Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

​​​​​​​መንግሥት ኢትዮጵያን የማይመጥኑ ድርጊቶችን ያስወግድ!

የአንድን አገር የሰላም፣ የዴሞክራሲ፣ የዕድገትና የዘለቄታ ጉዞ አመልካች ከሆኑ መሥፈርቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የመንግሥት አገርን በብቃት የመምራት አቅምና የሕዝብ እርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ባልተጣጣሙበት ስለአገር ጉዳይ ለመግባባት ይቸግራል፡፡ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሲቃኝ ደግሞ የተለያዩ ፍላጎቶችና የፖለቲካ አመለካከቶች ቢኖሩም፣ እነዚህን ልዩነቶች አቻችሎና አስታርቆ አገርን መምራትና እርካታ መፍጠር የግድ የሚባልበት ጊዜ ውስጥ ነን፡፡ ለዘመናት ሕዝቡ በልዩነቶቹ ውስጥ ሆኖ ያኖራትን አገር በአግባቡ መምራት ሲያቅት፣ ችግሮች ሲፈጠሩ አፋጣኝ መፍትሔዎችን አለመፈለግና ችላ ማለት ለአገር ህልውና አይበጅም፡፡ ለዘመናት በልዩነቶቹ አጊጦ የኖረ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት ነው፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ ኢትዮጵያን የማይመጥኑ ድርጊቶችን ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ባዕድ መሆን የለበትም፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ ካልሆነና ተጠያቂነት ከሌለበት ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ሕዝብና መንግሥት መተማመን ካልቻሉ ደግሞ አገር ሰላም መሆን አትችልም፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለበት የመንግሥት ሥልጣን ለበርካታ ችግሮች መንስዔ ስለሚሆን፣ የሕዝብን የማወቅ መብት ማክበር ተገቢ ነው፡፡ ከዘርፈ ብዙ ችግሮች መካከል አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን በማንሳት መነጋገር ተገቢ ነው፡፡

የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ለስምንት ወራት ሲያካሂድ የቆየውን ዘመቻ በማቆም፣ የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን በድንገት አስታውቋል፡፡ ማንም ጤነኛ ሰው እንደሚገነዘበው ጦርነት ለምንም ነገር መፍትሔ ባለመሆኑ፣ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የበኩልን መወጣት ተገቢ ነው፡፡ ከጥቅምት መጨረሻ እስካሁን ድረስ በተካሄደው ጦርነት ብዙዎች ውድ ሕይወታቸውን መክፈላቸው፣ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ መፈጠሩና የአገር ሀብት መውደሙ የሚያስቆጭ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ በድንገት እዚህ ውሳኔ ላይ ሲደረስ በተቻለ መጠን ሒደቱ ደረጃ በደረጃ ቢታወቅ ኖሮ፣ ቢያንስ በሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን ውዥንብር ለማጥራት ጠቃሚ ይሆን ነበር፡፡ አንደኛው ወገን የተናጠል ተኩስ አድርጎ ክልሉን ለቆ ሲወጣ፣ ተገዳዳሪው ደግሞ በአሸናፊነት ይዞታውን ማስመለሱን ሲያውጅ ነገ ምን ሊከሰት እንደሚችል ብዙዎችን ግራ ያጋባል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ የጠላትነት ስሜቶች ተጋግለው አገርን ቀውስ ውስጥ የሚያስገባ ችግር እንዳይፈጠር፣ ምን እየተደረገ እንደሆነ በግልጽ መነገር ይኖርበታል፡፡ እንደተባለው በሰብዓዊነት መንፈስ ዕርምጃው ተወስዶም ከሆነ በተብራራ መንገድ ለሕዝብ መገለጽ ሲገባው፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥያቄዎች ቢነሱ ሊያስገርም አይገባም፡፡ የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ከውስጣዊ ችግሮች ጋር ተዛምዶ የሚፈጥረው ቀውስ ሥጋት ፈጥሮ ከሆነም፣ ከመንግሥት በኩል የተብራራ መረጃ ለሕዝብ ሊቀርብ ይገባል፡፡ የተድበሰበሰ መረጃ ከጥቅሙ ጉዳቱ ከማመዘኑም በላይ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አይመጥንም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሊቀረፍ ያልቻለ ሌላ አንድ ትልቅ ችግር የፓርቲና የመንግሥት ሥራዎች መደበላለቅ ነው፡፡ በማናቸውም የዴሞክራሲ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ፓርቲዎች በምርጫ ሥልጣን ይይዛሉ፡፡ ለፖለቲካ ተሿሚዎችና ለባለሙያዎች ኃላፊነቶች ተለያይተው ይሰጣሉ፡፡ በሁሉም ሥፍራ የፖለቲካ ተሿሚዎችን ብቻ በመመደብ አገርን በካድሬ ለማስተዳደር ስለማይቻል፣ ለባለሙያዎች ትልቅ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ከፌዴራል ተቋማት እስከ ወረዳ መዋቅር፣ ከመንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋማት እስከ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ማደራጃ፣ ከጤና ድርጅቶች እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሁሉም ቦታዎች ውስጥ ለፓርቲ አባላት ብቻ ሹመት ማደል ማብቃት አለበት፡፡ በመላ አገሪቱ የሚገኙ የከተማ አስተዳደሮችና መንግሥታዊ ተቋሟት በባለሙያዎች የማይመሩት ለምንድነው? አገሪቱ ያስተማረቻቸው ልሂቃን ካላገለገሏት ምን ይሠሩላታል? ሁሉም የኃላፊነት መደብ በካድሬ ተይዞ ውጤት ይገኛል ማለት ዘበት ነው፡፡ ውጤቱም በተግባር እየታየ ነው፡፡ በአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች እንደ ችሎታቸውና ዝንባሌያቸው አገራቸውን እንዲያገለግሉ ዕድሉ ይሰጣቸው፡፡ ካድሬ ሁሉም ቦታ ሲሰገሰግ ሥልጣኑን ለማራዘም ሲል ምርጫ ለማጭበርበር የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ የድምፅ መስጫ ሳጥን ሳይቀር ከመስረቅ አይመለስም፡፡ በዚህም ምርጫ አቤቱታ የቀረበባቸው የካድሬ ሕገወጥ ድርጊቶች አሉ፡፡ ሕዝቡን የማይመጥኑ ተራ ድርጊቶች ናቸው፡፡

ኃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት አለመቻል የመንግሥት ሹማምንት ሌላው ችግር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ቦታዎች ቸልተኝነት በስፋት ይስተዋላል፡፡ የሚቆጣጠር አካል የለም ወይ እስኪባል ድረስ ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት ምክንያት፣ በየቦታው በጣም የሚያሳፍሩ ድርጊቶች ተንሰራፍተዋል፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ መንግሥታዊ አገልግሎት ሲስተጓጎልበትና ቅሬታ ሲያቀርብ አዳማጭ አያገኝም፡፡ በየቦታው ራሳቸውን ያነገሡ ሹማምንት ማንንም ሳያፍሩ በአደባባይ ጉቦ ይጠይቃሉ፡፡ አልሰጥም ያለውን ያንገላታሉ፡፡ ብልሹ አሠራሮችን በማስፈን የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የደላሎች መፈንጫ አድርገዋል፡፡ የሕዝብና የመንግሥት እየተባለ የሚለፈፍለትን መሬት ዛሬም በአደባባይ ማስወረርና የደላላ ሲሳይ ማድረግ ሊገላገሉት ያልቻሉት በሽታ ነው፡፡ ፍትሕ ፍለጋ የሚባዝኑ ዜጎች እንባቸውን የሚያብስላቸው በመጥፋቱ በየቤታቸው ይብሰለሰላሉ፡፡ በወረዳና በክፍላተ ከተሞች፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ በሕክምና ተቋማት፣ በግብይት ሥፍራዎች፣ በመንገድና ትራንስፖርት መሥሪያ ቤቶች፣ ወዘተ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት አይሞከርም፡፡ በአንድ ሰሞን የዘመቻ ግርግር ደንገጥ ብለው የሚሉ ሹሞች ነገሮች ሲረጋጉ ለበቀል ይነሳሉ፡፡ በዚህ ሥልጡን ዘመን ለሕዝብም ለአገርም የማይመጥኑ በየቦታው ተኮልኩለው አገር ሲያተራምሱ ያስቆጫል፡፡ በፓርቲ አባልነታቸው ብቻ እየተኩራሩ ሕግ ሲጥሱ ምንም አይሰማቸውም፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሞራል ልዕልና አይመጥኑም፡፡

አንድን ነገር በተመሳሳይ መንገድ በተደጋጋሚ በመሥራት ውጤት ማግኘት አይቻልም፡፡ እንዲሁም ስህተትን በስህተትማረም መሞከር ፋይዳ የለውም፡፡ ካለፉት ጥፋቶች ባለመማር ተደጋጋሚ ስህተቶች ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ በአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ማግለል፣ ሽማግሌዎችን ማራቅ፣ ምሁራንን አትድረሱብኝ ማለትና ወጣቶችን ተስፋ ማስቆረጥ ለዓመታት የዘለቀ የአገር በሽታ እንደነበር ብዙ የተባለበት ነው፡፡ አገርን ለመምራት ከብቃትና ከቁርጠኝነት ባሻገር የተለያዩ አስተያየቶችን ማድመጥም የአመራር ችሎታ ማሳያ ነው፡፡ በአንዳንድ የገዥው ፓርቲ አመራሮች ዘንድ እየታየ ያለው ግን በአንድ አቅጣጫ በተቃኘ አስተሳሰብ፣ የእውነትና የብርሃን መንገድ መሪ ለመሆን መንደፋደፍ ነው፡፡ የጀመሩትን ጉዞ ሳያቋርጡ በየመሀሉ የሌሎች ወገኖችን ምክርና የዕውቀት ተሞክሮ ማዳመጥ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን መልካም አጋጣሚ ወደ ጎን እየገፉ ከስህተት ወደ ስህተት መረማመድ ማንንም አያዋጣም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የታየው ግን ስህተትን በስህተት ለማረም እየተሞከረ ነው፡፡ ከዚህ የሚገኘው ውጤት ደግሞ አንገት ከማስደፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ሕዝብ እርካታ እንዲሰማውና በአገሩ ተስፋ እንዲኖረው ካልተደረገ በስተቀር፣ ሕዝብን እያስከፉ በግትርነት መቀጠል ውጤቱ አያምርም፡፡ ይህም ለሕዝባችን አይመጥንም፡፡

በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃመተማመንና በአብሮነት ለመዝለቅ የሚያስፈልገው፣ ለዘመኑ የሚመጥን የአመራር ጥበብመጎናፀፍ ነው፡፡ ትናንት የነበረው ሴረኝነት ለዛሬ አይሠራም፡፡ ዛሬም ካለ ለነገ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በትናንት ከንቱነት እየተኩራሩ የዛሬውን ዘመን በዚያው መንገድ ለመግራት መሞከር ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ይህች አገር ምንም እንኳ ለዘመናት በድህነትና በኋላቀርነት ውስጥ ብትዳክርም፣ በአንድ ወቅት ገናና ታሪክ የነበራት ናት፡፡ ለዓለም ካበረከተቻቸው ቅርሶች፣ ሥልጣኔዎችና በልዩነቶች ውስጥ ተቻችሎ የመኖር ተምሳሌታዊነቷ ጋር የተገመደው ታሪኳ፣ በጥቁር ዓለም ሕዝቦች ዘንድ አንፀባራቂ ያደረጋትን ፀረ ኮሎኒያሊስት ተጋድሎዋን ጭምር ያስተጋባል፡፡ ለአገሩ ቀናዒ የሆነው ሕዝቧ ደግሞ ሕግ አክባሪ፣ ሰላም ወዳድና በአግባቡ የሚመራው ካገኘ አንፀባራቂ ድል ማስመዝገብ የሚችል መሆኑን በዚህ ምርጫ ሳይቀር አሳይቷል፡፡ ይህንን ኩሩ ሕዝብ በአግባቡ መምራት ካልተቻለ የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ይህች ታሪካዊት አገር ልትመነደግ ስትፍጨረጨር የማይመጥኗት ድርጊቶች ሊወገዱ ይገባል፡፡ በተለይ ደግሞ አንገት የሚያስደፉ ድርጊቶችን ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል መንግሥት ኢትዮጵያን የማይመጥኑ ድርጊቶችን ቢያስወግድ ይመረጣል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...