Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለውበት መጠበቂያ የዋሉት ዕፀዋትና ቅመማ ቅመሞች

ለውበት መጠበቂያ የዋሉት ዕፀዋትና ቅመማ ቅመሞች

ቀን:

ዘመናዊ ሕክምና በአገር ውስጥ ከመጀመሩ በፊት ቀደምት አበው ከተለያዩ የዕፀዋት ዓይነት የባህል መድኃኒቶችንና የውበት መጠበቂያዎችን እያመረቱ ሲጠቀሙ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜም ቢሆን የባህል መድኃኒቶችን 80 በመቶ ያህል ሕዝብ እንደሚጠቀም ይነገራል፡፡ የውበት መጠበቂያዎችን የማምረቱ እንቅስቃሴም በዘመናዊ አገባብ የሚያከናውኑ ተቋማትም ወደ አደባባይ እየወጡ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ሆፕ ጄኔራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ይገኝበታል፡፡ ኩባንያው ከተለያዩ ዕፅዋትና ቅመማ ቅመሞች የፀጉር ቅባቶችና የሬት ሳሙና አምርቶ ለገበያ ያቀርባል፡፡

የፋብሪካው ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብቴ ዘውዴ እንደገለጹት፣ ኩባንያው ‹‹ወደ ተፈጥሮ እንመለስ›› በሚል መሪ ቃል እያመረተ የሚያወጣቸው ቅባትና ሳሙና ‹‹አፍሪ ኸርባል›› የሚል መጠሪያ አላቸው፡፡ ከነዚህም መካከል የፀጉር ዘይት/ቅባት የሚያመርተው ቀይና ነጭ ሽንኩርትን፣ ሮዝመሪን (የጥብስ ቅጠል)፣ አቮካዶን፣ ዝንጅብልን፣ ካሮትና ጉሎ ዘይትን (ካስተር ኦይል) በመጠቀም ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ጥቁር አዝሙድ፣ ዕርድ፣ የተፈጨ ቡና፣ ነጭ ሽንኩርትና ሞሪንጋን (ሽፈራው) በመጠቀም የፊት ሳሙና እንደሚያመርት፣ የማምረቱም ሥራ የሚከናወነው ኮተቤና ጀሞ አካባቢ በሚገኙ ሁለት የማምረቻ ማዕከላት ውስጥ እንደሆነ ነው ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡

ከቀይ ሽንኩርት የተመረተው ቅባት ፀጉርን ከመነቃቀልና ከመበጣጠስ፣ እንደሚያድን፣ ነጭ ሽንኩርት ደግሞ ፎረፎር እንዳይወጣ የመከላከል፣ ከተከሰተም የማጥፋት አቅም እንዳለው አቶ ሀብቴ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የተጠቀሱት ምርቶችን ጥራት የሚከታተልና የሚቆጣጠር እንዲሁም ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱ በዘርፉ በሳል ዕውቀትና ጠቃሚ ልምድ የቀሰሙ ባለሙያዎች እንዳሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸው፣ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ለመሆናቸው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት የዕውቅና ማረጋገጫና ምስክር ወረቀት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

ኩባንያው ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ሦስት ዓመት ሆኖታል፡፡ በእነዚህ ዓመታት በርካታ ተግዳሮቶች ተደቅነውበት ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ምርቶቹን ለኅብረተሰቡ ለማስተዋወቅ የተከናወነው ሥራ እልህ አስጨራሽና እጅግ አድካሚ መሆኑ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ከውጭ የሚገቡ የውበት መጠበቂያዎችን ለዘመናት ሲጠቀም የቆየው ኅብረተሰብ በአገር ውስጥ ምርት የሚያድርበትን ጥርጣሬ አስወግዶ እንዲጠቀም ማድረጉ በቀላሉ የሚታለፍ እንዳልሆነ ነው ያመለከቱት፡፡

ሌላው ችግር ገበያ ውስጥ ሰብሮ ለመግባት የታየው ፈተና ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ በትዕግሥትና በጥበብ ማለፍ እንደተቻለ፣ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት ምርቱ በሱፐር ማርኬቶችና በተለያዩ ሱቆች ተደርድረው የገዥ ያለህ እያሉ እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡

የምርቱ መጠን በወር ወይም በዓመት ቢሰላ ምን ያህል ይሆናል? ተብሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሀብቴ ሲመልሱም ‹‹መጠኑ ይሄን ያህል ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል›› ምክንያቱም ለቅባቱና ለሳሙናው ምርት የሚያገለግለው ግብዓት በቀላሉ አለመገኘት ነው፡፡ እንደውም ገበያ ላይ ከሚገኝበት ይልቅ የማይገኝበት ጊዜ ይበዛል፡፡ ሲመጣ ጠብቆና ተከታትሎ ለመግዛትም ያዳግታል፤›› ብለዋል፡፡

ከአቶ ሀብቴ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ወደዚህ ሥራ ለመግባት ያነሳሳቸው ከዕፀዋትና ከቅመማ ቅመሞች የውበት መጠበቂያን አምርቶ መጠቀሙ ከቤተሰብ ተያይዞ የመጣ ስለሆነ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ በውስጣቸው አድሮ አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ለመድረስ እንደቻሉ ነው የገለጹት፡፡

ተቋሙ ‹‹አፍሪ ኸርባል›› ተብሎ የተሰየመበትም ምክንያት ኢትዮጵያ የብርቅዬ ዕፀዋት ዝርያዎች የሚገኝባት አገር መሆኗን፣ እንዲሁም በእነዚህ ዝርያዎች የተመረተውንም ምርት በቅድሚያ በአፍሪካ ከዚያም በዓለም ገበያዎች ውስጥ የማስገባት ራዕይ ያነገበ ኩባንያ መሆኑን ለማሳወቅ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...