Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመሠረት በማኖር ብቻ የቀረው ሁለገብ ሕንፃ

መሠረት በማኖር ብቻ የቀረው ሁለገብ ሕንፃ

ቀን:

ከሃያ ሁለት ማዞሪያ አደባባይ ወደ መገናኛ በሚያቀናው የአስፋልት መንገድ ግማሽ ፌርማታ ያህል በመጓዝ መክሊት ሕንፃ ይደረሳል፡፡ በስተቀኝ በኩል ወደ ውስጥ የሚያደርሰውን ኮረኮንች መንገድ በመያዝ በግምት 400 ሜትር ያህል ከተኬደ በኋላ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጡረተኞች ማኅበር ጽሕፈት ቤት›› የሚል ማስታወቂያ የተለጠፈበት አንድ ትልቅ ግቢ ይገኛል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት የሚገኘው ይህ ግቢ ዙሪያው በቆርቆሮ አጥር የተከለለ ሲሆን፣ ከዋናው በር በስተቀኝ በኩል ካለው አጥር ጋር የተያያዘና የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ለዳቦ መሸጫ ያዘጋጁት የአንበሳ አውቶቡስ ቆሞ ይገኛል፡፡

ይህም አውቶቡስ ለሁለት ተከፍሎ አንደኛው የበሰለ ምግብና የጀበና ቡና ይሸጥበታል፡፡ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ ጫት መቸርቸሪያ ሆኗል፡፡ ከዋናው ኮረኮንች መንገድ ፊት ለፊት ካለው የቆርቆሮ አጥር ጋር ተያይዞ ደግሞ ኮንቴይነር፣ የፕላስቲክና በተለምዶ ‹‹አርከበ ሱቅ›› እየተባሉ የሚጠሩት ቤቶች ይታያሉ፡፡

በዚህ መልክ ከሚገኙት ቤቶች መካከል ግማሾቹ የልዩ ልዩ ዓይነት ሸቀጦች መቸርቸሪያ መደብሮች፣ ምግብና ድራፍት ቤቶች ሲሆኑ፣ እንደ መዝናኛ የሚመስሉ ካፍቴሪያዎችም ደንበኞቻቸውን ሲያስተናግዱ ይስተዋላሉ፡፡  

ወደ አጥር ግቢው ዘልቆ ሲገባ ፈረስ የሚያስጋልብ ሰፊ ሜዳ፣ ያለአገልግሎት ባዶውን ተራቁቶ ይታያል፡፡ በዋናው የአጥር በር በኩል ወደ ግቢው ሁለት ዕርምጃ ያህል ገባ ሲባል፣ ለጡረተኞች ልዩ ልዩ ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ ለሚገነባው ሁለገብ ሕንፃ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የካቲት 16 ቀን 2000 ዓ.ም. ያስቀመጡት የመሠረት ድንጋይ ይገኛል፡፡

ይሠራል ተብሎ በወሬ የቀረው ይህ ሕንፃ ባለ አራት ፎቅ ሆኖ ለጡረተኞች የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ክሊኒክ፣ መዝናኛና ካፍቴሪያ፣ ለገቢ ማስገኛም የሚውሉ ልዩ ልዩ ክፍሎች እንደሚኖሩት በወቅቱ ተገልጿል፡፡ ይህ ከሆነ ዛሬ 13 ዓመት ሆኖታል፡፡ ማኅበሩ የአገርና የሕዝብ ገንቢና ተጠሪ የነበሩና የሆኑ ጠረተኞች በአፍላ ዘመናቸው ለአገራቸው አገልግሎት በመስጠት የጡረታ ዕድሜያቸው ጣራ ሲደርሱ በጡረታ በክብር የተሰናበቱ ኢትዮጵያውያንን ያካተተ ነው፡፡

ጡረተኞቹ በቀሪ ጊዜያቸው ሊያጋጥሟቸው ከሚችሉ የማኅበራዊና የምጣኔ ሀብት ችግሮች አቅም በፈቀደ መጠን ተገቢ ድጋፍ ለመስጠትና ለአገር ለወገን ይጠቅማል የሚሉትን ሁሉ በማሰባሰብና በጥንቃቄ በመጠበቅ ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍም የሚሠራ ነው፡፡

አቶ ዓለሙ ሰይፉ የአዲስ አበባ ከተማ የጡረተኞች ማኅበር ዋና ፀሐፊ ናቸው፡፡ የሕንፃው ነገር ከምን ደረሰ? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ‹‹ለሕንፃው ማስጀመርያ የሚውል የተለያዩ የገቢ ምንጮችን ለመፍጠር እንቅስቃሴዎችን አካሂደናል፡፡ ከእንቅስቃሴያችንም መካከል በአጥሩ ዙሪያ ሱቆች፣ ለምግብና ቡና ቤቶች፣ እንዲሁም ለሸቀጣ ሸቀጥ መቸርቸሪያና ለብረታ ብረት ሥራዎች ያከራየናቸው ቤቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከእነዚህም በሚገኝ ገቢ ቢያንስ የሕንፃውን መሠረት ለማውጣት አስበናል፡፡ በዚህ ላይ የእኛ መንቀሳቀስ ብቻ የትም አያደርሰንም፡፡ ስለሆነም ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ባለሀብቶች፣ አገር ወዳድ ግለሰቦችና በጎ አድራጊዎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እጆቻቸውን እንዲዘረጉልን እንማፀናለን፤›› ብለዋል፡፡

ከአንድ ሺሕ ሜትር ካሬ በላይ በሆነው በዚሁ ቦታ ላይ ከ13 ዓመት በፊት ሊገነባ ታስቦ የነበረውን ይህን ሕንፃ አስጀምሮ ለማስጨረስ የተተመነው የገንዘብ መጠን 26,000,000 ብር እንደነበር፣ አሁን ግን ወጪው የትየለሌ እንደሆነና ይህንንም ለመሸፈን የማኅበሩ አቅም እንደማይችል አቶ ዓለሙ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ምን ያህል ገንዘብ ተሰብስቧል? አጠቃላይ የማኅበሩ ገንዘብ አቅም እንዴት ይታያል? በሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ማብራሪያ ፈልገን ለጊዜው ሰብሰብ ያለ መረጃ እንደሌላቸው፣ በተረፈ ማኅበሩ ከ35,000 በላይ የተመዘገቡ አባላት እንዳሉት፣ ከእነዚህም መካከል ቁጥራቸው በውል ያልተለዩ አባላት በሞትና በተለያዩ እክሎች ምክንያት አባልነታቸውንና ወርሃዊ ክፍያቸውን እንዳቋረጡ አመልክተዋል፡፡

ማኅበሩ ራሱን የቻለ ክሊኒክ አቋቁሞ የአባላቱን ጤንነት ሲንከባከብ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ብዙዎቹ አባላት በጤና መድን በመታቀፋቸው፣ ማኅበሩም ለክሊኒኩ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን እጁ እያጠረበት በመምጣቱ የተነሳ ክሊኒኩ አገልግሎቱን ካቋረጠ ውሎ ማደሩን ተናግረዋል፡፡

በየወሩ እየታተመ ይወጣ የነበረውና ‹‹ዋስትና›› በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ጋዜጣ ከአገልግሎት ውጪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጋዜጣው በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ልዩ ልዩ መረጃዎችን የሚያዝና በአባላቱም ዘንድ የተፈላጊኒቱ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቶ እንደነበረ አስረድተዋል፡፡

የማኅበሩን እንቅቃሴና የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ ብቻ ስለቀረው ሁለገብ ሕንፃ ጉዳይ ከሠራተኞና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአረጋውን ጉዳይ ማስተባበሪያና መከታተያ ጽሕፈት ቤት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮና ከአዲስ አበባ ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ሰፋ ያለ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም፡፡

መርሐ ግብሩን በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ገደብ ዕቅድ በማውጣት ተግባራዊ ለማድረግ ይንቀሳቀሳል የተባለለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጡረተኞች ማኅበር በጥቂት ሩቅ አሳቢዎች ጥረት የተቋቋመው በ1984 ዓ.ም. ሲሆን፣ ሕጋዊ የምስክር ወረቀት ያገኘው ደግሞ በ1986 ዓ.ም. መሆኑ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...