Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበተሽከርካሪ አደጋ መንስዔዎች ላይ የተጣለው ቅጣት ተመጣጣኝ አይደለም ተባለ

በተሽከርካሪ አደጋ መንስዔዎች ላይ የተጣለው ቅጣት ተመጣጣኝ አይደለም ተባለ

ቀን:

ከ35,000 በላይ አሽከርካሪዎች ተቀጥተዋል

በዓለም በየዓመቱ 1.35 ሚሊዮን ሕዝብ በትራፊክ አደጋ ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጋል፡፡ ይህም የሕዝብ መጠን የፕራግና ሳንቲያጎ ከተሞችን ያህል ሕዝብ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በየ25 ሰከንድ አምስት ሰዎች በዚሁ አደጋ ሕይወታቸው ይቀጠፋል፡፡ ይህም በመሆኑ 93 ከመቶ ያህሉ የሞት አደጋ የሚከሰተው መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ ሲሆን ከዚህ አኳያ በተጠቀሱት አገሮች ከአሥር ሰዎች ዘጠኙ እንደሚሞቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የአብዛኞቹ አገሮች ዓመታዊ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) ሦስት ከመቶ ያህሉን ለወጪ ይዳርጋል፡፡ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ 15 ሚሊዮን ሕዝብ በትራፊክ አደጋ ይሞታል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ይህም ሆኖ ግን የትራፊክ አደጋን መከላከል እንደሚቻል፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚከሰቱት አደጋዎች መንስዔዎቻቸው ብዙ ቢሆኑም፣ ቁልፍ የሆነ ዋና ዋና መንስኤዎች ግን ከስምንት እንደማይበልጡ ነው መረጃዎቹ ያመላከቱት፡፡

የከሉምበርግ ኢንሼቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ሕግ ማስከበር አስተባባሪ አቶ ቶሎሳ ገዳ እንደገለጹት፣ ዋነኞቹ መንስዔዎች በፍጥነትና ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የአደጋ መከላከያ ቀበቶ (ሴፍቲ ቤልት) አለመጠቀም፣ ተሽከርካሪ ውስጥ ሕፃናትን በአግባቡ አለማስቀመጥ፣ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ሔልመንት አለማድረግ፣ እያሽከረከሩ በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ (ሞባይል) መነጋገርና የትራፊክ መብራትን መጣስ የመሳሰሉ ይገኙባቸዋል፡፡

የከሉምበር ኢንሼቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ አጋር የሆነው ቫይታል ስትራቴጂክ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር የመንገድ ደኅንነትን በተመለከተ ለጋዜጠኞች ግንቦት 10 እና ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው ሥልጠና ላይ አቶ ቶሎሳ እንዳብራሩት፣ ከእነዚሁ ቁልፍ ከሆኑ መንስዔዎች መካከል በአንዳንዶቹ ላይ የኢትዮጵያ ሕግ የጣለው ቅጣት ሚዛኑ ያጋደለ ወይም ያልተመጠጠነ ነው፡፡

በዚህም መሠረት በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር የሚያሽከረክርና ከተጠቀሰው የፍጥነት መጠን ዝቅ አድርጎ የሚያሽከረክር ላይ የተጣለው ቅጣት ተመሳሳይ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ከፍተኛ የፍጥነት መጠን የሚያሽከረክረው ግለሰብ የሚያስከትለው የትራፊክ ጉዳት ከባድ መሆኑ እየታወቀ፣ የፍጥነት መጠኑን ዝቅ አድርጎ ከሚያሽከረክረው ጋር እኩል መቀጣታቸው አግባብነት እንደሌለው፣ ቅጣቱ በአጠቃላይ የፍጥነት ወሰንን ባለፈው ልክ የተቀመጠ አለመሆኑንም እንደሚያሳይ ነው የተናገሩት፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የጤና ማበልፀግ ኦፊሰር (መኮንን)፣ አቶ ዋስይሁን በላይ፣ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ የሆነውን የመንገድ ደኅንነት በተመለከተ በሰጡት ማብራርያ የአንድ ተሽከርካሪ ፍጥነት መጠን በሰዓት 30 ኪሎ ሜትር እንዲሆን የዓለም የጤና ድርጅት ያቀረበውን ፕሮፖዛል የአባል አገሮች ፖሊሲ አውጪዎች ሥራ ላይ ሊያውሉ እንደሚገባ ገልጸው፣ በተጠቀሰው ፍጥነት ማሽከርከር ተጋላጭ የሆኑ እግረኞችን፣ ብስክሌቶችን፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞችን ከአደጋው ሊከላከልላቸው እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

የዓለም አጀንዳ የሆነው 2022 ዓ.ም. እና የተባበሩት መንግሥታት ሁለተኛው የአሥር ዓመቱ የመንገድ ደኅንነት ፕላን፣ የመንገድ ደኅንነት በዘላቂ የልማት ግቦች 3.6 እና 11.2 ሥር መካተቱን፣ የ2022 ዓ.ም. አጀንዳ በዓለም ውስጥ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን የሞት መጠን 50 በመቶ ወይም ወደ 650,000 ዝቅ ለማድረግ ማቀዱንም ነው የጠቆሙት፡፡

ከመኮንኑ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው ኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ከ10,000 ሰዎች መካከል 34.4 ሰዎቸ ላይ ይደርስ የነበረውን የሞት መጠን በ2022 ዓ.ም. ወደ አሥር ዝቅ ለማድረግ  ግብ አስቀምጣ በመንቀሳቀስ ላይ ነች የሮድ ሴፍቲ አፍሪካ ቫይቷል ስትራቴጂስ ምክትል ዳይሬክተር ዳንኤል ሞላ (ኢንጂነር) የትራፊክ አደጋን ለመከላከል እንዲያስችል የሚሰጠው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በሕግ ማስከበር መታገዝ አለበት ብለዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በፍጥነትና በተለይ ጠጥቶ ማሽከርከር ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባት ሥልጠና ለትራፊክ ፖሊሶችና ለመንገድ ዲዛይን ባለሙያዎች መሰጠቱን፣ ሥልጠናውንም የተሳተፉት ፖሊሶች ጠንካራና አስተማሪ የሆኑ ቁጥጥር በማካሄዳቸው መጠነኛ መሻሻሎች መታየታቸውን አመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጄሬኛ ሄርጳ (ኢንጂነር) ‹‹ሰው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመንቀሳቀስ ገንዘብ ሊያወጣ፣ ጉልበቱን ሊያደክም ይችላል፡፡ ነገር ግን ደሙንና ሕይወቱን ማጣት የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ የመንገድ ደኅንነት ሁኔታ ሲነሳ በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል፣ እነርሱም ከ2009 ዓ.ም. በፊት እና በኋላ እንደሆነ፣ ከዚህ አንፃር ከ2009 ዓ.ም. በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የነበረው የሞት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡

ይህም መረጃ ሲተነተን በየዓመቱ በሰባት በመቶ ነው እያደገ የነበረው ከዚያ በኋላ በጥቂቱ እንደቀነሰ በተለይ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም አደጋው ወደ 18 በመቶ እንደቀነሰ አስረድተዋል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት በዋናነት ከመንገድ ትራፊክ አደጋ እየጨመረ ነው ይባል እንጂ ግልጽ አረዳድ እንዳልነበር፣ በዋናነት ትኩረት ይደረግ የነበረው በአደጋ ላይ እንጂ ስትራቴጂካዊ ዕይታ እንዳልነበረው ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ የአሽከርካሪዎች ስህተት ነው ተብሎ እንደሚደመደም፣ እንደማይገመገምም፣ በማሳዘን ላይ ያተኮረ እንደነበር፣ በቂ አደረጃጀትና አቅምም እንዳልነበረውም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ተቋማዊ አደረጃጀት በመፈጠሩ ባለሙያዎች ተቀጥረው መረጃ መተንተንን እንደተያያዙት፣ ስትራቴጂ እንደተዘጋጀ፣ የእግረኛን መሠረተ ልማት የማሻሻል ሥራ እንደተጀመረ፣ ለእግረኛ ሞት ምክንያት የሆኑ ጠጥቶ ማሽከርከርና ፍጥነት የመሳሰሉት ላይ ቁጥጥርና ክትትል መካሄድ እንደተጀመረ፣ መንገዶችን የማሻሻል ሥራ መከናወኑ እንደቀጠለ፣ ከመንገድ ሥራ ደኅንነት ጋር ተያያዥነት ካላቸው አካላት ጋር በቅንጅት መንቀሳቀሱ እንደቀጠለ ከዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አካሉ አሰፋ፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙ አሽከርካሪዎች መካከል ከ2010 ዓ.ም. እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ከ35,000 በላይ የሚሆኑት የተመደበውን የፍጥነት ወሰን ተላልፈው በመገኘታቸው ተቀጥተዋል፡፡

የመንገዱ ዲዛይን የሚያስገድድ እስካልሆነ ድረስ የከተማዋ የተሽከርካሪ ፍጥነት በሰዓት ከ50 ኪሎ ሜትር በታች መሆን እንዳለበት፣ በዚህም መሠረት አንድ ተሽከርካሪ በተመደበለት የፍጥነት ልክ ካሽከረከረ በእግረኛ ላይ የሚደርሰውን የሞት አደጋ 20 በመቶ ያህል እንደሚቀንስ፣ ነገር ግን ከተመደበው ፍጥነት በላይ በሰዓት አንድ ኪሎ ሜትር እንኳን ቢጨምር የሞቱን አደጋ በአምስት በመቶ ከፍ እንደሚያደርሰው በጥናት መረጋገጡንም አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...