Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከታማሚ ጎን የማይለዩ ሙያተኞች

ከታማሚ ጎን የማይለዩ ሙያተኞች

ቀን:

የጤና ሙያ በቀደመው ዘመን በተበታተነና ባልተደራጀ መልኩ በዘልማድ ወጌሻ፣ አዋላጅ፣ አዋቂና በሌሎች በተመሳሰሉ መጠሪያዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ይታወቅ ነበር፡፡ ከዚያም በዕርዳታ ድርጅቶች አማካይነትና ከዘመናዊ ሆስፒታል መደራጀት ጋር በተያያዘ የነርስ ሙያ (ነርሲንግ) ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ ቻለ፡፡

በአቶ ታፈሰ በቀለ የኢትዮጵያ ነርሶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አነጋገር፣ የነርሲንግ ሙያ ካሉት የጤና ባለሙያዎች ብቻውን ከግማሽ በላይ ሲሆን፣ የመሠረታዊ የጤና አገልግሎት አቅራቢና ኃላፊነት ወሳኝ በመሆን እያገለገለ ያለ ሙያ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሙያ ላይ የተሰማሩትም ከ85,000 በላይ እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡

ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. የዋለውን ዓለም አቀፍ የነርሶች ቀንን በማስመልከት፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ፣ ከሁለት ቀን በኋላ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ አቶ ታፈሰ እንደገለጹት፣ ነርሶች በየትኛውም የጤና ተቋም ያሉና ታማሚ አጠገብ የማይታጡ ናቸው፡፡

የሰላም ተምሳሌት፣ የአገልጋይነት እውነተኛ ምስክር መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከድንገተኛ፣ ተመላላሽ እና ተኝቶ ታካሚ፣ በአምቡላንስ ውስጥ ሕክምናና ክብካቤ በሁሉም ጤና ተቋም ክፍልና አገልግሎት በማማከር፣ ግንኙነት በማሳለጥና በማከም፣ በመንከባከብና የምክር አገልግሎት በመስጠት የሚደነቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲያስችል በቅድሚያ በወረርሽኙ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንደተሰጣቸው፣ በቀሰሙትም ሥልጠና መሠረት ማኅበረሰቡ በብዛት በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ የወረርሽኙ መተላለፊያ መንገዶችንና የመከላከያ ዘዴዎችን የሚጠቁም የማስገንዘቢያ ትምህርት በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አመልክተዋል፡፡

ብዙዎቹ ነርሶች በዲፕሎማ ደረጃ ላይ እንዳሉ፣ ከእነዚህም መካከል ለረዥም ጊዜ ላገለገሉ ነርሶች የስፔሻሊቲ ፕሮግራም እየተሰጠ መሆኑን፣ ከዚህ አንፃር ሁሉም ነርሶች ቢያንስ የመጀመርያ ዲግሪ እንዲይዙና በዚህም የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ እምነት እንዳላቸው ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም የሕክምና ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ወንድማገኝ ገዛኸኝ (ዶ/ር)፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተ ማግሥት በሐኪሞች ዘንድ ከፍተኛ መጉላላትና ተግዳሮቶች ተከስተውባቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ‹‹ነርሶቻችን ባይኖሩ ኖሮ ተግዳሮቶችንና መጉላላትን በመቋቋም አሁን ባለበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ያዳግታቸው ነበር፤›› ብለዋል፡፡

የኮሌጁ ምክትል ፕሮቮስት ሊዲያ ተፈራ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የሕክምና ትምህርቶች ግንባር ቀደም የሆነው የነርሶች ትምህርት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ትምህርቱ የዕድሜውን ያህል አድጓል ለማለት እንደማያስደፍር ከማብራሪያቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

በአገሪቱ ያሉ የመንግሥትን ሆስፒታሎች የዛሬ አሥርና 20 ዓመታት በፊት የነበራቸው ገጽታ ላይ እንዳልሆኑ፣ በዚህም የተነሳ ስፔሻላይዝድ እያደረጉ መምጣታቸውን መገንዘብና የነርሶችም ትምህርት አቅም ከዚሁ ገጽታ ጋር የተጣጣመ ሊሆን እንደሚገባ ነው ያመለከቱት፡፡

በጤና ሚኒስቴር የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክተር አሰግድ ሳሙኤል (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ብዙ ሐኪሞች ባላፈራችበት ወቅት ነርሶች ታካሚዎችን ርኅራኄና አክብሮት በተሞላበት መንፈስ እየተቀበሉ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር በሁለተኛው የጤና ዘርፍ ዕቅድ ብዙ ባለሙያዎችን ለማሳደግ መወጠኑንና በዲፕሎማ ደረጃ ላይ ላሉ ነርሶች የስፔሻሊቲ ፕሮግራም መጀመሩን ከዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...