Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበቴክኖሎጂ የታገዘ የቤት ለቤት ሕክምና አገልግሎት

በቴክኖሎጂ የታገዘ የቤት ለቤት ሕክምና አገልግሎት

ቀን:

የቤት ለቤት ሕክምናና ማስታመም አገልግሎት በኢትዮጵያ እምብዛም አልተለመደም፡፡ በርካታ የጤና ባለሙያዎች ቢኖሩም፣ በሐኪም ቤትም ሆነ በቤት ሕሙማን ከመደበኛ ሕክምና ውጭ ያለውን ክብካቤ የሚያገኙት በቤተሰብ፣ በዘመድና ጓደኛ ነው፡፡ በቤት ውስጥ ለዓመታት የቤተሰብ አባልን ማስታመምና መንከባከብም ለኢትዮጵያውያን የተለመደ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሕክምና ባለሙያዎች ክብካቤው ቢደረግ፣ አገልግሎቱን የሚሰጡት የጤና ባለሙያዎች ቦታና ጊዜ ሳይገድባቸው ሕክምና ለሚያገኘው ሰው ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የሚደርሰውን እንግልትና ስቃይ ያስቀራሉ፡፡ የቤተሰብን ድካምም ይቀንሳሉ፡፡ ለሥራ አጥ ሐኪሞችም የሥራ ዕድል ይፈጠራል፡፡

አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በዚህ ዓይነት አገልግሎት ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኸልፐርስ የቤት ለቤት ሕክምናና ማስታመም አገልግሎት በዘርፉ ከተሰማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ ወደ አገልግሎት ከገባ አምስት ዓመት የሞላው ድርጅቱ፣ በኢትዮጵያ የቤት ለቤት ሕክምና አገልግሎት የሞባይል መተግበሪያ (ሞባይል አፕልኬሽን) ዲዛይን አድርጎ አቅርቧል፡፡

የድርጅቱ መሥራች፣ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ጤና መኮንን አበራ ጉልላት እንደገለጹት፣ የሞባይል መተግበሪያው ድርጅቱ ከዚህ በፊት የነበሩትን አገልግሎቶች ይበልጥ ተደራሽ በማድረግ የጎላ ሚና ይጫወታል፡፡ አገልግሎቱን ይበልጥ የዘመነ የሚያደርግ ሲሆን፣ ሕሙማን በአቅራቢያቸው ባሉ ጤና ባለሙያዎች አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግም ሰፊ ዕገዛ ያበረክታል፡፡

የጤና ባለሙያዎች በአቅራቢያቸው ሥራ የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል የተባለው መተግበሪያ፣ ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የባለቤትነት መብት እንዳገኘ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የንግድ ሥራ ፈቃድ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ሕጋዊ ፈቃድ እንደተሰጠው የድርጅቱ መሥራች ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ በዋናነት ከሚሰጣቸው አልግሎቶች መካከል የቤት ለቤት ማስታመምና የአረጋውያን እንክብካቤ፣ ለደም ግፊት፣ ለስኳርና ለካንሰር ሕሙማን የሕክምና ክትትልና ማስታመም፣ ቁስልን በኬሚካል ማፅዳትና ማከም፣ በነርስ የታገዘ የሞግዚትነት አገልግሎት፣ ፊዚዮቴራፒ፣ በሆስፒታል ውስጥ አስታማሚን ተክቶ ማስታመም እንደሚገኙበትም አክለዋል፡፡

በሐኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን መስጠት፣ የቤት ለቤት የሐኪሞች ጉብኝት፣ በአፋቸው መመገብ ለማይችሉ ሕሙማን የሚመገቡበትን መሣሪያ መቀየር፣ የሽንት ቱቦ ማስገባትና መቀየር እንዲሁም የቤት ለቤት ሕክምና ዕቃዎችን ማቅረብ ከሚያበረክታቸው አገልግሎቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እንደ ጤና መኮንን አበራ የተጠቀሱትን አገልግሎቶች የሚሰጠው የከፍተኛውን፣ የመካከለኛውንና የዝቅተኛውን ማኅበረሰብ የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ተቋሙ እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ ለ35 የጤና ባለሙያዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር ለ65 ሕሙማን ነፃ የቤት ለቤት ሕክምና አገልግሎት፣ 15 ለሚሆኑ አካል ጉዳተኞች ደግሞ የዊልቸር ድጋፍ አድርጓል፡፡ በድርጅቱ መቀጠር የሚፈልጉ የጤና ባለሙያዎች ዳታውን በመጫን መመዝገብ እንደሚችሉ፣ ለምዝገባ የብቃት ምዘና ፈተና (ሲኦሲን) ማለፍ ግድ ሲሆን፣ የሥራ ልምድ መኖሩ ባይከፋም ግዴታ አለመሆኑን፣ ወደ ሥራ ወይም ወደ አገልግሎት የሚሰማሩት በቅድሚያ ድርጅቱ የሚያዘጋጀውን ሥልጠና ተከታትለው ካጠናቀቁ በኋላ መሆኑን ነው አመልክተዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ አነጋገር፣ ድርጅቱ የተጠቀሱትን አገልግሎቶች የሚሰጠው በአዲስ አበባና አካባቢዋ ብቻ ነው፡፡ በቀጣይም በየክልሎቹ ማስተባበሪያ ቢሮ በማቋቋም አገልግሎቱን ለመስጠት ዕቅድ አለ፡፡

የሥልጠና ዲፓርትመንት ኃላፊ በኃይሉ አበራ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ማንኛውም የጤና ባለሙያ ዳታውን በመጫን ሊመዘገብ እንደሚችል፣ ምዝገባው የሚከናወነው የባለሙያውንና የታካሚውን (ደንበኛው) የመኖሪያ አካባቢ ቅርበት አማክሎ ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱም አካሄድ ባለሙያውን ከትራንስፖርት ወጪ ለማዳንና ደንበኛውም አገልግሎቱን በፈለገው መጠን እንዲያገኝ ለማድረግ ነው፡፡

የፌዴራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አዳዲስ የሥራ ዕድሎችና ፕሮጀክቶች ዳይሬክተር ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ደርሶልኝ፣ የቤት ለቤት ሕክምናና ማስታመም አገልግሎት መስጠት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሦስት ዓይነት ጥቅሞች እንዳሉት ገልጸው፣ ከቀጥታ ጥቅሞች አንደኛው የፈጠራ ሥራ ተጠቃሚ መሆን፣ ሁለተኛውና ሦተኛው ደግሞ እንደ ቅደም  ተከተላቸው ለተመራቂ ሐኪሞች የሥራ ዕድል መፍጠርና ታካሚዎችን ባሉበት አገልግሎት መስጠት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል የሚጠፋውን ጊዜ እና በዚህም የተነሳ የሚያጋጥመውን ከሥራ ገበታ የመቅረት ዕድል እንደሚያድን እንዲሁም አስታማሚ የሌላቸውን ደግሞ ተንከባክቦና አስታማሚ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የሥራ ዕድል በመፍጠር ሒደት ውስጥ ሦስት ነገሮችን እንደሚያምንና አዳዲስ አስተሳሰቦችን ማምጣት፣ ፈጠራ የታከለባቸውን ሥራዎች በትብብርና በቅንጅት መሥራትና በመተማመንና በተግባር መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...