፡ ግልጽነት በአገራችን በተግባር እየታየ ነው ወይ ተብሎ ቢጠየቅ ምላሹ አጥጋቢ አይደለም ነው፡፡ በተወሰኑ ጊዜያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም በየደረጃው ያሉ ሹማምንት አልፎ አልፎ መግለጫ ቢሰጡም፣ የሚጠበቀውን ያህል የሚያረካ አይደለም፡፡ በርካታ ጥያቄ የሚነሳባቸው ጉዳዮች ምላሽ ባለማግኘታቸው እንቆቅልሾች በዝተዋል፡፡ መንግሥት የአገርን የዕለት ሁኔታ በግልጽ ማስረዳት ሲያቅተው ምላሽ የሚሹ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የሚገኘው ከሕዝብ በሚገኝ ፈቃድ ነው፡፡ ይህ ዴሞክራሲ በሰፈነባቸው አገሮች ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን የሕዝብ ነፃ ፍላጎት ነው፡፡ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የምትችለው ነፃ ኅብረተሰብ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረታዊ ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድርና የሕግ የበላይነት መኖር ናቸው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገው ትግል፣ የጥፋት ተዋናዮች በመብዛታቸው ሳቢያ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በየጎራው ጀብደኞች በመበርከታቸው ነው፡፡ ከአገር በላይ ራሳቸውን ያስቀደሙ ጀብደኞች በሕዝብ ስም እየማሉ አገር ሲያተራምሱ፣ የአገር ጉዳይ የሚያገባቸው ወገኖች የማስቆም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ችግሮች የሚፈተቱት በሰከነ መንገድ መሆን እንዳለበት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በአገር ጉዳይ እርስ በርስ በሚደረግ ግንኙነት በሰከነ መንገድ መነጋገር፣ መወያየትና ብሎም መደራደር ትልቅ ጥቅም ያስገኛል፡፡ ከዕለት ተዕለት የንግድ እንቅስቃሴ አንፃር ሲታይ እንኳ በሸማችና በነጋዴ መካከል ያለው ግንኙነት በድርድር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አገሮች በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሲገናኙ የሚቀድመው ድርድር ነው፡፡ ድርድር ግልጽነትና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ የሚከተል ከሆነ ደግሞ ጥቅሙ ለሁለቱም ወገኖች ነው፡፡ መነጋገርና መደራደር መቻል የሰከነ አዕምሮ ውጤት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለዓመታት የዘለቀው የፖለቲከኞች የመነጋገርና የመደራደር ፈቃደኝነት በመጥፋቱ በቂምና በበቀል መፈላለግ፣ የአገሪቱን ፖለቲካ ምን ያህል እንዳሽመደመደው የታወቀ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በአጎራባች ክልሎች መካከል የተስተዋሉ ግጭቶች ለዜጎች ሕይወት መጥፋትና ከቀዬ መፈናቀል ሰበብ የሆኑት፣ በሰከነ መንገድ ለመነጋገርና ለመደራደር ቅድሚያ ባለመሰጠቱ ነው፡፡ እልህና ግትርነት ደግሞ ስሜትን ለማጎንና እሳት ለመቆስቆስ ቅርብ ናቸው፡፡ የሰከነ አዕምሮ በስሜት አይነዳም፡፡ ይልቁንም ጥፋትን በሩቅ ለመከላከል መላ ይዘይዳል፡፡ በተደጋጋሚ እንደምንለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ለዘመናት ደግና ክፉ ጊዜያትን አንድ ላይ አሳልፏል፡፡ በተለይ በርካታ የመከራ ጊዜያትን ያሳለፈውና የሚወዳት አገሩን በጋራ ሲጠብቅ የኖረው በመረረ ድህነት ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ ነገር ግን በማስተዋልና በአርቆ አሳቢነቱ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቹን ጠብቆ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ ይህንን ኩሩና የተከበረ ሕዝብ ሰላሙንና ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን አስጠብቆ ወደ ልማት ማምራት የግድ ነው፡፡ ከግጭት የሚገኘው ዕልቂትና ውድመት ብቻ ነው፡፡ መስከን የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡

የአሁኗ ኢትዮጵያ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ብቻ ነው የሚያዋጣት፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ አገር ከሚመራው መንግሥት ጀምሮ እስከ እያንዳንዱ ዜጋ ድረስ ለአገር ህልውና ማሰብ ይገባል፡፡ ከአገር በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ከሕዝብ በላይ ምንም አይቀድምም፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በተዘረጋው መልክዓ ምድር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በአንድነት የጋራ አገራቸውን እንዲወዱና እንዲያሳድጓት መነጋገርና መደራደር ተገቢ ነው፡፡ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይገታቸው በጋራ አገራዊ ጉዳይ ላይ ተቀምጠው መነጋገር መቻል አለባቸው፡፡ አንድ ማኅበረሰብ የሠለጠነ ነው የሚባለው ልዩነቶቹን ማስተናገድ ሲችል ነው፡፡ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የመሆን ፍላጎት ጊዜ አልፎበታል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት ማግኘት የሚቻለው ለውይይትና ለድርድር ፈቃደኝነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ከቂምና ከጥላቻ የፀዳች አገር የምትኖረውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ክፋት፣ አሻጥር፣ ቁርሾና ጭካኔ ባሉበት ተያይዞ ከመጥፋት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ የሰከነ አዕምሮ ግን ከእነዚህ ደዌዎች የፀዳ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልገው በነፃነት እየኖረ ከድህነት መላቀቅ፣ ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት፣ ማኅበራዊ ፍትሕና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ተሟልቶ ይገኝ ዘንድ ደግሞ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ከኢትዮጵያ ምድር ግጭትም ሆነ ጦርነት እንዲያበቃ ግፊት ማድረግ አለባቸው፡፡ ለዚህም ሲባል ሰከን ማለት ያስፈልጋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...