Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዓለምን ሕዝብ ቁጥር የሚስተካከል ችግኝ ለመትከል ዘመቻ ተጀመረ

የዓለምን ሕዝብ ቁጥር የሚስተካከል ችግኝ ለመትከል ዘመቻ ተጀመረ

ቀን:

ችግኝ ተከላው ጎረቤት አገሮችንም ያካተተ መሆኑ ተጠቁሟል

ከ2011 ዓ.ም. ክረምት ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኝ ተከላ፣ ቀጣይ በሆነው በዘንድሮው ዝግጅት የዓለምን ሕዝብ ቁጥር የሚስተካከል ሰባት ቢሊዮን ችግኞችን በአገር ውስጥና በጎረቤት አገሮች ለመትከል እንዲቻል ዝግጅት መደረጉ ተነገረ፡፡ ይኼም በቀጣይ ሦስት ወራት የሚከወን ይሆናል ተብሏል፡፡

ማክሰኞ ግንቦት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን፣ የክልል ፕሬዚዳንቶችና አመራሮች፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች አመራሮች፣ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይፋ የተደረገው የቀጣይ ክረምት ወቅት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር፣ ከኢትዮጵያ አልፎ በአምስት የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮችም የሚከወን መሆኑ ተነግሯል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህም መሠረት ስድስት ቢሊዮን ችግኞች በኢትዮጵያ የሚተከሉ ሲሆን፣ አንድ ቢሊዮን ችግኞች ደግሞ በደቡብ ሱዳን፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በጂቡቲና በኤርትራ በፍላጎታቸው መጠን ተልከው ይተከላሉ ተብሏል፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ‹‹ችግኝ ተከላው የፖለቲካ ሳይሆን በዘላቂነት ጥቅም የሚያስገኝ ነው፤›› በማለት፣ ከአንድ ወር በታች ለቀረው ምርጫ ስለማይደርስም ለምርጫው ታስቦ የተደረገ ስላልሆነ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ተሳትፎ እንዲያደርግበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. አራት ቢሊዮን፣ በ2012 ዓ.ም. ደግሞ አምስት ቢሊዮን በድምሩ ዘጠኝ ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል በማለት በመድረኩ ሪፖርት ያቀረቡት የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን፣ ለአረንጓዴ አሻራ መነሻ የሆነው ምክንያት በዓለም እየጨመረ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥና የሙቀት መጠን መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ‹‹በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ በየዓመቱ አሥር በመቶ የሚሆነውን ምርቷን ታጣለች፣ ይኼም ከ35 እስከ 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል 20 ሚሊዮን ሕዝብ፣ በ2012 ዓ.ም. የችግኝ ተከላ ወቅት ደግሞ 23 ሚሊዮን ሕዝብ እንደ ተሳተፈ በማሳወቅ፣ በዘንድሮ የችግኝ ተከላ ደግሞ 25 ሚሊዮን ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ባለው መረጃ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተተከሉ ዘጠኝ ቢሊዮን ችግኞች መካከል የፀደቁት ምጣኔ 88 በመቶ እንደሆነ በማብራሪያቸው የገለጹት አቶ ኡመር፣ በዘንድሮው የችግኝ ተከላ ወቅት ካለፉት ሁለት የችግኝ ተከላ ዘመቻዎች በመማር የችግኝ ማፍላትና እንክብካቤ፣ እንዲሁም የተከላና እንክብካቤ ሥራዎችን የሚመሩ ማንዋሎችና መመርያዎች ተዘጋጅተው በሁሉም ደረጃ ላሉ አስተዳደሮች መዳረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለጎረቤት አገሮች ለሚሠራጨው ችግኝ የሎጂስቲክስ ዝግጅት ተደርጎ መጠናቀቁንና በአንድ ወር ውስጥም ይኼንን ለማከናወን መታቀዱን አክለዋል፡፡ ለዘንድሮው መርሐ ግብር ችግኝ ለማፍላት 21,600 ኩንታል የችግኝ ዘር ቀርቦ ጥቅም ላይ መዋሉን፣ ከነ መጠባበቂያ ችግኞች 6.2 ቢሊዮን ችግኞች የሚተከሉበት 1.9 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

ነገር ግን ችግኞቹ የሚተከሉባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ካርታ ሊኖራቸው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ዘንድሮ በ900 ሚሊዮን ብር በጀት የሚከወነው አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ግማሹ ከመንግሥት፣ ቀሪው ደግሞ ከአጋሮች በሚገኝ ድጋፍ ይሸፈናል የተባለ ሲሆን፣ እሳቸው የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር መሪ ቃል ‹‹አረንጓዴነት ለጋራ ልማት›› የሚል እንዲሆን ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ደኖቿና በተያያዥም የአየር ፀባይዋ ስለተራቆተ፣ ‹‹ኢትዮጵያን እናልብስ›› የሚለውን በምክረ ሐሳብ ደረጃ አቅርበው ከተሰብሳቢዎች ድጋፍ በማግኘቱ የዘንድሮው መርሐ ግብር መሪ ቃል እሳቸው ያቀረቡት ስያሜ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...