Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ወንድማማቹን  ሕዝብ ለመለያየት የሚካሄደውን እኩይ ተግባር በኅብረት ልንዋጋው ይገባል›› የየሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ፣ የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት የድጋፍና ልማት ማኅበር ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት ድጋፍና ልማት ማኅበር ከተቋቋመ ውሎ አድሯል፡፡ ማኅበሩ ያቀፋቸውን አባላት በልማት እንዲሳተፍ በማመቻቸት ረገድ ፍሬያማ ውጤት እያስገኘ መጥቷል፡፡ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ ሲሆኑ በወቅታዊ ሁኔታና በማኅበሩ እንቅስቃሴ ላይ ከታደሰ ገብረማርያም ጋር ያካሄዱትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት በትግራይ ክልል ለጥሞና ጊዜ ሲባል ሠራዊቱ የተቆጣጠራቸውን ሥፍራዎች ለቅቆ እንዲወጣ ያሳለፈውን ውሳኔ ማኅበሩ እንዴት ያየዋል?

የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፡- ወደ ሕግ የማስከበሩ እንቅስቃሴ ከመግባቴ በፊት ስለ ቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝሰዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ወይም የቀድሞው የመከላከያ ሠራዊት ምንነት በአጭሩ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ የኢሕዲሪ ሠራዊት ከምሥራቅ እስከ ሰሜን ድረስ በርካታ የጦር ሜዳ ውሎች አሉት፡፡ በእነዚህም የጦር ሜዳ ውሎዎች ውስጥ ያካበታቸው ልምዶችና የቀሰማቸው ወታደራዊ ማንነቶች ያሉት ስብስብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) የተካሄደውንም ሕግ የማስከበር ሥርዓትና የተወሰደውንም ዕርምጃ ከዚህ አንፃር ነው የምንመለከተው፡፡ በዚህም መሠረት በወታደራዊ ምልከታ ስናየው ኢፌዴሪ በእንዲህ ዓይነቱ ትልቅ አገራዊ የሆነ ግዳጅ ላይ የወሰደው ዕርምጃ በበቂ ሁኔታ አዋጭ የሆኑ መንገዶችን አጥንቶ ያሳለፈው ውሳኔ እንደሆነ ይታየናል፡፡ የቀድሞ የኢሕዲሪ ሠራዊት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ባካሄዳቸው ትንቅንቆች  ላይ ያየናቸውንና ያካበትናቸው ልምዶች አሉ፡፡ እነዚህም ልምዶች የቀድሞው ሠራዊት 17 ዓመት ሙሉ ውጊያውን ሲያካሂድ ፋታ ወስዶ ራሱንና የዲሞክራሲ መስመርን ያዳመጠበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ትንቅንቁ የተካሄደው እስከ መጨረሻዋ ድረስ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ግን ከቀድሞውና እኛ ከነበርንበት የውጊያ ውሎ ትምህርት የወሰደ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ዝም ብሎና ዓይንን ጨፍኖ የነበረውን ነገር መቀጠል መፍትሔ አያመጣም፡፡ ዛሬ ጊዜ ፖለቲካውና የጊዜው የዲፕሎማሲ ሁኔታ ተለውጧል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የዓለም ዲፕሎማሲ  በአገሪቱ ላይ ጫና አሳድሯል፡፡ ይህን ሁሉ ተቋቁሞ፣ መለስ ብሎ  ራስን ገምግሞ፣ አይቶና ፈትሾ አዋጭ የሆነውን መንገድ መውሰድ ብልህነት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱንና ብልሃት የተሞላበትን መንገድ ቀይሶ ካልተሠራ በስተቀር እኛ በነበርንበት ጊዜ የነበረውን የውጊያ ጠባይ ዓይነት መከሰቱ አይቀሬ ነው፡፡ ሌላው ቲፒኤልኤፍ ያካሄደው የረዥም ዓመት ንቅናቄ በአንድ ትውልድ ሥነ ልቦና ውስጥ ምሽግ ለማበጀት አስችሎታል፡፡ ይህን በሥነ ልቦና የተጎዳውን ትውልድ ከዚህ ሐሳብ ለማውጣት ብልህነትና ጥንቃቄ የተሞላበት ሰፊ ሥራና እንቅስቃሴ ይጠይቃል፡፡ ማኅበረሰቡንም ከዚህ ሥነ ልቦና መታደግ ያስፈልጋል፡፡ ለመታደግ ደግሞ ጦርነት ብቻውን መፍትሔ አያመጣም፡፡ በተለያየ መልኩ የመፍትሔ ሐሳቦችን አመንጭቶና ቃኝቶ ትውልዱን ለመታደግ ጥረት መደረግ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በቀድሞው ኢሕዲሪና በአሁኑ ኢፌዲሪ በተለያዩ ዓውደ ግንባሮች የተካሄዱት ውጊያዎች የሚያመሳስላቸውንና የሚያለያያቸውን እንቅስቃሴዎች እንዴት ይገነዘቡታል?

የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፡- እኔ በነበርኩበት ወይም በኢሕዲሪና በአሁኑ የኢፌዲሪ  ጊዜ የተካሄዱት የውጊያ ትንቅንቆች በወንድማማቾች ወይም በአንድ አገር ልጆች መካከል የተካሄዱ መሆናቸው አንድ ወይም ተመሳሳይ ያደርጋቸዋል፡፡ ልዩነታቸው ግን እኛ የነበርንበት ጦርነት ርዕዮተ ዓለምን (አይዲኦሎጂ) የተንተራሰ ሲሆን፣ የአሁኑ ደግሞ ሥልጣን ላይ መቆናጠጥን ያለመ መርሕ ነው፡፡ አገሪቷን እኔ ካልመራሁ አይሆንም የሚሉ ስሜቶች ሲደባለቁባት ይስተዋላል፡፡ በተረፈ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በጥሩና አስተማማኝ በሆነ ቁመና ላይ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ለዚህም እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ወታደራዊ መሣሪያዎችን ታጥቋል፡፡ በመሣሪያም ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቡም የላቀ፣ የመጠቀና የዘመነ ነው፡፡ ሌላው የሚያመሳስለን ነገር ቢኖር በእኛ ጊዜ ወደፊት በተንቀሳቀስን ቁጥር ከፊት ለፊታችን፣ ከበስተኋላችንና ከግራና ቀኝ ጎናችን በርካታ የሆኑ ልዩ ልዩ ሰው ሠራሽ እንቅፋቶች ይደቀኑብን ነበር፡፡ በአሁኑ መከላከያ ሠራዊትም ላይ እንደዚህ ዓይነት እንቅፋቶች ይጋረጡበት ነበር፡፡ በቀድሞው ዘመን ከጦርነት ሰላም ይወለዳል ተብሎ ይታሰብ ነበር፡፡ አሁን ወይም ዛሬ ግን ሰላም የሚወለደው በጦርነት ሳይሆን በውይይት፣ በንግግርና በመቀራረብ  ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ባለበት ለረዥም ጊዜ በሚወሰድ ጦርነት ውስጥ ገብቶ መገዳደሉ ተፈላጊ አይደለም፡፡ ሌላው መታወቅ ያለበት ነገር ጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ የኖረ፣ የሚያመሳስለውና የሚያገናኘው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች ያሉት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ወንድማማቹን ሕዝብ ለመለየት የሚካሄደውን እኩይ ተግባር በኅብረት ሆነን ልንዋጋው ይገባል፡፡   

ከዚህ አኳያ የአሁኑ መንግሥት የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ተገቢና ትክክል ናቸው፡፡ ሕዝብንና አገርን የሚመራ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት አካል ቆም ብሎ የማሰቢያ ጊዜ መውሰድ፣ ለዛም ማኅበረሰብ አስቦ ወደ ራሱ ተመልሶ እንደገና ወደ ኢትዮጵያዊነትና ወደ አንድነቱ የሚመጣበትን ቦይ መክፈቱ ልክና ልክ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ለጥሞና ጊዜ ብሎ የወሰደው ዕርምጃ እንደ አንድ በጎ ነገር ቢታይም ዝም ብሎ መቀመጥ ነው ያለበት? ወይስ ምን ዓይነት ጥንቃቄዎች ማድረግ አለበት ይላሉ?

የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፡- እንግዲህ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ የጥሞና ወይም የማሰቢያ ጊዜ ሰጥቷል፡፡ በጁንታውም መካከል ችግሩን ቁጭ ብለው ለመፍታት የሚፈልጉ አካሎች ካሉ ዕድል መስጠቱም ጥሩና ማለፊያ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ያንን አካባቢ በዚህ መልኩ ለቆ ሲወጣ ለአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይም ለትግራይ ሕዝብ የማያስፈልጉ ወይም ጥሩ ያልሆኑና ለትውልዱም የማይጠቅሙ ክስተቶች እንዳያቆጠቁጡ መንግሥት ትልቅ የሆነ ወታደራዊ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይገባዋል፡፡ ቦታውን ነፃ አድርጎ ባዶውን እስከለቀቀ ድረስ በርካታ ያልታሰቡ ነገሮች ሊፈለፈሉ ይችላሉ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በደኅንነቱና በመከላከያ ደኅንነቱ፣ በሠራዊቱ እንደ መንግሥት ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ትልቅ የሆነና ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ማከናወን አለበት፡፡ ወደፊት የኢትዮጵያ ጉዳይ፣ የመንግሥት ጉዳይ የትኛውን መሥፈርት ተከትሎ ቢኬድ ነው ውጤት ሊያመጣ፣ ኢትዮጵያም ልታተርፍ የምትችለው የሚለውን አካሄድ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን መንግሥት የሰጠውን የጥሞና ጊዜ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለተግባራዊነቱ የኢትዮጵያ በተለይ የትግራይ ክልል ሕዝብ የየበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡ በተረፈ ሥልጣን አላፊና ቀሪ፣ የሰው ልጅ ሟች፣ ትውልድ፣ አገርና አንድነት ግን ቀጣይ እንደሆኑ መገንዘብ  ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ይጠበቃል?

የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፡- አገር እንድትኖር ከተፈለገ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ያለውን መንግሥት በተቻለው መጠን መርዳት፣ ማገዝና ከጎኑ መቆም አለበት፡፡ መንግሥትም ቆም ብሎና ኢትዮጵያን እንደገና አዋቅሮ ቀድሞ ወደነበረችበት ወደ አገራዊ ማንነቷ እንድትመለስ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ሁልጊዜ የሚጮሁትና የሚስተጋቡት ድምፆች ‹‹ይህች አገር ትፈርሳለች›› የሚል ነው፡፡ እነዚህ እኩይና ተስፋ አስቆራጭ ድምፆች በአየር ላይ ተንገዋለው እንዲቀሩ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብና ሌሎችም የፀጥታ አካላት አንድነትና ፍቅር መሥርተው የዕለት ተዕለት ሥራቸውን በትጋትና በንቃት ማከናወን፣ እንዲሁም እገሌ ከገሌ ሳይባል ሁሉም ሰው ለሰላምና ለነፃነት ዘብ መቆም ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ መልኩ ከተንቀሳቀስን ውጤት ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ የአገር ሉዓላዊነትን በማስከበር ረገድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ምን ያህል ዝግጁ ነው?

የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፡- የቀድሞ ኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና ልማት ማኅበር በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የቀድሞ ሠራዊት አባለትን ያቀፈ፣ እንዲሁም አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ከ280 በላይ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እንዳሉት መታወቅ ይኖርበታል፡፡ አባላቱም ለስድስተኛ ጊዜ በተከናወነው ምርጫ ላይ በየአቅራቢያቸው በሚገኙት ምርጫ ጣቢያዎች በታዛቢነትና አካባቢያቸውን በመጠበቅ የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ መንግሥትንና የኢትዮጵያን ሕዝብ አቅም በፈቀደ መጠን ለማገልገል ዝግጁ የመሆናችንን ያህል ደግሞ የምንናገረውን የሚያዳምጠንና ለጥያቄያችን መልስ የሚሰጠን አካል እንዲኖረንም እንፈልጋለን፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት በሚያስፈልገው ነገር ወይም በዚህ ቦታ ላይ ታስፈልጉኛላችሁ ብሎ ቢጠራን በተፈለግንበት ቦታ ሁሉ አለምንም ማወላወል ለመሳተፍ ምንጊዜም በተጠንቀቅ ላይ ሆነን እንገኛለን፡፡ ይህን ጉዳይም በተደጋጋሚ ጊዜ ተናግረናል፡፡ አሁንም ለተግባራዊነቱን የመንግሥትን መልስ በመጠባበቅ ላይ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ለመከላከያ ሠራዊት ያለውን ድጋፍ በምን መልኩ ነው የሚገልጸው?

የሃምሳ አለቃ ማኅበራችን ለመከላከያ ሠራዊት ያለውን ድጋፍ ለመግለጽ የሚያስችልና በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑ የተለያዩ ሁለት ዝግጅቶችን አቅዶ ዕውን ለማድረግ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴን በማከናወን ላይ ነው፡፡ ዝግጅቶቹም የሚከናወኑት በመስቀል አደባባይና ትግላችን ሐውልት በቆመበት ሥፍራ በሚገኘው የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ነው፡፡ አደባባዩና ፓርኩ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አሻራ ማለትም የምድር ጦር፣ አየር ወለድ፣ ባህርና አየር ኃይሎች አሻራ ያረፈባቸው ናቸው፡፡ በተለይ አደባባዩ ደመራ ለኩሰን፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ፈጽመን፣ መሪዎቻችን ለስብሰባ ጠርተውን ያሉንን አዳምጠን የተመለስንበት ብቻ ሳይሆን ወታደራዊ ሥልጠና ጨርሰን የአገር ዳር ድንበር ለማስከበር ወደ ግዳጅ ከመሰማራታችን በፊት በሥልጠና የቀሰምነውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በትርዒት መልክ ያቀረብንበት፣ ለአገር ሉዓላዊነት መከበር ቃል ኪዳን እንገባበት የነበረ ነው፡፡ የአምባገነኑን ዚያድ ባሬ ወራሪ ጦር ከደመሰስን በኋላ ከሕዝቡ ጋር ሆነን ‹‹ጉሮ ወሸባዬ!›› የጨፈርንበትና ድል የተቋደስንበትም ጭምር መሆኑን መረሳት የለበትም፡፡ በዚህም የተነሳ በዚህ አደባባይ ኢትዮጵያ ቀን በጎደለባት ጊዜ ከጎኗ የቆሙላት የቁርጥ ቀን ልጆቿ ዛሬም አለንልሽ የሚል ድምፅ ለማሰማት የሚያስችል ኢቨንት በቅርቡ ለማካሄድ አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት ተጠናቅቋል፡፡ ‹‹እኛም ትውስታ አለን መስቀል አደባባይ፣ እንዲህ ታሪክ ቆሞ ትንሳዔውን ስናይ›› በሚል መሪ ቃል ለሚካሄደው ኤቨንት (ሁነት) ዕውን መሆን የሚረዳ ፕሮጀክት ፕሮፖዛል አዘጋጅተን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አቅርበናል፡፡ ዝግጅቱም እየተከናወነ ያለውና ኢቨንቱም የሚካሄደው ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ነው፡፡ ኢቨንቱ ለአገር ህልውና ትልቅ ግብዓት አለው ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ልታካሂዱት ያሰባችሁት ዝግጅት ከዚህ የተለየ ነው?

የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፡- በዚሁ ፓርክ ላይ የሚከናወነው ዝግጅት ከመስቀል አደባባዩ እምብዛም አይለይም፡፡ ዝግጅቱ ሕግን በማስከበር እንቅስቃሴ ላይ የአካልና የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ያለንን ልባዊ ድጋፍ ለመግለጽ ነው፡፡ በኋላ ደጀንነትና ከፍ ሲልም ከጎኑ ተሰልፈን ለአገር ዳር ድንበር መከበር ተገቢውን መስዋዕትነት ለመክፈል ከመንግሥት ትዕዛዝ ብቻ በመጠባበቅ ላይ መሆናችን በድጋሚ የምንገልጽበት ዝግጅት ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህም በቂ ወታደራዊ ልምድና ዕውቀት ያለን ለመሆናችን ምስክር አያሻውም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ በባለቤትነት ለመያዝና ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ተቋማት ለመገንባት ሐሳብ አላችሁ ይባላል፡፡ በዚህ ላይ የሚሰጡት ማብራሪያ አለ?

የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፡- በፓርኩ ውስጥ ወደ 600 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ፕሮጀክት ለማከናወን አቅደን እየሠራን ነው፡፡ በዚህም ፕሮጀክት ከሚከናወኑት ተግባራት መካከል ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት፣ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ካፌና ሬስቶራንት የሚገኙበት ሲሆን የትግላችን ሐውልትም ዕድሳት ይደረግለታል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ጉዳዩ በይበልጥ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር ተቀራርበን እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ገንዘቡን ከየት ነው የምታገኙት?

የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፡- ፋይናንስን በተመለከተ ወደ ሦስትና አራት የሚጠጉ አማራጮችን በፕሮጀክት ፕሮፖዛል ውስጥ አካተናል፡፡ የመጀመርያው አማራጭ በአባልነት ያቀፍነው የቀድሞ ሠራዊት ነው፡፡ ይህ ማለት አንድ ሚሊዮን አባላቱ እያንዳንዳቸው ሁለት ብር ቢያዋጡ፣ ከዛም ከፍ ሲል አምስት ወይም አሥር ብር በነፍስ ወከፍ ቢሰጡ የሚገኘውን ገንዘብ ማስላት ይቻላል፡፡ ከዚህም ሌላ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች ድጋፍና በጎ ህሊና ያላቸው በጎ አድራጊዎች ዕገዛ አይለየንም የሚል እምነት አለን፡፡ መንግሥትም የበኩሉን ዕርዳታ ጣል እንደሚያደርግልን እንተማመናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለቤት ኪራይና ለሠራተኞች ደመወዝ ወርኃዊ ወጪያችሁ ምን ያህል ነው? የገንዘቡስ ምንጫችሁ ምንድነው?

የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፡- የቤት ኪራይ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ነው የምንከፍለው የአንድ ወር 20,000 ብር ሲሆን የሦስት ወራቱ 60,000 ብር ነው፡፡ ደመወዝ ተከፋይ የሆኑ ሠራተኞችን ጨምሮ በየሦስት ወሩ ወደ 100,000 ብር የሚጠጋ ወጪ እናደርጋለን፡፡ እነዚህ ገንዘቦች በመንገዱ እንደሚወራው ከአባላት በየወሩ ተዋጥቶ የሚከፈል አይደለም፡፡ አንድ አባል የሚከፍለው አንድ ጊዜ ሲመዘገብና መታወቂያ ሲወሰድ ብቻ ነው፡፡ የገንዘቡም መጠን 50 ብር ነው፡፡ በተረፈ አንዴ ተመዝግቦ መታወቂያ ከወሰደ በየወሩ አይከፍልም፡፡ እንዲከፍል የሚያስገድድም ሥርዓትም ሆነ ሕግ በማኅበሩ መተዳደሪያ ውስጥ አልሰፈረም፡፡ ለቤት ኪራይና ለሠራተኛ የምንከፍለውን ገንዘብ የምናገኘው በአብዛኛው በልመና ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ የማኅበሩ ደጋፊዎችና አንዳንድ የቀድሞ ሠራዊት መኰንኖች ይተባበሩናል፡፡ ጫን ያለ ነገር ሲመጣ ደግሞ ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ኪሱን የሚፈትሽበት ጊዜ ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- መታወቂያው ለሠራዊቱ ያበረከተው ፋይዳ አለው?

የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፡- አዎ ጠቅሞታል፡፡ ሥራ ሲቀጠር የቀድሞ ሠራዊት አባልና ልምድም ያለው ለመሆኑ አሳይቶበታል፡፡ የሕክምና አገልግሎት ቢያንስ በቅድሚያ እንዲያገኝ አግዞታል፡፡

ሪፖርተር፡- ቋሚ የሆነ የገቢ ምንጭ የላችሁም?

የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፡- ቋሚ የሆነ የገቢ ምንጭ እስካሁን የለንም፡፡ ለመፍጠር ግን እየተፍጨረጨርን ነው፡፡ እስካሁንም ባደረግነው መፍጨርጨር ‹‹ፈጥኖ ደራሽ የጥበቃና የፅዳት አገልግሎት ኤጀንሲ›› አቋቁመናል፡፡ ከዚህም ሌላ ‹‹ራስ አድማስ›› በሚል መጠሪያ የሚታወቅ የማይክሮ ፋይናንስ (የገንዘብና ብድር) አክሲዮን ማኅበር ለመመሥረት የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርጸን ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በማከናወን ላይ ነን፡፡ በተረፈ ኤጀንሲው በቅርብ ቀን የተቋቋመ እንደመሆኑ መጠን ለራሱ ተርፎ ማኅበሩን በሚደጉምበት ደረጃ ገና አልደረሰም፡፡ ኤጀንሲው በሚገባ ተጠናክሮ ሲንቀሳቀስና አክሲዮን ማኅበሩ ሥራ ላይ ሲውል የፋይናንስ ችግራችን ሙሉ ለሙሉ እንኳን ባይሆን በመጠኑም ቢሆን ይቀላል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከመንግሥትና ከሕዝቡ ምን እንዲደረግላችሁ ትሻላችሁ?

የሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፡- መንግሥት ለቢሮ የምንገለገልበት ሁለት ክፍሎች ያሉት ቤት ቢሰጠን ከኪራይ ነጻ እንሆናለን፡፡ ለኪራይ የምናወጣውን ለሌላ ልማት ላይ እናውላለን ብለን እናስባለን፡፡ ሕዝቡ ደግሞ በየመንገዱና በየአደባባዩ በልመና ላይ በነበርንበት ወቅት ከመቀነቱ እየፈታ በመርዳት ከጎናችን እንደቆመ ሁሉ፣ ዛሬ ደግሞ ተወተርትረን አሁን ለደረስንበት ደረጃ የዕርዳታ እጁን እንዲዘረጋልን አጥበቀን እንማጸናለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...