Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​​​​​​​አቅጣጫ ስተናል!

ጉዟችን ተጀምሯል። ከፒያሳ ወደ መገናኛ ልንጓዝ ነው። ‹‹የስሜቴ ጌታ የዕድሌ ባለቤት፣ የምወዳትን ልጅ አርግልኝ ጎረቤት›› ይላል ለዛው የማይነጥፈው መስፍን አበበ። ነፍሱን ይማረውና ተሳፋሪዎች ይወዘወዛሉ። ‹‹ ሰው መሆን!›› ይላል አጠገቤ የተሰየመ ወጣት። ‹‹ምኑን አይተኸው ደግሞ በዚህ ዕድሜህ? ባይሆን በእኛ ያምራል…›› ይሉታል ከጀርባችን የተሰየሙ ጎበጥ ያሉ አዛውንት። ‹‹ደግሞ ብለን ብለን በሚያምርብንና በማያምርብን እንጣላ?›› ሲላቸው ከአንገታቸው እየተወዛወዙ በዝምታ አለፉት። ይኼኔ አዝማቹን ጨርሶ መስፍን ቀጥሏል። ‹‹አንተ አሞራ እባክህ ተላከኝና ብሎ መለየት በአንተ ያምራልና›› ይላል። ተሳፋሪዎች ከአዝማቹ እኩል በአቤት አቤት ይወዛወዛሉ፡፡ በሐሳብ የነጎዱት ፈዘው ተቀምጠዋል። ‹‹የዘንድሮ ነገር የተገላቢጦሽ፣ አህያ ወደ አደን ውሻ ወደ ግጦሽ፣ የዘንድሮ ጉዴን እኔ ምን አውቃለሁ፣ እንዲሁ በሆዴ እብሰለሰላለሁ…›› ሲል፣ ‹‹መብሰልሰልስ ቢሉህ መብሰልሰል ነው እንዴ?›› ይላሉ አዛውንቱ አቀንቃኙን በአካል እንደሚያናግሩ ሁሉ። ተጀመረ ማለት ነው!

ከሚናገረው የማይናገረው በዝቷል። አዛውንቱና መሀል ወንበር የተቀመጠ ወጣት እየቆያዩ የዘፈኑን ግጥም ተከትለው አንድ፣ አንድ ይላሉ። ደርሶ ሆድ የሚብሰው ሰው አየኝ አላየኝ ሳይል በዓይኑ ያቀረረ ዕንባውን አንኳሎ ሲያበቃ፣ ‹‹ሶፍት ይዛችኋል?›› ብሎ አጠገቡ ያሉትን ይጠይቃል።አልያዝንምየሚለው ሲበዛ፣ ሲያልፍ ሲያገድም ከእኔም፣ ከእሷም፣ ከእሱም በተነካካበት ወዛም መዳፉ ጉንጩን ይጠርጋል። ይኼን በሰያፍ ያስተዋሉት አዛውንት ቀና ሳይሉ ዘወር ሳይሉ፣ ‹‹አይዞህ ወንድ ልጅ ዋጥ ነው…›› ይላሉ። ማን ለማን፣ ለምን በምን ምክንያት እንደሚናገር ዓይኑን መቆጣጠር አቅቶት እንደሚያነባና በምን ምክንያት እንደሚስቅ ግራ ያጋባል። መንገድ የሁሉም ነውና ዛሬም በትናንትናው ጎዳና በተዳከመ፣ በተሰላቸ፣ በተበራታ፣ ተስፋ በሰነቀ ዝብርቅርቅ ስሜት ተሰባስቧል። መንገድ ሁሉን እንደ ቅኝቱና እንደ ዜማው እያገጣጠመ ደግሞም እያሸዋወደ ያስጉዘዋል። ወደፊት!

ገሚሱ ስለሰሞንኛው የፖለቲካ ውሽንፍር ይቀዳል። ገሚሱ ስለትናንት ማታ አመሻሹና አዳሩ ገጠመኙን እየጨመረ እየቀነሰ አብሮት ካለው ወዳጅ ጋር ያሽካካል። ጥቂቱ ስለሥራና ኑሮ በሹክሹክታ ይነጋገራል። በዚህ መሀል አንዱ ስልኩን ጮክ አድርጎ ከፍቶ ወዳጁን የት ነህ ሲለው ይሰማናል። ‹‹አሁን ከቢሮ ሾልኬ ወጥቼ ወደ ምሽግ እየሄድኩ ነው…›› ይላል የወዲያኛው። ‹‹በቃ ጦርነት ተጀመረ የሚባለው ዕውን ነው ማለት ነው?” ይላል ሌላው ወሬ ጠልፎ። ‹‹የምን ጦርነት?›› ይሉታል እንቅልፍ ሸለብ አድርጓቸው የነበሩ ወይዘሮ ባነው። ለእሳቸው መልስ ሳይሰጥ የስልኩ ወሬ ቀጠለ።       ‹‹አትመጣም ዲያ?›› ይላል በወዲያ በኩል። ይኼኛው፣ ‹‹ዛሬ ቻፓ የለም፣ ተጋባዥ ድምፃዊ ነህ ካልከኝ ግን ከች እላለሁ…››  ይለዋል። ‹‹ዛሬማ ምን የመሰለ ጫት ነው የማስቅምህ። ባለፈው የነገርኩህን ሰውዬ እኮ አዋክቤ ሃምሳ ሺሕ አስወርጄዋለሁ። በቃ አፍጥነው…›› ሲለው ሰማን። ስልኩ ተዘጋ። በለው!

‹‹እኔ እኮ ምሽግ ሲል ለአገር ዳር ድንበር ዋጋ ሊከፍል የመከላከያ ሠራዊቱን የተቀላቀለ መስሎኝ እኮ ነው። ለካ የበርጫውን ጀማ ነው ምሽግ  የሚለው?›› ሲል ያደረቀን ተሳፋሪ፣ ‹‹ይብላኝ እሱ ፈጣሪ መርጦ መርቆ በአባቶቻቸው የእናት አገር ፍቅር ስሜት አጥምቆ ሲፈጥራቸው ለለያቸው ልጆቻችን እንጂ፣ ዘንድሮ እናንተማ ታስፈጁን ነበር…›› ብለው ወይዘሮዋ ስላቅ ጀመሩ። ‹‹ምን አባታችን እናድርግ ብለው ነው? ይኼው እኛም እኮ ከተማ ለከተማ የቻልነውን ያህል ቀማኛና ዘራፊውን እያደንን እያስተፋን ነው…›› ቢላቸው ተጋባዥ ድምፃዊ ነህየተባለው ወጣት፣ ‹‹አይ ይኸው እያየናችሁ አይደለም እንዴ? አገር በምድረ ሌባ እንደ ቆዳ ተወጥራ ዳር ተቀምጣችሁ ስትሰፉ ውላችሁ ስትሰፉ ስታድሩ። የተሰበረ ቅስማችሁን ሳትጠግኑ ምርቃና ሰበራ እያላችሁ አገሩም ዳንኪራ ቤት ብቻ ሆነ…›› ሲሉ፣ ሁሉም በዝምታ ሰምቶ እንዳልሰማ አንገት ደፉ።ቢደፉን እንጂ የተደፋነው፣ ወደን አይደለም የተተፋነውአሉ ነው የተባለው ገንዳውን የሞሉ ቆሻሾች በኅብረት ድምፅ? ይብላኝ ለጠራጊው!

ኋላ መጨረሻ ከተሰየሙት ተሳፋሪዎች ጨዋታው ድንግር ያለው አንድ ቆዳ ጃኬት ለባሽ፣ ‹‹እኔ ምለው ቤትና ስፖኪዮ እኩል ሆኑ እንዴ?›› ብሎ መጠየቅ። ‹‹እንዴት?›› ሲሉት አጠገቡ ያሉት፣ ‹‹እንዲህ እንደ ቀላል ነገር ተነቅሎ የሚጠፋው ስፖኪዮ እንጂ ቤት አልነበረም ብዬ ነዋ…›› አለ። ‹‹በል ከዛሬ ጀምሮ ነው ብለህ ማመን አለብህ። በዚህ የስርቆቱን መራቀቅና ዓይን አውጣነት በቅጡ ካልተዳህ፣ ነገ ኢትዮጵያ ራሷ ስትሰረቅ ሐዘኑን የመቋቋም ጉልበት አይኖርህም…›› ብሎት አረፈው አንዱ። ሰው ሰውነትን ለማዳበር ጂም ይገባል፣ እዚህ የነገን ሐዘን ለመቋቋምንባ ይቆጥባል። ዕንባ ቆጣቢ ተቋም ቢቋቋምልን ግን እንዴት አሪፍ ነበር!

ጉዟችን ቀጥሏል። አጠገቤ የተቀመጠችው የውበት እመቤት ከጓደኛዋ ጋር በስልክ ስለወርኃዊ ወጪዋ ታወራለች። ‹‹ብታምኝም ባታምኝ ለካርድ ብቻ በወር ሁለት ሺሕ ብር አወጣለሁ። እኔማ ቁጭ ብዬ ሳስበው ግራ የገባኝ ነገር ዕውን በእኔ ኃይል ነው እየኖርኩ ያለሁት በእሱ ቸርነት?›› ትላታለች። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ወጣቶች አንዱ፣ ‹‹ለምን መስመር አታደርጊውም?›› ይላል። ‹‹መስመር ለማድረግ የንግድ ፈቃድ ያስፈልጋታል…›› ይላል ሌላው። ‹‹መስመር ምንድነው?›› ብለው አዛውንቱ መጠየቅ። የአዛውንቱን ጥያቄ ችላ ብሎ ባለቆዳ ጃኬቱ፣ ‹‹መስመር ለማድረግ የሚያስፈልገው ንግድ ፈቃድ ብቻ አይመስለኝም፣ ሌላ መስመር ሳይኖረው አይቀርም…›› አለ። ‹‹ኧረ የመስመር ያለህ? አስምራችሁ ጨረሳችሁን እኮ እናንተ? ምንድነው መስመር?›› አዛውንቱ በስጨት አሉ። ‹‹እኛም አናውቀውም ፋዘር። አቅጣጫ አሳይተው መስመር ሲሉ ሰማን ተከተልናቸው…›› ብሎ አጠገባቸው የተሰየመው ወጣት መለሰላቸው። ይገርማል!

‹‹እናንተ ዝም ብላችሁ የሰው መስመር የምትከተሉት የራሳችሁ መስመር የላችሁም እንዴ?›› ሲሉ፣ ‹‹ቢኖረንስ አባት? በቀይ የተሰመረና በነጭ የተቀለመ አንድ ነው እንዴ?›› አለቻቸው ሒሳብ ለማውጣት ትልቅ ቦርሳዋን ስትከፍት በፌስታል የተቋጠረ ደረቅ እንጀራዋን ያየንባት ጠይም። ‹‹ምን እሱ ብቻ? እንዳሻችሁ ብለውን ሲያበቁ እውነት መስሎን ስንጫወት መስመሩን የፈለጉበት ቦታ ላይ አስምረው ወጥ ረገጣችሁ ይሉናል። ከመከተል ሌላ ምን አማራጭ አለን?›› አለ እዚያው ካጠገቧ የተሰየመ። ‹‹እኮ ማንን ነው የምትከተሉት?›› አዛውንቱ ግራ ግብት ብሏቸው ሲጠይቁ ወጣቶቹ በአንድ ድምፅ፣ ‹‹መስመሩን ነዋ!›› ብለው አሽካኩ። ወይ መስመሩና አሰማመሩ!

ወይዘሮዋ፣ ‹‹ሌላው ቢቀር እኚህን አዛውንት አታከብሩም? ይወልዷችኋል እኮ?›› እያለች አልለቅ አለች። ጎልማሳው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ሰው እኮ በዘመኑ ያሉትን መሪዎቹን፣ አስተዳዳሪዎቹን፣ ጎረቤቶቹን፣ እናቱንና አባቱን እያየ አድጎ ነው ባህሪው የሚገነባው። እነዚህ ልጆች እኮ ‘ከላይ የሚወርደውን ሐሳብ የሚቀበል እስከሆነ ድረስ አራተኛ ክፍልም ይሁን’ እየተባለ ዕውቀትና አዋቂ ሲዋረድ እያዩ አድገው፣ አገርን በክብርና በነፃነት ያቆዩዋት አባቶች በጡረታ ገንዘብ የቤት ኪራይ እየከፈሉና በኑሮ ውድነት እየተጠበሱ፣ በፖለቲካና በአስተሳሰብ ልዩነት እርስ በርስ ተናንቀው ያስተናነቁን ሰዎች ሐውልት ሲቆምላቸው እያዩ አድገው ታላቅን ማክበር ብሎ ነገር ከየት ያመጡታል?” ብሎ ታክሲዋን በድንጋጤ ፀጥ ረጭ አደረጋት። አሁን እስኪ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት በሕግ በፀናባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንዲህ ሲባል እንዲህ ክው ማለት ነውር አይደለም? ነው እንጂ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹እህህህ…›› ብሎ አንዱ ከመጨረሻ ወንበር በረዥሙ ተነፈሰ። ‹‹ምነው? ታፍነህ ነበር እንዴ?›› አሉት አጠገቡ የተሰየሙት። ‹‹የለም በነፃ መኖር አምሮኝ ነው…›› ብሎ መለሰ። ‹‹ሲያምርህ ይቅር እንዳንልህ አንተም እንደ እኛ ብዙ አምሮህ የቀረ ነገር ስለሚኖር ሌላ ዕጦት አንመኝልህም…›› አለችው ቆንጂት። ‹‹ደግሞ በነፃ መኖር ያማረው ማን በነፃ ሲኖር አይቶ ነው? እንኳን በሰው በአህያም አልተቻለ…›› ጎልማሳው ገባበት። ‹‹አህያ? የምን አህያ?›› ጠየቀች ወይዘሮዋ። ‹‹አልሰማችሁም ይህችን ጆክ። ሰውዬው በቃ ኑሮ ከበደውና የእኔ ቢቀር አህያዬን በነፃ ማኖር አለብኝ ብሎ ቆርጦ ተነሳ። ከዚያ ቀስ እያለ የዕለት ምግቧን ሲቀንስ፣ ቀስ እያለ ሲቀንስ… ሲቀንስ… ሲቀንስ… መጨረሻ ላይ አህያው ፍግም አለች። ምን ቢል ጥሩ ነው? ‘ወይኔ በነፃ ላኖራት ትንሽ ሲቀረኝ አህያዬ ሞተች!’ ጉድ እኮ ነው…›› ሲል ተሳፋሪዎች ተሳሳቁ። ‹‹እህም! ቀልድ፣ እንኳን በነፃ ተከፍሎስ መኖር ተቻለ እንዴ ዘንድሮ?›› ብላ ወይዘሮዋ ነገር ስትጀምር፣ ‹‹ዋጋው ዋጋ ስላጣ እኮ ነው እኔም በነፃ መኖር ያማረኝ…›› ብሎ ያ ቀልደኛ ወጣት ጣልቃ ገባባት። ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ ወያላው ሲያወርደን የነፃና የዋጋ ነገር ከየልቦናችን ጋር እያፋጠጠን አቅጣጫ አሳተን፡፡ ስንቶች ይሆኑ አቅጣጫ ስተው ጉድ የሆኑት፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት