Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊካናዳ  ለሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ ከ99 ሚሊዮን ብር በላይ ረዳች

ካናዳ  ለሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ ከ99 ሚሊዮን ብር በላይ ረዳች

ቀን:

የሆስፒታል አገልግሎቶችን ለማሻሻል አዲስ ትልም በሥራ ላይ ውሏል

የካናዳ መንግሥት በኢትዮጵያ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለከፋ ጉዳት ለተዳረጉና ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ 37,250 ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ የሚያስችል 99.5 ሚሊዮን ብር ረዳች፡፡

ገንዘቡን በመንግሥታቸው ስም ለዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ቢሮ ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ያስረከቡት፣ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ሚስተር ስቲፈን ጆቢን ሲሆኑ፣ የተረከቡት ደግሞ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ሚስተር አደለ ከሆዶር ናቸው፡፡ አምባሳደሩ በዚሁ ጊዜ ዩኒሴፍ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ክፉኛ የተጎዱ ሕፃናትን ለመታደግ የሚያካሂደውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዩኒሴፍ ተወካይ ሚስተር አደለ ከሆዶር የተሰጠው ድጋፍ በእርስ በርስ ግጭቶችና በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ ለከፋ ችግር የተጋለጡ ሕፃናትን ሕይወት በማትረፍ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የገለጹት፡፡

የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ቢሮ ዘንድሮ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የበረሃ አንበጣ መንጋና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያሳደሩት አሉታዊ ተፅዕኖዎች፣ ግጭቶችና መፈናቅሎች ባስከተሉት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ለከፋ ጉዳት ለተዳረጉ 518,400 ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ የሚያስችል ግብ መጣሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተዘጋጀው ግብ ውስጥ ከተካተቱት ሕፃናት መካከል 500,000 ያህሉ ኢትዮጵያውያን የቀሩት 18,400 ደግሞ ስደተኛ ሕፃናት ናቸው፡፡ ዩኒሴፍ ዓምና በተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ሳቢ ክፉኛ ለተጎዱ 438,700 ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ማቅረቡንም ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል፣ በሆስፒታሎች የሚሰጡትን አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል፣ ተገልጋይ ተኮር አገልግሎቶችን ለማጠናከር፣ የሆስፒታል ሠራተኞችና ባለሙያዎች የሚያበረክቷቸው አገልግሎቶች አመቺና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ የእኔን ያገባኛል (አይ ኬር) ኢኒሼቲቭ ሥራ ላይ ማዋል ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የእኔን ያገባኛል ትልም (ኢኒሼቲቭ) እንቅስቃሴ በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሰኔ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በተጀመረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ሚኒስትሯ እንዳመለከቱት፣ የሆስፒታሎችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በርካታ የሪፎርም ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ኢኒሼቲቩ ግን ለየት የሚያደርገው በማሻሻል ሥራ ላይ ማኅበረሰቡና ሌሎቹም ባለድርሻ አካላት ከሆስፒታሉ ሠራተኞችና ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅተው መንቀሳቀሳቸው ነው፡፡

ትልሙ የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታልን ጨምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚገኙና በተመረጡ 24 ሆስፒታሎች በዚሁ ዕለት መጀመሩን ሚኒስትሯ አመልክተው፣ ተጠናክሮ መቀጠልም እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታምሩ አሰፋ (ዶ/ር)፣ ሆስፒታሉ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚገጥሙትን ችግሮች በጥልቀት በመተንተን፣ እንዲሁም ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑ የሥራ አፈጻጸሞችን በመገምገም ጠንካራና ደካማ ጎን ለመለየት እንደቻለ ነው የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...