Monday, May 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለአገር ሰላም መስዋዕትነት መከፈል አለበት!

ለሰላም ሲባል የሚከፈል ዋጋ መኖሩ አጠያያቂ አይደለም፡፡ የሚከፈለው ዋጋ ግን የሚታሰበውን ሰላም ማስፈን ይኖርበታል፡፡ ከምንም ነገር በላይ የሆነው የሕዝብ ደኅንነትና የአገር ህልውና ጉዳይ ማዕከላዊ ነጥብ ሰላም በመሆኑ፣ የማንኛውም ውሳኔ መነሻና መድረሻ በዚህ ላይ ማጠንጠን ይጠበቅበታል፡፡ ከሕዝብና ከአገር በላይ የሚቀድም ስለሌለ፣ ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ተቆጥረው በማያልቁ ጦርነቶችና ግጭቶች የደመቀ ስለሆነ፣ አሁን ግን ያለፈው እንዳለፈ ተቆጥሮ አውዳሚ ከሆኑ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ውስጥ መውጣት የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የግዛት አንድነቷና ሉዓላዊነቷ ተከብሮ የውጭ ጣልቃ ገብነትን መቋቋም የምትችለው፣ ሰላሟን አስተማማኝና ዘለቄታዊ በማድረግ ለልማት በጋራ ለመነሳት ቁርጠኝነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ የአገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ በጋራ መምከር፣ መከራከርና ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል ውሳኔ ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አገርንና ሕዝብን ረስቶ ሥልጣን ላይ ብቻ ማተኮር፣ ግላዊና ቡድናዊ ፍላጎትን ከአገር ማስበለጥና የኢትዮጵያዊያንን ዘመን ተሸጋሪ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶችን ዋጋ አልባ ማድረግ የሚጠቅመው ታሪካዊ ጠላቶችን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አይረቤ አመለካከትና ፍላጎት የሚያስገኘው ሰላም የራቃትና ደካማ ኢትዮጵያን ስለሆነ፣ ለአገር እናስባለን የሚሉ ወገኖች በሙሉ ከኢትዮጵያ ሰላም የሚቀድም ምንም ነገር የለም በማለት በጋራ መነሳት አለባቸው፡፡

አገር ሰላም ውላ እንድታድር ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተናጠልና የወል ኃላፊነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለአስተዳደራዊ ጉዳይ ሲባል ውስጣዊ ነፃነትንና ራስ ገዝነትን የተጎናፀፉ ቢሆንም፣ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ደኅንነትና መብት መከበር በኃላፊነት መንፈስ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሁሉም ሥፍራ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት ማየት፣ አንዱን ከሌላው አለማበላለጥ፣ በሥራም ሆነ በተለያዩ ግንኙነቶች ሊገኙ የሚገቡ ጥቅሞች ከአድልኦ የፀዱ እንዲሆኑ መትጋት፣ ማንነትን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ መጠቃቀሞችና መጠቃቃቶች እንዳይኖሩ መከላከልና የመሳሰሉት በኃላፊነት ሲከናወኑ አገር ሰላም ውላ ታድራለች፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አንዱን ባለቤት ሌላውን መጤ በማድረግ ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽሩ ከፋፋይ ድርጊቶች መወገድ አለባቸው፡፡ የአንድን አገር ሕዝብ በማንነትና በእምነት በመከፋፈል አገር አልባ ለማድረግ የተሠሩ ደባዎች በሙሉ መክሸፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በአራቱም ማዕዘናት በፈለጉት ሥፍራ የመንቀሳቀስ፣ የመኖር፣ የመሥራት፣ ንብረት የማፍራትና የመሳሰሉት መብቶቻቸውን በተግባር ማረጋገጥ የግድ መሆን አለበት፡፡ ሕዝብ በአገሩ ደስተኛ የሚሆነውና ሰላም በአስተማማኝነት የሚሰፍነው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ከአሁን በኋላ ምንም ዓይነት ግጭት ወይም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ማድረግ የሚቻለው፣ በዘርፈ ብዙ የአገሪቱ ዋነኛ ጉዳዮች ላይ በእኩልነት ለመነጋገር ፈቃደኝነት ሲኖር ነው፡፡ ይህንን ፈቃደኝነት ለማምጣት ግን እጅግ በጣም አሰልቺና እልህ አስጨራሽ ጥረቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ለይስሙላ ያህል የሚደረጉ ምክክሮች ላይ ብቻ ከማተኮርና ውጤት እያጡ ተስፋ ከመቁረጥ፣ ለዘለቄታው የሚያዋጡ ነገር ግን ከመጠን በላይ ትዕግሥትና አስተዋይነትን ለሚጠይቁ ዓበይት ጉዳዮች ጊዜን፣ ዕውቀትን፣ ጉልበትንና ሀብትን ለማስተባበር መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በማይረቡ ጉዳዮች ምክንያት ጥልቅ የሆነ መከፋፈል በተፈጠረባት አገር ውስጥ ተባብሮ መሥራት ከተቻለ ተዓምር መፍጠር አያቅትም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘመን ተሸጋሪ የሆኑና በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ ውጤታማ የሆኑ የግጭት አፈታትና የሽምግልና ሥርዓቶች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህን የሚያኮሩና ለሌላ የሚተርፉ ማኅበራዊ እሴቶችና ትሩፋቶች ይዞ አገርን ችግር ውስጥ መጣል ያብቃ፡፡ ከራሳቸውና ከቡድናቸው ፍላጎት በላይ ለምንም ነገር ደንታ ከሌላቸው በስተቀር፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአገሩ ሰላም የሚያስቀድመው ምንም ነገር የለውም፡፡

ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን በአግባቡ እያስተናገዱ በአንድነት አገራቸውን መገንባት ይችላሉ፡፡ በታሪክ ጠባሳዎች ላይ ብቻ በማተኮር እርስ በርስ ለመተናነቅ ከማድባት ይልቅ፣ ያለፉትን ስህተቶች በጋራ እያረሙና እያስተካከሉ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት አብረው መኖር አይሳናቸውም፡፡ ኢትዮጵያዊያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋና በሌሎች ጉዳዮች የየራሳቸው የሆኑ መገለጫዎች ቢኖሩዋቸውም፣ ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ኅብረ ብሔራዊት አገር ለመገንባት አያቅታቸውም፡፡ ለዘመናት የብሔርና የእምነት ልዩነት ሳይገድባቸው ተጋብተውና ተዋልደው ታላላቅ ማኅበራዊ እሴቶችን ያፈሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ለጠላት በተገዙ የግጭት ነጋዴዎች መበለጥ የለባቸውም፡፡ በስሜት የሚነዱ አፍለኞችን በማነሳሳት ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ ለማጋደልና አገር ለማፍረስ የሚፍጨረጨሩ ቢኖሩም፣ አርቀው በሚያስቡና በሰከኑ ኢትዮጵያዊያን ጥረት ዓላማቸው እየከሸፈ እዚህ ተደርሷል፡፡ ነገር ግን አሁን ከፍተኛ የሆነ ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በእኩልነት፣ በነፃነትና በፍትሐዊነት የምታስተናግዳቸው አገር እንድትገነባ አርዓያነት ያለው ተግባር ሊኖር ይገባል፡፡ የአንድ ወገን የበላይነት የተጫጫናቸውን አጓጉልና ኋላቀር ትርክቶች በማስወገድ፣ የወደፊቱን የጋራ ብሩህ ሕይወት አመላካች ጉዳዮች ላይ መተኮር አለበት፡፡ በታሪክ አንፀባራቂ የሚባሉ ክንውኖችን ብቻ ሳይሆን አስከፊ የሚባሉትንም በመቀበል፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያን በጋራ ሊገነቡ የሚያስችሉ የመሠረት ድንጋዮችን ማኖር ተገቢ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ሰላም የሚቀድም ነገር የለምና፡፡

ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸውም ዘመኑን የሚመጥን አስተሳሰብ መላበስ ይኖርባቸዋል፡፡ ዓላማቸውን ለማስፈጸምም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገዶችን መከተል አለባቸው፡፡ ውስጣቸው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን ከሌሎች ጋር መግባባት ስለማይችሉ፣ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራቸው ከውስጥ ወደ ውጭ ብቻ ሳይሆን ከውጭ ወደ ውስጥም ተመልካች መሆን ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለቁጥር የሚያታክቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሥርተው የፈረሱት፣ ከውጫዊ ተፅዕኖ ባልተናነሰ በራሳቸው ውስጣዊ ችግር እንደሆነ የማይካድ ነው፡፡ ጊዜያዊ ግንባርና ትብብር ፈጥረው በግለሰቦች መታበይ ብዙዎች እንዳይሆኑ ሆነው አልፈዋል፡፡ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ለዘመናት ሲደሰኮርለት የነበረው “የዓላማና የተግባር አንድነት” እንደ እንቧይ ካብ የተናደው፣ ውስጣዊ ሰላምና ዴሞክራሲ በመጥፋቱ እንደነበር ከፈረሰው ኢሕአዴግ ውድቀት መማር ይቻላል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተተብትቦ የግለሰቦች መፈንጫ የነበረው ኢሕአዴግ ወራሽ ብልፅግና፣ ከዚህ ታሪክ ካልተማረ ስህተት መደጋገሙ አያጠራጥርም፡፡ ብልፅግና የሚመራው መንግሥት ውስጥ በግልጽ የሚታዩ ከቀድሞ የተወረሱ አሳሳቢ ጉዳዮች ስላሉ፣ እንደ ቀድሞው ሁሉ አሁንም በሕግ አምላክ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል አሁንም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያሉት ጭምር፣ ከስህተታቸው ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ አሉ፡፡ የሰላምን መንገድ መዝጋት አያዋጣም፣ ለኢትዮጵያ ህልውናም አይበጅም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጭቆና ቀንበር የሚላቀቀው፣ ከአስከፊው የድህነት ማጥ ውስጥ የሚወጣው፣ መብቱና ነፃነቱ ተከብሮ በሰላም መኖር የሚችለው የአገሪቱ ልሂቃን ራሳቸውን ሲገሩ ነው፡፡ በትምህርት ተቋማት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሲቪክ ማኅበራት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት፣ በእምነት ተቋማት፣ በሚዲያዎችና በመሳሰሉት ውስጥ የሚገኙ ልሂቃንም ራሳቸውን መግራት ካልቻሉ አንዲት ጋት መራመድ አይቻልም፡፡ ልሂቃኑ ከታሪክ ስህተት ተምረው ለዘመኑ የሚመጥን ቁመና ላይ ካልተገኙ መኖራቸው በራሱ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በግልጽነትና በተጠያቂነት መንፈስ ፈትሸውና ተንትነው ለመፍትሔ የሚረዱ ሐሳቦችን ማቅረብ የሚገባቸው ልሂቃን፣ ፋይዳ ቢስ የአሉባልታ ኩሬ ውስጥ ሲዋኙ ያሳፍራል፡፡ የተለዩ ሐሳቦችን በምክንያታዊነት መሞገት የሚጠብቃቸው ልሂቃን በሴራ ንድፈ ሐሳብ ትንተና ብቻ ከተጠመዱ፣ መኖራቸው ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ የቀሰሙት ዕውቀት ችግር ፈቺ መሆን ሲገባው፣ ለተጨማሪ ችግሮች መፈልፈያ ሲውል ያሳስባል፡፡ የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ካጋጠሙና ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ችግሮች አንፃር በመተንተን መልካም ዕድሎች እንዳይመክኑ ማድረግ የሚገባቸው ልሂቃን፣ በሚፈለጉበት ቁመና ላይ ሳይገኙ በስህተት ላይ የሚረማመዱ ከሆነ ኪሳራው የአገር ነው፡፡ የእስካሁኑን ተደጋጋሚ ስህተት ማረም የሚቻለው ለአገር ቅድሚያ በመስጠት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያ ሰላም ማንኛውም መስዋዕትነት መከፈል አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...