Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆዎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢንፎርሜሽን አብዮት አሁን ለደረሰበት ዕድገት የኢንዱስትሪ አብዮት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ የኢንዱስትሪ አብዮት በዓለም በስፋት ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት የነበረው የግብርና ሥራ የዜጎች መተዳደሪያ ቢሆንም፣ የግብርናና ሌሎች የእጅ ሥራ ውጤቶች ለሰው ልጅ አሰልቺና አድካሚ በመሆናቸው አገሮች ወደ ኢንዱስትሪ መር ሥርዓት ገብተዋል፡፡

የመጓጓዣ፣ የኤሌክትሪክ አውታሮች ዝርጋታ በስፋት መገንባት ከጀመሩበት እ.ኤ.አ. ከ1770ዎቹ ወዲህ የተስፋፋው የኢንዱስትሪ አብዮት ለፈጠራ ቴክኖሎጂዎች በር የከፈተ ነበር፡፡ የእጅ ሥራዎች በፋብሪካዎች የተተኩበት፣ የእንፋሎት ባቡርና ኃይል፣ የጋዝ ብርሃንና ሲሚንቶ የማምረት ሒደት የኢንዱስትሪው አብዮት ውጤቶች ናቸው፡፡  

የዓለም ሕዝቦችን የአኗኗር፣ የሕይወት ዘይቤና ክህሎት ወደ አንድ ዕርምጃ ከፍ ያደረገው የኢንዱስትሪ አብዮት ኢትዮጵያንም ከ100 ዓመታት በፊት ጀምሮ በባቡር፣ በመንገድ፣ በመብራትና በስልክ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንድትሆን ያስቻለ ነው፡፡

የሲኒማ፣ የውኃ መስመር ዝርጋታ፣ የመኪናና ሌሎች የሰዎችን ሥራ ሊያቀሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት አብዝተው ከሚጠቀሱት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በመቀጠል የኢትዮጵያ መሪዎች የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን በማስገባት ረገድ ካስቆጠረችው ረዥም ዓመታት አንፃር አሁን ያለችበት የኢንዱስትሪ ዕድገት ወደኋላ የቀረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ አብዮቱን እንደ ሌሎች አገሮች ለማስቀጠል ብዙ ማነቆዎች እንዳሉ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ያስረዳሉ፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተዋንያንና የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች መጋቢት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረጉት ውይይት በዘርፉ ያለውን ተግዳሮትና መልካም አጋጣሚዎች ተነስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንዱትሪ ልማት ቢሮ አዘጋጅነት በተደረገው ውይይት ባለፉት ዓመታት የተሠሩ ሥራዎችና ተግዳሮቶችን የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው በሪፖርታቸው አቅርበዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት መንግሥት ለ2,476 አነስተኛ፣ ለ662 መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ እንዳደረገላቸው፣ 425 ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ እንደተሸጋገሩና 59 አምራች ኢንዱስትሪዎች የመሬት አቅርቦት ችግር እንደተፈታላቸው በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡

እንደ አቶ ኤፍሬም፣ በዘርፉ ብዙ ጥሩ ክንውኖች ቢደረጉም በመንግሥትና በአምራች ኢንዱስትሪው በኩል በርካታ ችግሮች ተስተውለዋል፡፡

ብቁና የሠለጠነ የአመራር ብቃት ችግር፣ ያልተናበበ አደረጃጀት፣ የሠለጠነ ብቁ የሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ አለመታገዝ፣ እንዲሁም ለችግሮች ያለው ምላሽ አሰጣጥ አናሳ መሆን ለዘርፉ ችግሮች ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ ተካተዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረት፣ የገቢ ምርቶችን ከመተካት አንፃርና በቅርቡ ደግሞ በማኅበራዊ አገልግሎቶች ተሳትፏቸው ጉልህ ሚና እንዳላቸው አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል፡፡ 

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ያሉትን ችግሮች የገለጹ ሲሆን፣ በተለይም በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ዜጎች ባለኢንዱስትሪዎች መካከል ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ አድልኦ አንስተዋል፡፡ በመንግሥት የሚደረገው ትብብር እንደሚለያይም ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ከውጭ አገሮች ዜጎች አምራች ኢንዱስትሪዎች በተለየና ባነሰ መልኩ ለአገር ውስጥ አምራቾች የሚደረገው ትብብር የአገሪቱን ዜጎች ከውድድር ውጪ ሊያደርግ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ባለሀብቶችን በጥንቃቄ ማየት አለበት ያሉት በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል አቶ ማርቆስ ታደሰ ናቸው፡፡ ለአገር ውስጥ አምራቾች የሚደረገውን ድጋፍ በአትኩሮት ማየት ቢቻል መልካም ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ከውጭ አገሮች የሚመጡ ዜጎች በቀላሉ መሬት ማግኘት እንደሚችሉ የገለጹት አቶ ማርቆስ፣ ለአገር ውስጥ ዜጎች ግን መሬት የማግኘት ሒደቱ እጅግ የተጓተተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለኢንዱስትሪ ውጤቶች ተገቢ ደረጃ አለመኖር፣ የላቦራቶሪ ደረጃዎችም ዘመናዊ ባለመሆናቸው በውጭ አገሮችና በአገር ውስጥ አምራቾች መካከል ያለውን ውድድር ከባድ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ በይበልጥ የተነሳው የዘርፉ ባለሀብቶች የሚሠሩበት መሬት የማግኘት ዕድል አናሳ መሆን ነው፡፡ ሒደቱም ረዘም ያለ ጊዜ የሚጠይቅ ነውም ተብሏል፡፡

የኢንዱስትሪው ዘርፍ በተፈለገው ልክ እንዳያድግ ካደረጉት ችግሮች ውስጥ የመሠረተ ልማት ችግሮች ዋነኛ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ የመንገድ፣ የመብራት፣ የውኃና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ችግሮች በዋነኛነት ማነቆ ናቸው ተብሏል፡፡ የባንክ ብድር የማግኘት ዕድልና ውጭ ምንዛሪ እጥረት ዘርፉን ችግር ላይ እየጣለ እንደሚገኝ፣ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች በዘርፉ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ሠራተኞቻቸውን የቀነሱና ድርጅት እስከ መዝጋት የደረሱ መኖራቸው ተገልጿል፡፡

አስመጪዎች ውጭ ምንዛሪ የማግኘታቸው ዕድል ከአምራቾች የተሻለ መሆኑን የጠቆሙት አስተያት ሰጪዎች፣ የአገር ውስጥ አምራቾች የሚበረታቱበትንና የሚታገዙበትን መንገድ ማሻሻል ይገባል ተብሏል፡፡

ምርት ለማምረት ከውጭ አገሮች የሚገቡ ግብዓቶች ላይ የጉምሩክ የዋጋ ተመን አስቸጋሪነት የተነሳ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ወደብ ላይ ተዘግቷል በማለትና መሰል ምክንያቶች በመዘርዘር መንግሥት እንዲወርስ የሚደረግበት አካሄድ አለ ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ የተገኙ የመንግሥት ኃላፊዎች በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዘርፉ ችግሮች ከመንግሥት በኩል ብቻ ሳይሆኑ ከአንዳንድ ባለሀብቶችም እንደሚመነጩ ተጠቁሟል፡፡

በተሰማሩበት መስክ በትክክለኛ መንገድ መታገል፣ የምርት ጥራት ደረጃ ከፍ ማድረግና በመንግሥት የሚደረገውን ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡

በመንግሥት በኩል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመሥራት ልምድ ማሻሻል፣ ጠንካራ የክትትልና የትብብር ሥራ ማከናወንና ሕግ የማስከበር ሥራው በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል ተነግሯል፡፡

ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለተሰማሩ ከ138 ሔክታር መሬት በላይ በከተማ አስተዳደሩ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዋነኝነት በሕገወጥ መልኩ የተያዙና ሳይለሙ የከረሙ ቦታዎችን በማስለቀቅ ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ ለዚሁ ተግባር እንደሚውሉ ተጠቁሟል፡፡

በዘርፉ በየደረጃው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባና በአምራች ኢንዱስትሪውና በመንግሥት መካከል የሚደረገው የውይይት መድረክ ቀጣይነት እንደሚኖረው ታውቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች