Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

አርሶ አደሩን ያማከለው ፕሮጀክት

ትኩረቱን በልማታዊ ትብብር ላይ ያደረገውና ‹‹ኢንተርናሽናል ኦርጋናይዜሽን ፎር ዴቨሎፕመንት ኮኦፕሬሽን›› በሚል መጠርያ የሚታወቀው ተቋም፣ በተለያዩ ክልሎች የአርሶ አደሮችን የገቢ አቅም በማጎልበት ውጤት እንዳስመዘገበ ይነገርለታል፡፡ አቶ ደስታ ዳመና የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቢሮ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በድርጅቱ እንቅስቃሴና ባከናወናቸው የልማት ተግባራት ላይ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡-  በልማታዊ ትብብር ላይ እንደምታተኩሩ መጠርያችሁ ያመለክታል፡፡ ስለ ተቋማችሁና የልማት ሥራውን በኢትዮጵያ መቼና የት እንደጀመረ ቢገልጹልን?

አቶ ደስታ፡- ኢንተርናሽናል ኦርጋናይዜሽን ፎር ዴቨሎፕመንት ኮኦፕሬሽን መቀመጫውን ኔዘርላንድስ ያደረገ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ የተቋቋመውም በ1956 ዓ.ም. ሲሆን፣ ዓላማውም አነስተኛ ገቢ ያላቸውን አርሶ አደሮች አቅም ማሳደግ ነው፡፡ ዓላማውንም ዕውን ለማድረግ የሚንቀሳቀሰው በአፍሪካ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ ነው፡፡ በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቡርኪና ፋሶ፣ በሩዋንዳና በሴኔጋል ውስጥ እየሠራ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከ40 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡  

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱ በየትኞቹ ክልሎች እየተገበረ ይገኛል?

አቶ ደስታ፡- በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በአፋርና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሚገኙ በተለያዩ ወረዳዎች ነው፡፡ ሥራውም የሚያተኩረው በአነስተኛ ይዞታ የሚተዳደሩ አርሶ አደሮችን ኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ፣ ምርትና ምርታማነታቸውን ማሳደግና ድርቅን የመቋቋም አቅማቸውን ማጠናከር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የወጣቶችን የሥራ ፈጠራ የማጎልበት፣ አርሶ አደሮችን ከተለያዩ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር የማገናኘት፣ የገበያ ትስስር መፍጠርና የወተት ከብት እርባታ ላይ ያለመ እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡ ለዚህም የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ቀርፆ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚከተለው አካሄድ ምን ይመስላል? አርሶ አደሮቹ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለመሆን እንዴት እየተንቀሳቀሱ ነው?

አቶ ደስታ፡- ፕሮጀክቱን ተግባራዊ የሚያደርግባቸው አካሄዶች የተለያዩ ናቸው፡፡ የቁጠባና ብድር አገልግሎት ለማግኘት እንዲያስችላቸው በየአቅራቢያቸው ከሚገኙ ስድስት የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ በማድረግ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አርሶ አደሮቹም በተበደሩት ገንዘብ ያለሟቸውን ወይም ያቀዷቸውን ሥራዎች ሁሉ አከናውነው የተበደሩትን ተመላሽ እያደረጉ ለቀጣይ ሥራቸው ደግሞ ሌላ ብድር እየወሰዱ በመንቀሳቀስ ከድህነት አረንቋ ለመላቀቅ እየጣሩ ነው፡፡ ምርጥ ዘር በማቅረብ ምርትና ምርታማነታቸውን ከፍ ከማድረግ ባሻገር ካመረቱትም መካከል ከፊሉን ለቀለባቸውና ለዘር ሲያስቀምጡ፣ የቀረውን ገበያ አውጥተው በመሸጥ ፍላጎታቸውንም እያረኩ ነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በዚህ ዓይነት መልኩ በኦሮሚያ ክልል የነበረው ፕሮጀክት የመተግበሪያ ጊዜው ያለቀ ሲሆን፣ በቀሩት ክልሎች ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡  

ሪፖርተር፡- በኦሮሚያ ክልል ሲከናወን የቆየው ፕሮጀክት ለስንት ዓመት የቆየ ነበር፣ በዚህም ፕሮጀክት ምን ያህል አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል?

አቶ ደስታ፡- ፕሮጀክቱ እየተተገበረ የነበረው በኦሮሚያ ክልል በአርሲና በምዕራብ አርሲ ዞን በሚገኙ የቢራ ገብስ እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ ዞን በድንች አምራች አርሶ አደሮች ላይ ነው፡፡ በሦስት ዞኖችና ሰባት ወረዳዎች ለሚገኙ አምራች አርሶ አደሮች ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2013 ዓ.ም. የልማት ሥራዎቹ ተሠርተዋል፡፡ በዚሁ ፕሮጀክት 76,000 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የማድረግ ዕቅድ የነበረን ቢሆንም፣ በተከናወነው ብርቱ ሥራ 86,000 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ችለናል፡፡      

ሪፖርተር፡- የተጠቀሱት አርሶ አደሮች የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለመሆናቸው ማረጋገጫው ምንድነው?

አቶ ደስታ፡- ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የብድር አገልግሎት ለማግኘት የተንቀሳቀሱበትን እንዲሁም የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ በወተት ከብት ዕርባታ ላይ ለማልማት ሲንቀሳቀሱ ጉዳዩ በይበልጥ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል የቀረበላቸውን አገልግሎት፣ በድርጅቱም በኩል የተደረገላቸው ድጋፍና አስተዋጽኦ  ግምት ውስጥ ያስገባ መረጃ ማጠናከር ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ኦሮሚያ ላይ ትኩረት ያደረግው ፕሮጀክት ቢያበቃም በድጋሚ የሚተገበርበት አካሄድ ይኖር ይሆን? በቀሩት አራት ክልሎች እየተተገበረ ያለው ፕሮጀክት ዕጣ ፈንታ ምንድነው?

አቶ ደስታ፡- በኦሮሚያ ክልል ድርጅቱ ይንቀሳቀስባቸው በነበሩ ወረዳዎች ተጀምሮ የተጠናቀቀውን ፕሮጀክት ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ድርጅቶች በዕለት ተዕለት ሥራቸው ውስጥ አካትተው የሚያጠናክሩት ይሆናል የሚል እምነት አለን፡፡ ይህም ሆኖ ግን ያለፈውን ልምድና ተሞክሮ ወስደን ተመሳሳይ ፕሮጀክት ዲዛይን እናደርጋለን፡፡ ለዚህም አስፈላጊውን ፈንድ ፈላልገን ዳግም የምንሠራበት ጊዜ ይኖራል፡፡ በቀሩት አራት ክልሎች የሚካሄደው ፕሮጀክት ግን እስከ ሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ድረስ ይዘልቃል፡፡    

ሪፖርተር፡- በኦሮሚያ ክልል ሲከናወን የቆየውና አሁን የተጠናቀቀው እንቅስቃሴያችሁ ግምገማ ምን ያሳያል?

አቶ ደስታ፡- የአርሶ አደሮቹ ተወካዮች፣ ከጉዳዩ ጋር ይበልጥ ትስስርና ግንኙነት ካላቸው የባለድርሻ አካላት፣ የግብርና ባለሙያዎችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎ፣ እንዲሁም ኔዘርላንድስ ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት የተመረጡ ሰዎች ተሳታፊ የሆኑበት ስብሰባ አድርገናል፡፡ በአምስቱ ዓመት ፕሮጀክት ላይ ጥልቅ የሆነ ውይይትና የሐሳብ መለዋወጥ ነበር፡፡ በውይይቱ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን የዳሰሱ የፓናል ውይይት ተከነውኗል፡፡ ከግምገማውና ከውይይቱ ከተገኘው ውጤት ለመረዳት እንደተቻለው ፕሮጀክቱ እጅግ ጠቃሚና ለሌሎች አስተማሪ ሆኖ መገኘቱን ነው፡፡ በአጠቃላይ እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክት በክልሉ በሚገኙ ሌሎች ወረዳዎች ላይ ቢተገበር መልካም መሆኑ ተደርሶበታል፡፡    

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...