Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየአማራ ክልላዊ መንግሥት ለክልሉና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ አቀረበ

የአማራ ክልላዊ መንግሥት ለክልሉና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ አቀረበ

ቀን:

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ማክሰኞ ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት፣ ‹‹አንድነታችንን ጠብቀን ያጋጠመንን የህልውና አደጋ በትግላችን እንቀለብሰዋለን›› በሚል ርዕስ ባወጣው ባለአምስት ነጥብ መግለጫ፣ ለክልሉና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ አቀረበ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በአንድ ወገን የወሰደውን የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ የሕወሓት ኃይል በኢትዮጵያና በአማራ ክልል ሕዝብ ላይ መሰረተ ሰፊ የሆነ ወረራና ጥቃት ማድረግ መጀመሩን የክልሉ መንግሥት በመግለጫው አስታውቋል፡፡

‹‹የሕወሓት ኃይል የጀመረብንን ግልጽ ወረራ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያወግዘውና የምንጊዜም አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፍፁም ጥርጣሬ የለንም፤›› ያለው የአማራ ክልል መንግሥት፣ ‹‹በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በግልጽ እንደሚያውቀው የአማራ ክልልና ሕዝብ ቀጥተኛና የቅርብ ተጠቂ መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም ትግላችን ለሕዝባችን ህልውናና ለአገር ሉዓላዊነት መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ፣ የጋራ ጠላታችንን በጋራ እንድንፋለመው የአጋርነት ጥሪያችንን እናቀርባለን፤›› ብሏል፡፡

- Advertisement -

‹‹የሕወሓት ኃይል ከአማራ ክልል ጋር በሚያዋስኑት ሁሉም አቅጣጫዎች መጠነ ሰፊ ወረራና ጥቃት እየፈጸመ የሚገኝ ቡድን መሆኑ እንዲታወቅና ሁሉም የአማራ ክልል ሕዝብ ጉዳዩን ከህልውናው ጋር በማስተሳሰር እንዲመለከተው፣ ከዚህ ቡድን ጋር ቀጣይ የምናደርገው ሁሉን አቀፍ ትግል የህልውና ትግል መሆኑን አውቆ በገንዘብ፣ በጉልበትና በሕይወት መስዋዕትነት አስፈላጊውን አበርክቶ ለማድረግ ራሱን እንዲያዘጋጅና የመንግሥትን ጥሪ እዲጠባበቅ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል፤›› ሲል አሳስቧል፡፡

‹‹ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ ከላይ እስከ ታች በማንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕግጋትን በመቃረን ሕፃናትንና ሴቶችን በጅምላ ጦርነት እየማገደና ያለ የሌለውን አቅሙን ተጠቅሞ ክልላችን ላይ ወረራ ፈጽሟል፡፡ በተለይም ለዘመናት የአማራ ሕዝብ የማንነትና የወሰን ጥያቄ እያነሳ ሲታገልባቸው የቆዩ የራያ አላማጣና ኮረም አካባቢዎችን ዳግም በመውረር፣ እንዲሁም ወልቃይት ጠገዴ፣ ሴቲት ሁመራን በተለይም ጠለምትና አካባቢውን ለመያዝ ሙከራ መጀመሩን ጠቁሟል፡፡ ይህንን ድርጊትና ዳግም ወረራ የክልሉ መንግሥት በፍጹም የማይቀበለውና በጀመርነው የህልውና ትግል ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብታችንን የምናረጋግጥ መሆኑን አበክረን እንገልጻለን፤›› በማለት የክልሉ መንግሥት አስታውቋል፡፡

በየግንባሩ ለሚገኙ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ለክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት፣ ለሕዝባዊ ፖሊስና ሰላም አስከባሪ አባላት ጥሪ ያቀረበው የአማራ ክልል መንግሥት፣ ‹‹እንዲሁም አገርና ሕዝብን ለማዳን የተግባር እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ የምትገኙ የየክልሉ የፀጥታ አካላት በዚህ ታሪካዊ መድረክ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት በመግጠም ለአገራችሁ ሉዓላዊነትና ለሕዝባችሁ ህልውና የምትከፍሉትን ክቡር መስዋዕትነት ታሪክ ምንጊዜም ሲያስታውሰው ይኖራል፡፡ በቀጣይም የተሰጣችሁን ሕዝባዊና አገራዊ ተልዕኮ በፅናትና በቁርጠኝነት እንደምትወጡ እምነታችን የፀና ነው፤›› በማለት፣ ‹‹ስለሆነም መላው የኢትዮጵያና የአማራ ሕዝብ ከጎናችሁ መሆኑን አውቃችሁ በጀግንነት ታሪካዊ ጠላታችንን በመደምሰስ ለአገራችሁ ዳግም የኩራት ምንጭ እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን፤›› ሲል አሳስቧል፡፡

‹‹ለአገራችን ሉዓላዊነት መከበርና የጭቁን ሕዝባችን የህልውና ትግል እንጂ እላፊ ጥቅም ለማግኘት የምናደርው ትግል በፍጹም አይደለም፡፡ የአማራ ሕዝብ ከፉክክር ይልቅ ትብብርን፣ ከእብሪት ይልቅ ድርድርን የሚያስቀድም በፍትሕ ከሄደች በቅሎየ ያለፍትሕ ያጣኋት ጭብጦየ ትቆረቁረኛለች ብሎ የሚያምን ሕዝብ ነው፡፡ ስለሆነም ዛሬ የምናደርገው ትግል ለልጅ ልጆቻችን የምናወርሰው የኩራትና የክብር ምንጭ እንደሚሆን አንጠራጠርም፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የወሰደው ተናጠላዊ የተኩስ አቁም ውሳኔን ተከትሎ የሕወሓት ኃይል አገርና ሕዝብ ለማዋረድ የሚያደርገውን ዕብሪተኛ እንቅስቃሴ መሠረት በማድረግ፣ በጠላት ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወሰድ በአጽንኦት እናሳስባለን፤›› ሲል መግለጫውን ቋጭቷል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄም (አብን) በዕለቱ ተመሳሳይ መግለጫ አውጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...