Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለኮቪድ-19 ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ትምባሆ አጫሾች

ለኮቪድ-19 ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ትምባሆ አጫሾች

ቀን:

ትምባሆ በሰው ማኅበራዊ ሕይወትና ኢኮኖሚ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የሚያደርስ ምርት በመሆኑ፣ በዓለም ጤና ድርጅት መሪነት በዓለም አቀፍና በየአገሮቹ የተለያዩ የቁጥጥር ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ የቁጥጥሩም ዓላማ ከትምባሆ ነፃ የሆነች ዓለምና ትውልድ መፍጠር ነው፡፡ ከትምባሆ ነፃ የሆነ ዓለም ለመፍጠር ግንዛቤ ማስጨበጥን አስመልክቶ ከሚከናወኑ ተግባራት ደግሞ በየዓመቱ የሚከበረው ትምባሆ የማይጨስበት ቀን ይገኝበታል፡፡

‹‹ትምባሆ ያጨሳሉ? እንግዲያውስ ለማቆም ቆራጥ ይሁኑ!›› በሚል መሪ ቃል፣ ‹‹የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን›› ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ተከብሯል፡፡ በዕለቱ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የትምባሆ ቁጥጥር ሥራ ዘርፈ ብዙ የተሟላ ስትራቴጂ የሚፈልግ ነው ወጥነትና ዘላቂነት ያለው ሥራም ይጠይቃል፡፡

ትምባሆን የሚጠቀሙ ዜጎች ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለውስብስብ የጤና ችግርና ሞት ተጋላጭ መሆናቸውን ያስታወሱት ዶ/ር ሊያ፣ ‹‹በቅርቡ የወጡት የጤና መረጃዎች ትምባሆ አጫሾች ከማያጨሱ ጋር ሲነፃፀሩ በኮቪድ-19 ሳቢያ ለሚመጣ የፅኑ ሕመም፣ ስቃይና ሞት ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን እንደሚሳዩ ተናግረዋል፡፡  

ትምባሆ ተጠቃሚ ዜጎች ማጨስ ለማቆም ለመወሰን ከዚህ የበለጠ ዕድል እንደሌለ በመገንዘብ የሚያጨሱ ከሆነ ለማቆም ቆራጥ እንዲሆኑ እንዲሁም ለማቆም ፈልገው ድጋፍ ከፈለጉ የባለሙያ ዕርዳታ እንዲጠይቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይህንን ለማገዝ ጤና ሚኒስቴር በጀመረው የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ዕቅድ ውስጥ የሱስ ማገገሚያ ማዕከላትን በአገር አቀፍ ደረጃ ማስፋፋት አጀንዳ መያዙን ገልጸው፣ የሙያ አገልግሎት ወይም ምክር የሚፈልጉ በሚኒስቴሩ 652 ነፃ ስልክ አገልግሎት ውስጥ የሙያ አገልግሎት ለመስጠት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ሊያ፣ በ2008 ዓ.ም. የትምባሆ ማጨስ ምጣኔን በተመለከተ በተካሄደው አገራዊ ጥናት ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ ታዳጊዎች፣ ከወጣቶችና ጎልማሶች መካከልም 29 ከመቶ ያህሉ ለደባል ጉዳት ተጋላጭ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ በተለይ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ መዝናኛ ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሠሩ ለደባል አጫሽነት እንደተጋለጡ አሳይቷል፡፡

በሆቴሎች፣ በሬስቶራንቶችና ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ላይ ያሉ ትምባሆ እንዳይጨስ በማድረግ፣ ትምባሆ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎችም በሥፍራዎቹ ትምባሆ ባለማጨስ ግዴታቸውን እንዲወጡ ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡

ማንኛውም ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ የሚገለገል ሰው ጤናውን ለመጠበቅ ሲል ከትምባሆ ማጨስ ጋር በተያያዘ የሕግ መተላለፍ ባየ ጊዜ የቤቱን ሥራ አስኪያጅ ወይም አስተናጋጅ ሕገወጥ ተግባርን እንዲያስቆምላቸው በመንገርና በመጠየቅ እንዲሁም ሕገወጥ ተግባሩ ካልቆመ ለሚመለከተው የሕግ አስከባሪ አካል ሪፖርት በማድረግ የቁጥጥሩ አካል እንዲሆኑም ጠይቀዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2011 ዓ.ም. ያፀደቀው የትምባሆ ምርቶች ቁጥጥር አዋጅ ከፀደቀ ሦስት ዓመታት እንዳለፈው፣ በእነዚህም ዓመታት በጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስተባባሪነት የትምባሆ ምርቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ለማስፈጸም በርካታ ተግባራት እንደተከናወኑም አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሔራን ገርባ፣ ትምባሆ በዓመት ወደ ስምንት ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት እንደሚቀጥፍ፣ ሞት ከሚያስከትሉ ስምንቱ ትልልቅ በሽታዎች የስድስቱ መንስዔ እንደሆነ፣ የትምባሆ ጭስ ወደ ሰባት ሺሕ ኬሚካሎች እንዳሉት፣ ከእነዚህም ውስጥ በጥቂቱ 70 ያህሉ ለተለያዩ የካንሰር ሕመሞች መንስዔ እንደሆኑ፣ 80 ከመቶ የሚሆነው ሞት አነስተኛ ገቢ ወይም በማደግ ላይ ባሉ ደሃ በሚባሉ አገሮች ላይ እንደሚከሰት ተናግረዋል፡፡

የትምባሆ ጉዳት ከጤና በሻገር ድህነትን የሚያመጣና ኢኮኖሚንም የሚጎዳ ነው፡፡  አካባቢንም ከመበከል ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው፣ ይህ ብቻ ሳይሆን የማያጨሱ ሰዎችም የሚያጨሱ ሰዎች ለሚለቁት ጭስ እንደሚጋለጡና በዚህም አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሰለባ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

አጫሾች የዕድሜቸውን 10 ዓመት በአማካይ እንደሚያጡ በማስታወስም  አጫሾች እንዲያቆሙ መሥራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በ2008 ዓ.ም. ከ15 ዓመት በላይ በሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ በተሠራው ጥናት የአጫሾች ቁጥር አምስት ከመቶ በላይ መሆኑን ያሳያል፡፡ ወደ 6.5 ሚሊዮን የሚጠጉ የማያጨሱ ሰዎች ደግሞ ለጭሱ ተጋላጭ ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር በፊት የነበሩ አዋጅ 66 እና ሌሎች ሕጎች ሲታዩ ትምባሆን በአግባቡ ለመቆጣጠር የማያስችሉ ስለሆነ፣ መንግሥትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ ቁርጠኝነት ወስደው የ2011ዱ አዋጅ ጠንካራ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ይህም አዋጅ ፀድቆ የወጣው ጥር 2011 ዓ.ም. መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡

በተጠቀሰውም አዋጅ ውስጥ ከአንቀጽ 46 እስከ 52፣ አንቀጽ 57 እንዲሁም ከአንቀጽ 61 እስከ አንቀጽ 67 ድረስ ያሉት ድንጋጌዎች በጣም ጥሩ መሆናቸውን፣ በአዋጁ ከተሸፈኑት መካከል ማንኛውም ሰው ያለ ፈቃድ ትምባሆ ማምረት፣ ማከፋፈልና ማስመጣትም እንደማይችል፣ ለሥራና ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ቦታዎች ከትምባሆ ነፃ እንዲሆኑ እንደሚደነግግ፣ 21 ዓመት ላልሞላቸው መሸጥና እንዲሸጥ ማድረግ፣ ልዩ ጣዕም ያላቸው ትምባሆዎች ሽሻን ጨምሮ ኤሌክትሮኒክ ሲጋሬት መከልከላቸውን፣ ከዚህም ጎን የትምባሆ ፓኬጅ 70 ከመቶ ያህሉ ሥዕላዊ በሆነ የጤና ማስጠንቀቂያ እንዲሸፈን መደረጉን ወ/ሪት ሔራን ተናግረዋል፡፡

ሕጉን ለማስፈጸም ሁለት መመርያዎች ወጥተው ተግባራዊ የተደረጉ ሲሆን፣ ሕገወጥ የትምባሆ ንግድን ለመከላከል ፕሮቶኮል ተዘጋጅቶም እንደ ሕግ ተደርጎ እንዲፀድቅ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መላኩን አስታውሰዋል፡፡ የታክስ ሕጉም ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡ በዚህም የተነሳ የትምባሆ ዋጋ በፊት ከነበረው ጨምሯል፡፡  

በአሁኑ ጊዜ በስድስት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ትምባሆ ማጨስን የሚቃወም እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በቀሩትም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡ ሥራው በአንድ የመንግሥት ተቋም ብቻ የሚሠራ ባለመሆኑም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ አሳስበዋል፡፡

ትምባሆን ለመቆጣጠር ከተጠቀሱት ተግዳሮቶች መካከል ክልሎች ትምባሆን በሚመለከት ሕግ አለማውጣታቸው አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ተግዳሮት ደግሞ የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች ኮንትሮባንድን እንከላከላለን በማለት ትምባሆን የማስተዋወቅ ሥራ ማከናወናቸውና በባለሥልጣኑ ሥራ ላይ ጣልቃ የመግባት እንቅስቃሴ ማሳየታቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ሕገወጥ ምርትን መከላከልና ተጠያቂ ከማድረግ አንፃር ክፍተት መፈጠሩን እንዲሁም ከፍትሕ፣ ከተቆጣጣሪና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ አለመንቀሳቀስና አለመናበብ ችግር መኖሩን፣ ጠንካራና ሰፋ ያለ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አለመሠራቱን  ገልጸው፣ በአጠቃላይ ሕጉን በአግባቡ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ መሥራችና ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ በቀለ፣ ተቋማቸው ካንሰርና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችን አስቀድሞ ለመከላከል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ፣ በሥራ ላይ ካዋላቸው ሰባት ፕሮጀክቶች መካከልም ሦስቱ ለካንሰርና ለሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ዋና አጋላጭ ምክንያት በሆነው ትምባሆ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ የትምባሆን ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች አስቀድሞ ለመከላከል ይቻል ዘንድ የግንዛቤ ማስጨበጫና የሕግ ማዕቀፎች እንዲኖሩት ከማስቻል አንስቶ በሳምባ ካንሰር ላይ ተገቢ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሠረት በአራት ክልሎች እየተተገበረ ያለው የሳምባ ካንሰር ፕሮጀክት አባል የሆነው የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ‹‹የቼስት ዩኒት››፣ 15 ክፍሎችን አድሶ ለተቋሙ ዘመናዊ መሣሪያዎችን ገዝቶ ማስረከቡን አስረድተዋል፡፡

ለዕድሳቱና ለመሣሪያዎቹ ግዥም ከ6.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዳደረገና ክፍሎቹ ለአገልግሎት ዝግጁ በመሆናቸው በቅርቡ ለማስመረቅ ዕቅድ መያዙን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡           

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...