Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የሥጋት ደመናው ይገፈፍ!

ለኢትዮጵያ በዚህ ጊዜ የሚያስፈልጋት የመላ ሕዝቧ አንድነት ነው፡፡ ሕዝብ አንድነት ሲፈጥር ማንም አገሩን አይደፍርም፡፡ አንድነት ሲኖር የኢትዮጵያ ወጣቶች ጥራት ያለው ትምህርትና አስተማማኝ ገቢ ያለው ሥራ ያገኛሉ፡፡ ከሌብነት፣ ከሱስና ከአልባሌ ድርጊቶች ተወግደው ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ ተሟጋች ይሆናሉ፡፡ አገር ለማጥፋትና ለማተራመስሚያደቡ መሰሪዎች መሣሪያ አይሆኑም፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ እያንዳንዱ አገሩን የሚወድ ዜጋ ለአገራዊ አንድነት አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለአገራቸው ህልውና በፅናት መቆም የሚችሉት፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ከጎናቸው በቁርጠኝነት ሲቆሙ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዱ የሚፈልጉ ኃይሎችም የሚገቱት፣ ኢትዮጵያዊያን እንደ ጥንቶቹ አባቶቻቸውና እናቶቻቸው በአንድነት ሲቆሙ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንገት አስደፊው ድህነት ከመጠን በላይ ስላንገሸገሸው፣ ከዚህ በኋላ መሠረታዊ ፍላጎቶቹ ተሟልተው በክብር መኖር ይገባዋል፡፡ ሕዝብ የድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ ወሬ፣ ሐሜት፣ አሉባልታ፣ ጥላቻ፣ ራስ ወዳድነት፣ ራዕይ አልባነት፣ ግጭትና ትርምስ ለኢትዮጵያ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት አግኝታቸው ያመለጧት ወርቃማ ዕድሎች ያስቆጫሉ፡፡ መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር ሕዝብ የጠበቃቸው ቀርተው የማይፈልጋቸው ክፉ ነገሮች እየተጫኑበትና ልጆቹ እስር፣ ስደትና ሞት ዕጣ ፈንታቸው ነበር፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ታፍነው ኢትዮጵያዊያን ቁም ስቅላቸውን አይተዋል፡፡ ከዚያ አስመራሪ አዙሪት ውስጥ መውጣት የግድ መሆን አለበት፡፡ አገሪቱ ላይ ያንዣበበው የሥጋት ደመና መገፈፍ ይኖርበታል፡፡

የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖችም ራሳቸውን መግራት አለባቸው፡፡ የራሳቸውን ዓላማ ሲያቀነቅኑ ተቃራኒ ሐሳብን በጥላቻ ንግግር መመከት የለባቸውም፡፡ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጠበቃ ነን እየተባለ፣ ተቃራኒ ሐሳብ የሚያራምዱ ወገኖችን ማንነት፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ባህልና ሌሎች መለያዎችን ማብጠልጠል ተቀባይነት የለውም፡፡ የጥላቻ ንግግር ስሙ እንደሚገልጸው ለአገር ጥፋት እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ የጥላቻ ንግግርን እንደ መብት በመቁጠር ተቃራኒ በሚባሉ ወገኖች ላይ ዘመቻ መክፈት ሥልጣኔ አይደለም፡፡ ጠላትነት ከማበራከት ውጪ ለአገር ጥቅም የለውም፡፡ የሌሎችን ነፃነት እያከበሩ በሐሳብ የበላይነት መብለጥ የዴሞክራቶች መገለጫ ነው፡፡ የሐሳብ ልዕልና ያለው ለሌሎች ነፃነት ይጨነቃል፡፡ የሐሳብ ልዕልና ሲጠፋ ግን ጉልበተኝነት ይከተላል፡፡ ጉልበት ደግሞ የሕገወጦች መለያ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የምትሉ በሙሉ ለሐሳብ የበላይነት ታገሉ፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው የተሻለ ሐሳብ ይዞ ገበያ የሚወጣውን ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

መንግሥት ጥሩ ሲሠራ የሚመሠገነውን ያህል ሲያጠፋም መወቀስ አለበት፡፡ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት፣ የሕግ የበላይነት ማስከበር ሲሳነው ይወቀሳል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና የመሳሰሉት ሲመሠገኑ ወቀሳም ይጠብቃቸዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ውስጥ ልዩነትን የማክበር፣ የመተቻቸትና የመወቃቀስ ባህል ሊዳብር የሚችለው የሲቪክ ተቋማት ሲያብቡ ነው፡፡ የኅብረተሰቡ ንቃተ ኅሊና በሲቪክ ተቋማት አማካይነት ሲዳብር የንግግርና የውይይት ባህል ይጠናከራል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ልሂቃን ለሐሳብ ነፃነት ተግተው መሥራት አለባቸው፡፡ ሚዲያዎች ተጠናክረው የተለያዩ ሐሳቦችን ማንሸራሸር እንዲችሉ ነፃነታቸው ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ከጀብደኛና ተገቢ ካልሆኑ ድርጊቶች ወጥተው በሙያ ሥነ ምግባር ብቻ እንዲመሩ ማገዝ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ ፖለቲከኞች ከተለመደው የሴራ ፖለቲካ ወጥተው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉት፣ ልዩነትን ለማክበር የሚያስችል ሰብዕና ሲጎናፀፉ ነው፡፡ ከአሉባልታ፣ ከሐሜት፣ ከጥላቻና ከብሽሽቅ በመውጣት በሥልጣኔ ጎዳና ላይ መራመድ ያዋጣል፡፡ እስካሁን የተመጣበት መንገድ አትራፊ ሳይሆን አክሳሪ ስለነበር፣ ራስን ከዘመኑ ጋር እኩል ማራመድ ይጠቅማል፡፡ አገሪቱ ላይ የሚያንዣብበው የሥጋት ደመናም ይገፈፋል፡፡

አገራቸውንና ሕዝባቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን ከሴራ፣ ከተንኮል፣ ከጥላቻና ከቂም በቀል የፀዱ ናቸው፡፡ በገዛ ወገናቸው ላይ በደል አይፈጽሙም፡፡ እናት አገራቸውን የመከራ ቋት አያደርጉም፡፡ ለባዕዳን ፍርፋሪ ሲሉ የአገራቸውን ሚስጥር አሳልፈው አይሰጡም፡፡ አገራቸው የሰላም፣ የልማት፣ የደስታና የዴሞክራሲ አምባ ሆና ሕዝባቸው በነፃነት እንዲኖር መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡ በሕዝብ ደም እየነገዱ ሥልጣን፣ ክብርና ሀብት አያጋብሱም፡፡ በቅናትና በምቀኝነት ተነሳስተው ተፎካካሪያቸውን አያጠፉም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ያሉት ግን መታወቂያቸው መግደል፣ ማፈናቀል፣ መከፋፈል፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ማነሳሳት፣ መዝረፍ፣ አገርን መዳከምና የመሳሰሉት ዕኩይ ድርጊቶች ናቸው፡፡ 21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን አስተሳሰብ ይዘው ክፋት ይዘራሉ፡፡ አዲሱን ትውልድ ይመርዛሉ፡፡ የአገር ሰላም ያቃውሳሉ፡፡ በዕድገት ፈንታ ውድቀት ያጣድፋሉ፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ክብር ስለሌላቸው አንደበታቸው የሚተፋው መርዝ ነው፡፡ ከአገር አንድነት ይልቅ ስለመነጣጠል ይደሰኩራሉ፡፡ ስለተጠናከረች ኢትዮጵያ ሳይሆን ስለምትፈራርሰው ኢትዮጵያ ነጋ ጠባ ይሰብካሉ፡፡ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው ከዘመኑ ጋር ስለማይመጥን፣ የሚያሴሩት ሁሉ በግልጽ ይታወቃል፡፡ አገራችሁንና ሕዝባችሁን ከልብ የምትወዱ ኢትዮጵያዊያን ግን፣ በግልጽና በድፍረት ወጥታችሁ ዘመኑን እንደምትመጥኑ በተግባር አሳዩ፡፡ በአገራችሁ ላይ የሚያንዣብበውን የሥጋት ደመና ግፈፉ፡፡

በፌዴራልም ሆነ በክልል ብሔራዊ መንግሥታት የሚወሰዱ ማናቸውም ዕርምጃዎች፣ በመርህ ላይ የተመሠረቱና አብሮ የሚኖረውን ሕዝብ ፍላጎት ያማከሉ መሆን አለባቸው፡፡ መርህ በምክንያታዊነት መመራትን፣ ትክክለኛና ስህተትን መለየትን፣ ግልጽነትን፣ ሀቀኝነትን፣ ብስለትን፣ ፍትሐዊነትን፣ ሥነ ምግባርንና የመሳሰሉትን እሴቶች መላበስ ነው፡፡ መንግሥት አገር ሲያስተዳድር በተቻለ መጠን ውሳኔዎቹ በመርህ ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የሕዝብን ጤና፣ ሰላም፣ ደኅንነትና ህልውና የሚጎዱ ማናቸውንም ዓይነት ድርጊቶች የመከላከል ኃላፊነት አለበት፡፡ ሕዝብም መንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ማገዝ ሲኖርበት፣ ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን ማጋለጥ ይጠበቅበታል፡፡ ሕገወጥ ከሚባሉ ድርጊቶች መካከል ግጭት በመቀስቀስ የአገር ሰላም ማደፍረስ፣ ንብረት ማውደም፣ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ የአደንዛዥ ዕፆች ዝውውር፣ ግብር መሰወር፣ የአገር ሀብት መዝረፍ፣ የመሬት ወረራና ሌሎች ሕገወጥ ድርጊቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ የበላይነት እንዳይዝ መንግሥትና ሕዝብ በአንድነት መቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግሥት በተለመደው አዝጋሚ አፈጻጸሙ ድንገት እየባነነ ቁረጠው ፍለጠው ዓይነት ዘመቻ ውስጥ ሲገባ፣ ሕዝብ ደግሞ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በነበረበት እንዳይቀጥል መግታት ይኖርበታል፡፡ በተለይ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ምሁራንና ልሂቃን በዚህ በኩል ጠንከር ያለ አቋም መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግራና ቀኙን የማያማትሩ የመንግሥት መርህ አልባ ዕርምጃዎች የሚያስከትሉት ጦስ መዘዙ ለአገር ስለሚተርፍ፣ ያንዣበበውን የሥጋት ደመና መግፈፍ ያስፈልጋል፡፡

ከጥንት ጀምሮ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያዊያን በሕይወት መስዋዕትነት ጭምር አገር ጠብቀው አስተላልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ዞር ብለን ታሪካችንን በፅሞና ካየነው በሕዝብ መካከል መተሳሰብ፣ መከባበር፣ መተዛዘን፣ ያለውን ነገር መካፈል፣ ልዩነቶች መኖራቸው እስከማያስታውቅ ድረስ በጋብቻ ተሳስሮ መዋለድ፣ ረቂቅ የሆኑ የጋራ ሥነ ልቦናዎችና መስተጋብሮች፣ እንዲሁም የአገር ፍቅር ስሜት በመስረፃቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግረዋል፡፡ ይህንን ከመሰለ አስተዋይ፣ ጨዋና ኩሩ ሕዝብ ውስጥ የወጡ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ልሂቃንና በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች ለምን መስከን ያቅታቸዋል? ለምንስ ከሕዝባቸውና ከአገራቸው በፊት የራሳቸውን ጥቅም ያስቀድማሉ? ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉስ ለምን በንፁኃን ሕይወት ይቆምራሉ? ለምንስ ሕዝብና አገርን አንድ ጋት የማያራምድ ከንቱ ድርጊት ውስጥ ይገኛሉ? ከሐሜት፣ ከአሉባልታና ከክፋት ለመላቀቅ ለምን ይቸግራቸዋል?  ለአገራቸው በቅንነትና በትጋት የሚያገለግሉ ወገኖችን ለምን ያደናቅፋሉ?  በስክነት መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያን የግጭት የስበት ማዕከል ማድረግ አያዋጣም፡፡ የሥጋት ደመናው በፍጥነት ይገፈፍ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...