Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​​​​​​​ወወክማ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የሚያሠራውን ሕንፃ እንዲያቆም  ጠየቀ

​​​​​​​ወወክማ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የሚያሠራውን ሕንፃ እንዲያቆም  ጠየቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ)፣ በዘውዳዊ ሥርዓት በዋና መሥሪያ ቤትነት ይገለገልበት በነበረው ሕንፃ ፊት ለፊት ባለው ባዶ ቦታ ላይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ኮሚሽን አዲስ ሕንፃ ለመገንባት የሚያከናውነውን እንቅስቃሴ በመቃወም ግንባታው እንዲቋረጥ ጠየቀ፡፡

ኮሚሽኑ ደግሞ ሕንፃውን የሚያስገነባው የኅብረተሰቡን የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ጥያቄ ለመመለስ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የወወክማ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳግማዊ ሰላምሳ እንደገለጹት፣ ጥያቄውንም ሊያነሳ የቻለው ኮሚሽኑ እንዲያስተዳድረው የተረከበውን ዋና መሥሪያ ቤት፣ የትምህርትና ሥልጠና ማዕከል ሕንፃዎች፣ እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የያዘውን የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ለወወክማ እንዲመለስለት የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ የውሳኔ ሐሳቡም ያመነጨው በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተወካይ የተመራው ኮሚቴ ነው፡፡

ከሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ከወወክማና ወሴክማ የተውጣጡ አባላትን ያካተተው ኮሚቴው፣ ይህ ዓይነቱን የውሳኔ ሐሳብ ሊያመነጭ የቻለው ሰነዶችን በሚገባ ከመረመረና በዝርዝር የተጠቀሱት ንብረቶች የወወክማ ንብረት መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በውሳኔውም ሐሳብ ላይ የመጨረሻ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዳቀረቡላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ትዕዛዝ ሳያሳርፉበት ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩና ከዛን ጊዜ ጀምሮም ጉዳዩ በእንጥልጥል እንደቆየ ከዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ይህም ቢሆን ብሔራዊ ወወክማ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ጉዳዩ ዕልባት እንዲያገኝ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለኮሚሽኑና ለቢሮው በተደጋጋሚ ጊዜ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡ ለቀረበውም ጥያቄ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት የስፖርት ኮሚሽኑ ሕንፃ ሊገነባ መሆኑን በደብዳቤ እንዳሳወቀው፣ ወወክማም ደብዳቤው እንደደረሰው ግንባታው እንዲቆም ቢጠይቅም ከኮሚሽኑ ምላሽ እንዳላገኘ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

‹‹ይህም ሆኖ ግን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ለማነጋገር ወይም ለውይይት በሩን የከፈተ አካላት አለማግኘታችን መላውን የወወክማ አባላት፣ ወጣቶች፣ ደጋፊዎች፣ በውጭና በአገር ውስጥ የሚገኙ አጋር አካላትን ሥጋት ላይ ጥሏል፡፡ በመሆኑም ጥያቄያችን ቅቡል ሆኖ የውሳኔ ሐሳቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ቢያገኝ አገልግሎታችንን በማስፋፋትና ተረጋጋተንም በማከናወን ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት አለን፤›› ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ዳግማዊ ማብራሪያ የኢትዮጵያ ወወክማ ፆታ፣ ዘርና ሃይማኖትን ሳይለይ የወጣቶችን የልማት ራዕይና ግብ በጠንካራ መሠረት ላይ በመጣል በአዕምሮ የጎለበተ፣ በመንፈስ የጠነከረና በአካል የዳበረ ወጣት ለማፍራት ሁሉን አቀፍ እንቅስቃስ እያደረገ ነው፡፡ ይህንንም እንቅስቃሴ እያካሄደ ያለው በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔርና ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልሎች ሲሆን፣ ሥራውም የሚካሄደው በተጠቀሱት ክልሎች ውስጥ ባቋቋማቸው አሥር ቅርንጫፎች አማካይነት ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ነው፡፡

ወወክማ በአሁኑ ጊዜ ከ30,000 በላይ አባላትና በጎ ፈቃደኞች፣ እንዲሁም 80,000 የፕሮጀክት ተጠቃሚዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን አቅፎ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዝግጁነት፣ በስፖርት፣ በበጎ ፈቃደኝነት፣ በሕይወት ክህሎት፣ በሲቪክ ተሳትፎዎች በአመራርነት ብቃት ላይ ሁለገብ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወወክማ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1942 ዓ.ም. ሐሳቡ ተጠንስሶ በአዋጅ ቁጥር 4/1943 የተቋቋመ ሲሆን፣ በ14 ጠቅላይ ግዛቶች በሚገኙ 21 ከተሞች ውስጥ 25 ቅርንጫፎችን በመክፈት ሰፊ አገልግሎቶች ሲሰጥ እንደነበር፣ በደርግ ዘመነ መንግሥት ከነበረው የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ጋር አብሮ አይሄድም በሚል ከ1969 ዓ.ም. ጀምሮ ለ16 ዓመታት ያህል እንደተዘጋ፣ ሕንፃዎቹና ልዩ ልዩ ንብረቶቹም ለተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲወረስ ተደርጓል፡፡ ሆኖም በ1983 ዓ.ም. የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ወወክማ በ1984 ዓ.ም. እንደገና መልሶ መቋቋሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መሐሪ ሰለሞን ስለ ጉዳዩ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ኮሚሽኑ የሚያሠራው ሕንፃ ባለሰባት ፎቅ ሲሆን በውስጡም ልዩ ልዩ የቤት ውስጥ መጫወቻዎችና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚዘወተሩባቸው ክፍሎችን ያካተተ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ሕንፃው የሚገነባው በቀድሞው ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ፊት ለፊት ሳይሆን በሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት አጠገብ በመሆኑ ዋናውን ሕንፃ አይጋርደውም ብለዋል፡፡ ይህም እንደተጠበቀ ሆኖ ሕንፃው የሚገነባው በመንግሥት ፈቃድና ዕውቅና በማግኘት መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ብሔራዊ ወወክማ የሕንፃውን ግንባታ በተመለከተ ለኮሚሽኑ ላቀረበው ጥያቄ በደብዳቤ የታገዘ መልስ እንደተሰጠው ከአቶ መሐሪ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...