Tuesday, May 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

​​​​​​​ሕገወጥ ድርጊቶች በፍጥነት ይታረሙ!

በኢትዮጵያ ከብሔራዊ መግባባት በፊት መነጋገርና መደማመጥ መቅደም አለበት፡፡ መነጋገርና መደማመጥ ሊኖር የሚችለው ደግሞ፣ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች ሕግና ሥርዓት ሲያከብሩ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት ሳይከበር ስለብሔራዊ መግባባትም ሆነ ስለሌሎች ጉዳዮች ለመነጋገር ያዳግታል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን መያዝ ያለበት በምርጫ ከሆነ፣ ምርጫ በተቻለ መጠን ከማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ መከናወን ይኖርበታል፡፡ ከምርጫ ፍፁማዊ ተግባር ባይጠበቅም፣ ዋነኛ ተዋናዮቹ ግን መሠረታዊ መሥፈርቶችን በማክበር ነፃ ሆኖ እንዲከናወን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ገዥውንም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የሚመለከት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ በዘንድሮው ምርጫ በተለያዩ ሥፍራዎች አባላቱ የፈጸሙትን አስከፊ ድርጊት ማረም ይጠበቅበታል፡፡ በውስጠ ፓርቲ ዲሲፕሊንም ተገቢውን ዕርምጃ ወስዶ ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ አለበት፡፡ ‹‹ለምጣዱ ሲባል ዓይጧ ትለፍ›› ተብሎ የምርጫው ጦስ አገር እንዳይረብሽ ሲባል አስከፊው ድርጊት ዝም ቢባልም፣ ወደፊት ፈጽሞ ተቀባይነት የማይኖረውና ለአገር ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ እንደሚሆን መታመን አለበት፡፡ በሕገወጦች ምክንያት አገር መረበሽ የለባትምና፡፡ በሌላ በኩል ለሥልጣን ሲባል ብቻ ሐሰተኛ ውዥንብሮችን ሲነዙ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ግለሰቦች፣ ድርጊታቸው ሕገወጥ መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ከሕግ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች የሚያስከትሉት ግጭት ነው፡፡ ግጭት ደግሞ ዕልቂትና ውድመት ነው ትርፉ፡፡ የኢትዮጵያ ፈተና ማብቃት ያልቻለው ሕገወጥ ድርጊቶች በመበራከታቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያን በምታህል ትልቅ አገር የመንግሥት ሁነኛ ቃል አቀባይ ጠፍቶ ሕዝብ ማወቅ ያለበት የአገር መረጃ፣ ምንጫቸው በማይታወቅ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችና የዩቲዩብ አጋፋሪዎች መለፈፉ ያስገርማል፡፡ መንግሥት ለአገሪቱ ሕዝብ ተጠያቂነት ያለበት መሆኑ የተረሳ ይመስል፣ ግለሰቦች በሕዝብ የማወቅ ነፃነት ላይ ሲቀልዱ ዝምታው ያሳዝናል፡፡ በእጁ ያሉትን መረጃዎች ለሕዝብ በቀጥታ ማሠራጨት ሲገባው፣ የአገር መረጃ በማይገባቸው አካላት አማካይነት ሲተላለፍ ነገ የሕጋዊነት ጥያቄ እንደሚያስነሳበት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተከናወነ ስላለው ግጭት በቀጥታ ለሕዝብ የተጣራ መረጃ ማስተላለፍ ሲኖርበት፣ ውዥንብሮች በዝተው በሕዝብ ውስጥ መደናገር እየተፈጠረ ነው፡፡ የመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ለማኅበራዊ የትስስር ገጾች ባለቤቶች ተላልፎ ተሰጥቶ እውነትና ሐሰቱን ለመለየት ያልተቻለበት ጊዜ ላይ በመደረሱ፣ ምንጫቸው በማይታወቅ አካላት የሚሠራጭ መረጃ በአገር ላይ ሽብር እየፈጠረ ነው፡፡ መንግሥት በፍጥነት ለሕዝብ ጥራት ያለው መረጃ በቀጥታ ካላቀረበ፣ ኃላፊነት በጎደላቸው አካላት የሚሠራጩ አደናጋሪ መረጃዎች ቀውስ ይፈጥራሉ፡፡ አሁን የሚታየው ሕገወጥ የመረጃ ፍሰት ተስተካክሎ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥራት ያለው መረጃ በፍጥነት ያግኝ፡፡ ካልሆነ ግን በሕገወጥ ጎዳና መንጎድ መዘዙ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ 

ሕግና ሥርዓት ከሚጣስባቸው መስኮች አንደኛው ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል ነው፡፡ በሥልጣን መባለግ የሚፈጠረው የመንግሥት አሠራር ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ሲጎድለው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዜጎች በሕግ የተሰጧቸው መብቶች ይጣሳሉ፣ የአገር ሀብት የግለሰቦች መጫወቻ ይሆናል፣ በቡድን የተደራጁ ኃይሎች እንዳሻቸው ይሆናሉ፣ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መሬት በጠራራ ፀሐይ እየተወረረ ግለሰቦች ሲከብሩበት ጠያቂ አይኖርም፣ ግብር መሰወርና በኮንትሮባንድ መክበር፣ ያለ ገደብ የቀረጥ ነፃ መብት ተጠቃሚ መሆን፣ የሰዎችን ሕጋዊ ንብረት መቀማት፣ በብሔርና በእምነት እየተሳሳቡ ገደብ አልባ ጥቅም ማጋበስና ሌሎችን ማጥቃት፣ በፖለቲካ አመለካካት ልዩነት ያላቸውን ኃጢያት እየለጠፉ ማሰር፣ ማሰቃየትና የመሳሰሉ ሕገወጥነቶች ይበራከታሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነቶቹ ዓይን አውጣ ድርጊቶች የሚከፉ ደግሞ ሰላማዊውን የፖለቲካ ፉክክር እርግፍ አድርገው በመተው፣ አደገኛ ድርጊት ውስጥ በመሰማራት አገር አውዳሚ ግጭቶችን ይቀሰቅሳሉ፡፡ ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ የበላይ እየሆነ ሲቀጥል ሥርዓተ አልበኝነት ይነግሣል፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መቃቃር እየተፈጠረ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋል፡፡ ለልማት ከሚነሳው ይልቅ ጠመንጃ ወልዋዩ ይበራከታል፡፡

የመንግሥትና የፓርቲ ሥራ መቀላቀል አንድ ሁነኛ መፍትሔ ካልተበጀለት፣ የአንድ ጎራ አመለካካት ሁሉም መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ እየነገሠ ለተቃውሞ መቀስቀስ ምክንያት ይሆናል፡፡ ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ አድርጎ ማደራጀት የሚያስፈልገው፣ የመንግሥትና የፓርቲ ሥራ እንዳይቀላቀል ነው፡፡ በምርጫ ሥልጣን የያዘ ማንኛውም ፓርቲ ተቋማትን በካድሬዎቹ የሚያጥለቀልቅ ከሆነ፣ የፈለገውን ያህል ቸር ሆኖ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ለተፎካካሪ አመራሮች ቢሰጥም ዋጋ የለውም፡፡ የመንግሥት ሥራና የፓርቲ ሥራ መለያየት አለባቸው፡፡ ስትራቴጂካዊ የመንግሥት ተቋማትን የሚመሩ የፖለቲካ ሹማምንት መሆናቸው ተገቢነት ሊኖረው ቢችልም፣ ሥራዎችና ባለሙያዎች የግድ መገናኘት አለባቸው፡፡ ተቋማት የፓርቲ አባልነት መመልመያ ጣቢያ የሚሆኑት ባለሙያና ሥራ ሳይገናኙ ሲቀሩ ነው፡፡ ብዙዎቹ የመንግሥት ተቋማት ከዕቅድ እስከ አፈጻጸም ከሚታሰበው በላይ ድክመት የሚታይባቸው፣ ብዙዎቹ ተሿሚዎች ክህሎትና አቅም ስለሌላቸው ነው፡፡ ለሹመት የሚታጩት በብሔር ኮታ ስለሆነ ተቋማቱ በሚያሳዝን ሁኔታ ከደረጃ በታች ወርደው፣ አገልግሎት ፈላጊውን ሕዝብ ለከፍተኛ እንግልት ይዳርጋሉ፡፡ እንዲህ የሚደራጁ ተቋማት የሕገወጦች መፈንጪያ እየሆኑ ለአመፅ መቀስቀስ በር ይከፍታሉ፡፡ ሕገወጥነት ተቋማትን እያሽመደመደ ዜጎችን በአገራቸው ጉዳይ ባይተዋር ያደርጋቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የግማሽ ክፍለ ዘመን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቁ መሰናክል፣ የፖለቲካ ሥራን በሠለጠነ መንገድ ለመምራት አቅምና ፍላጎት መጥፋቱ ነው፡፡ ምንም እንኳ የፖለቲካ ሥራን ዘመኑን በሚመጥን የዕድገት ደረጃ ለመምራት አቅሙና ብቃቱ ያላቸው ውስን ፖለቲከኞች መኖራቸው ባይካድም፣ በብዛት የሚስተዋሉት ግን ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያስፈልጋቸው ማስተባበል አይቻልም፡፡ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ውስጥ በአመራር ደረጃ ያሉት የተሻለ ደረጃ ላይ ቢገኙም፣ ታችኛው መዋቅር ላይ ግን ለማመን የሚከብዱ ሕገወጥ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ በርካቶች ናቸው፡፡ እንኳንስ የፖለቲካ አመራር ለመስጠት ራሳቸውን ለመምራት ዝግጅት የሌላቸው ሰዎችን ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በዚህ መጠን በተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥም ከስሜታዊነት የዘለለ ለምክንያታዊነት ቦታ የማይሰጡ በርካቶች አሉ፡፡ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሰጡት ሥፍራ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ከላይ ወደ ታች የሚንቆረቆረውን ለማስተጋባት እንጂ የተሻለ ሐሳብ ለማመንጨት ያለው ተነሳሽነት አናሳ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የፖለቲካ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ በማቀራረብ አብሮ ከመሥራት ይልቅ፣ የአገርን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም የሚጎዱ ድርጊቶች ላይ መረባረብ በመብዛቱ አገር ተጎድታለች፡፡ ለሕገወጥነት በር እየተከፈተ ብዙዎች ተገድለዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል፣ ተፈናቅለዋል፡፡

እርግጥ ነው መቼም ቢሆን በአገር ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ፍፁም መሆን አይቻልም፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ አገር አቀፍ ድረስ በርካታ ውጣ ውረዶች መኖራቸው የግድ ነው፡፡ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ በበርካታ ጉዳዮች ከተቀመጡ መሥፈርቶች አማካይ ደረጃ ላይ ለመገኘት መሞከር፣ በሒደት ትልቅ ደረጃ ላይ እንደሚያደርስ መተማመን የግድ ነው፡፡ ለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ ለሕግ የበላይነት መከበር ጥረት ማድረግ የአገር ባህል መሆን አለበት፡፡ ሕግና ሥርዓት ሲኖር አድሏዊነት፣ ሌብነት፣ ጉልበተኝነት፣ ዕብሪት፣ ከመልካም ባህሪ ተፃፃሪ መሆን፣ አስመሳይነትና የመሳሰሉት ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ምርጫ ሲካሄድ ሰላም ብቻ ሳይሆን ነፃነት ይኖራል፡፡ ሥልጣን የሕዝብ ፈቃድ መገለጫ ይሆናል፡፡ የአገር ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይከፋፈላል፡፡ ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው ይረጋገጣል፡፡ በሥልጣን መባለግ ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀል ይሆናል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት በነፃነት ተደራጅተው ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡ የሲቪክ ማኅበራት ያብባሉ፡፡ የዘፈቀደ እስርና ማንገላታት ይቆማሉ፡፡ ሚዲያዎች በነፃነትና በኃላፊነት ስሜት ተግባራቸውን ይወጣሉ፡፡ ፍርድ ቤቶች በነፃነት ይሠራሉ፡፡ የፀጥታ ኃይሎች በሕጉ መሠረት ብቻ ሥራቸውን በገለልተኝነት ያከናውናሉ፡፡ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት መርህ መሆናቸው በተግባር ይረጋገጣል፡፡ ለዚህም ሲባል ሕገወጥ ድርጊቶች በፍጥነት መታረም ይኖርባቸዋል

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...