Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹70 ከመቶ ተላላፊ በሽታዎች 30 በመቶ ወረርሽኞች የሚነሱት በደን ጭፍጨፋ አማካይነት ነው›› መለሰ ማሪዮ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር

ብዝኃ ሕይወት ለሰው ልጅ የኑሮ ዋስትና እንዲሁም የምግብ፣ የመጠለያ፣ የውኃ፣ የልብስና የመድኃኒት ምንጭ ነው፡፡ እነዚህ ሀብቶች ለግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ግብዓትነት ከሚሰጡት አገልግሎት ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥን የማቃለል፣ ቆሻሻና በካይ ቁሶችን የማበስበስ፣ የአየርና የውኃን ንጽህና የመጠበቅ ተግባራትን በማከናወን የሰው ልጅ የመኖርያ አካባቢን ጤናማና ምቹ እንዳይሆን የሚያደርግ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሆኖም የሰው ልጅ የአካባቢ ጥበቃን ሳያገናዝብ በሚያደርጋቸው ተግባራት ምክንያት የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የድርቅና የምድረ በዳነት መስፋፋትና የብዝኃ ሕይወት ሀብቶች በከፍተኛ ፍጥነት መመናመንና መጥፋት ተጋርጦባቸዋል፡፡ በምድሪቱ በብዛት የሚታየው የአመራረትና የተመረተውን የመጠቀም ሒደት የተፈጥሮ ሀብትን የሚያወድም፣ ብዝኃ ሕይወትን የሚያመነምን በአጠቃላይ የተፈጥሮ አካባቢን የሚጎዳ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መለሰ ማርዮ (ዶ/ር) 20ኛውን ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት መታሰቢያ ቀንን ምክንያት በማድረግ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ብዝኃ ሕይወትን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ጋር ያካሄዱትን ቃለ ምልልስ ታደሰ ገብረማርያም እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡

ጥያቄ፡- የዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ቀን እንዴት ታስቦ እንዲውል ተደረገ? ዓላማውስ ምንድነው?

ዶ/ር መለሰ፡– ከ1984 ዓ.ም. በፊት የነበረው የብዝኃ ሕይወት ሀብት አጠቃላይ የዓለም ሀብት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ ከተጠቀሰው ዘመን ጀምሮ ግን  አገሮች የየራሳቸው ሉዓላዊ መብት በራሳቸው የብዝኃ ሕይወት ሀብት ላይ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም የተደረገው በስምምነት ሲሆን፣ ስምምነቱም የተደረገው ናይሮቢ ኬንያ በተካሄደው ስብሰባ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የዘንድሮ ቀን ታስቦ የሚውለው ‹‹እኛ ለተፈጥሮ የመፍትሔ አካል ነን›› በሚል መሪ ቃል ነው፡፡ ዓላማውም ብዝኃ ሕይወት ያለበትን ሁኔታ ለማሳወቅ፣ ግንዛቤ ለመፍጠርና መንግሥት ለብዝኃ ሕይወት ትኩረት እንዲሰጥ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ጥሩና ጠቃሚ ልምዶችን ለማስፋት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ከሚል እምነት ነው፡፡

ጥያቄ፡- ‹‹እኛ ለተፈጥሮ የመፍትሔ አካል ነን›› የሚለው መሪ ቃል ለመፍትሔው የሁሉንም ርብርብ ቢጠይቅም፣ በተለይ የትኛው የኅብረተሰብ ክፍል ነው በይበልጥ የመፍትሔው አካል የሚሆነው?

ዶ/ር መለሰ፡በመጀመርያ የደን ጭፍጨፋ፣ የውኃና የምግብ ዋስትና ችግሮች እንዳሉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ 70 ከመቶ ያህሉ ተላላፊ በሽታዎች እንዲሁም 30 በመቶ የሚሆኑት ወረርሽኞች የሚከሰቱት በደን ጭፍጨፋ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አሁን ካለው የምግብና የውኃ ፍላጎት አንፃር በ2022 ዓ.ም. እንደ ቅደም ተከተላቸው 50 እና 30 በመቶ መጨመር እንዳለበት ያመለክታል፡፡ የሥነ ምኅዳር መመናመንና የአየር ለውጥ ችግሮችም እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህም ማለት ብክለትን አየር ላይ፣ ውኃና አፈር ውስጥ መልቀቅም ሳይጠቀስ የማይታለፍ ችግር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ቀድሞ የነበሩ 80 ከመቶ የሚሆኑት አገር በቀል የአዝርዕት ዝርያዎች መውደማቸው መረሳት የለበትም፡፡ ወራሪ መጤ ዝርያዎችም (ፒሮሶፒስ፣ እምቦጭ አረም፡ ፓርቲኒየም፣ ስትራይጋና የወፍ ቆሎ የመሳሰሉት) በብዝኃ ሕይወት ሀብቶች ላይ የኑሮ አካባቢያቸውን በመሻማትና ተፈጥሮአዊ ይዘትን በመቀየር ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው፡፡ በተጠቀሱት ችግሮች የመፍትሔ አካል መሆን ያለባቸው በመጀመርያ ሁሉም ዜጎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የብዝኃ ሕይወት ተቆርቋሪዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙኃን ናቸው፡፡ መፍትሔ ሊያበጁ የሚችሉትም ከፍ ብሎ በዝርዝር በተጠቀሱት ችግሮች ለዓለም ማኅበረሰብ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በማከናወን፣ ሥርዓተ ምኅዳር እንዲጋገግሙ በማድረግ፣ ልዩ ልዩ የዛፍ ችግኞችን በመትከል፣ የሳይንሳዊ ምርምር ግኝቶችን ሥራ ላይ በማዋል፣ ፓርኮችንና ጥብቅ አካባቢዎችን በመንከባከብ፣ አረንጓዴ አሻራ የተባለውን ንቅናቄ በማጠናከር ነው፡፡

ጥያቄ፡- ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ተላላፊ በሽታዎችንና ወረርሽኞችን አስመልክተው ያነሷቸውን ችግሮች አፍታትተው ቢያስረዱን?

ዶ/ር መለሰ፡በደን ጭፍጨፋ ሳቢያ ከፍ ብሎ የተጠቀሱት ችግሮች እንደሚከሰቱ ገልጫለሁ፡፡ በተለይ ወረርሽኙ ቫይረስ በሚል ተህዋስያን የሚሠራጭ መሆን መታወቅ ይኖርበታል፡፡  ይህም የሚሆነው በጭፍጨፋው ምክንያት ደን ውስጥ የነበሩት እንስሳት በዋነኛነት ሰው ወዳለበት (አግሮ ፎርስትራ) ወይም ወደ ዛፍ ጥላ ስር ቀረብ ይላሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ሰው ራሱ ደግሞ ቁጥሩ እየጨመረ ሲመጣ ወደ እንስሳቱ ዘንድ መጠጋቱ አይቀርም፡፡ ይህም የሚሆነው የእርሻ ማሳውን እያሰፋውና እየገፋው ሲሄድ ከእንስሳት ጋር ንክኪ መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ አድርገን የምንወስደው ማሌዥያ በተባለ አገር የሆነውን ክስተት ነው፡፡ በዚህ አገር በአንድ ወቅት በጣም አደገኛ የሆነ ‹‹የኒን ቫይረስ›› የሚባል ወረርሽኝ ተከሰተ፡፡ የተከሰተውም በአካባቢው ከነበረው ጥቅጥቅ ደን ሲሆን የመከሰቱም መንስዔ ጥቅጥቅ ደኑ በመጨፍጨፉ የተነሳ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የሌሊት ወፎቹ ወደ እርሻው ማሳ በረሩና አረፉ፡፡ የእርሻውን ማሳ ለማስፋት በተደረገውም እንቅስቃሴ ውስጥ ወፎቹ በአቅራቢያው ካሉት አሳማዎች ዘንድ ተጠግተው የአሳማዎችን ምግብ መበከልና ማተራመሱን ተያያዙት፡፡ ይህ ዓይነቱንም ምግብ የበሉት አሳማዎች በውስጣቸው ቫይረስ ተሠራጨ፡፡ ሰውም የአሳማዎችን ሥጋ መብላት እንደጀመረ በቫይረሱ ተጠቃ፣ ለወረርሽኙም ተዳረገ፡፡

ጥያቄ፡- ቀደም ሲል የተጠቀሱትና ጠፍተዋል የተባሉ የዕፀዋት ወይም የአዝርዕት ዝርያዎች  እንደጠፉ ቀሩ ወይስ ለዘር ያህል እንኳን ተርፈዋል?

ዶ/ር መለሰ፡ከዛሬ 45 ዓመት በፊት የነበሩና አሁን የጠፉ የዕፀዋት ዝርያዎች በኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ጂን ባንክ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የምርምር ተቋማት ከባንኩ እየወሰዱ በማብዛት ለተጠቃሚው እንዲደርስ እያደረጉ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ሰበብ ነባር ዛፎች እየተጨፈጨፉና እየወደሙ ናቸው፡፡ ይህንን ተግባር ለማስቆም ምን እያደረጋችሁ ነው?

ዶ/ር መለሰ፡በተጠቀሰው ሰበብ ምክንያት ጭፍጨፋና ውድመት መካሄዱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በተለይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ክፍሎች ቀደም ሲል የነበሩት ሹማምንት አላስፈላጊ ከሆነ የሥልጣን አጠቃቀም ጋር ተያይዞ  ነባር ዛፎችን ሊተካ በማይችል አኳኋን ጨፍጭፈዋቸዋል፡፡ አሁን ግን ይህ ዓይነቱ ጭፍጨፋ ጋብ ያለ ይመስላል፡፡ የኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ከእኛ ጋር አብሮ እየሠራ ነው፡፡ ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከታቸው የየክልሉ አካላትም ትብብር እያደረጉልን ነው፡፡

ጥያቄ፡- መንግሥት ለብዝኃ ሕይወት በተለይም የተራቆቱ አካባቢዎችን አረንጓዴ  ለማልበስ እያካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር መለሰ፡መንግሥት ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት እየጨመረ እንደሄደ ነው እኔ የማየው፡፡ ምክንያቱም በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የአረንጓዴ አሻራ (ግሪን ሌጋሲ) የማኖር እንቅስቃሴ መከናወኑ ለብዝኃ ሕይወት ተቆርቋሪ ወይም እንደ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ሆኜ ስመለከት እጅግ በጣም የሚያስደስትና የሚያረካ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ብዝኃ ሕይወት ስምምነት ላይ አረንጓዴ አሻራን በመተግበር ላይ የመንግሥትን ቁርጠኝነት እኛና ሌሎችም አንዳንድ አውሮፓውያን አድንቀውታል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ በአርአያነት፣ በመልካም ተሞክሮነትና በምሳሌነት እንዲታይ ተደርጓል፡፡ በዚህ መልኩ ባለፉት ዓመታት በተካሄደው ዘመቻ ዘጠኝ ቢሊዮን፣ በዚህ ዓመት ደግሞ ስድስት ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ተከላ 20 ቢሊዮን እስከሚደርስ ድረስ እንደሚቀጥል ነው፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...