Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአየር ንብረት ለውጥ ሥጋት የሆነባት ድሬዳዋ

የአየር ንብረት ለውጥ ሥጋት የሆነባት ድሬዳዋ

ቀን:

በዕፀዋት ሀብቷ የምትጠቀስ ከተማ ነበረች፡፡ አትክልትና ፍራፍሬዎቿ ምግብነታቸው ብቻ ሳይሆን መስህብነታቸውም ይነገርላቸው ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ይህንን እንደቀድሞው ማስታወስ አይቻልም፡፡ ለአትክልትና ፍራፍሬዎቿ ሀብት መከታ የነበሩና የድሬዳዋ ከተማን ውበት ያላበሱ ዛፎችም ተመናምነዋል፡፡

አብዛኛው ነዋሪዎቿ በንግድ፣ በተለይ ደጋማው ክፍል ደግሞ በእርሻ የሚተዳደርበት ድሬዳዋ ከዚህ ቀደም እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በርካታ ዛፎች  ነበሩባት፡፡ በተለይም ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚዋሰነው ደጋማው ክፍል አገር በቀል በሆኑ የዛፍ ዝርያዎች የተከበበና የበዮ አዋሌ ወረዳም በጥድ፣ በዋንዛና በግራር ዝርያዎች የተሸፈነ እንደነበር የከተማ አስተዳደሩ የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን የደን ባለሙያ አቶ ማሙሽ ዘውዱ ያስታውሳሉ፡፡

ታችኛው የድሬዳዋ ክፍል ቆላማ ሲሆን፣ በግራር ዝርያዎች የተሸፈኑም ነበሩ፡፡  አቶ ማሙሽ እንዳስረዱት፣ አካባቢው ከዓመታት በፊት እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የደን ሽፋኑ የተሻለ ነበር፡፡ የተለያዩ ጥናቶችን ጠቅሰው እንዳሉትም የከተማው 32 በመቶ ያህል በደን የተሸፈነ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን የነበረው ሽፋን በአንድ ሦስተኛ ቀንሷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አሁናዊ የደን ሽፋን

በድሬዳዋና አካባቢዋ ያለው የደን ሽፋን 9.2 በመቶ መሆኑን ከሁለት ዓመት በፊት የተጠኑ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከእነዚህ የደን ሀብቶች ውስጥ ሰፊውን ቁጥር የሚይዘው በሳይንስ ስሙ ፕሮሶፒስ ጃኒቶሪያል (Prosopis Janitorial) ተብሎ የሚጠራው የዓረም ዝርያ ነው፡፡

ይህ የአረም ዝርያ በድሬዳዋና አካባቢዋ ካለው የደን ሽፋን ውስጥ 4.93 በመቶውን ይይዛል፡፡ ከዚህ ሥፍራ በተጨማሪም የአዋሽ በረሃማ አካባቢዎችን በስፋት ይዟል፡፡ በድሬዳዋ ካለው የደን ሽፋን ውስጥ አብዛኛውን ከያዘው የዓረም ዝርያ በተጨማሪ ቁጥቋጦዎችና ሌሎች የዛፍ ዝርያዎች ደግሞ 3.67 በመቶውን ይሸፍናሉ፡፡

ይህ ዝርያ ለአካባቢው ኅብረተሰብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ለአንዳንዶች መተዳደሪያም ነው፡፡ የመሬት መሸርሸርና የአየር ንብረት ለውጥን ከመቀነስ አንፃርም ጥቅም እንዳለው ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡

ነገር ግን ዝርያው ጥቅም እንዳለው ሁሉ የጎንዮሽ ጉዳቱ ከፍተኛ ስለሆነ  መንግሥት ዓረሙን ለማጥፋት እየሠራ ይገኛል፡፡ የዚህ የዓረም ዝርያው ከሌሎች የዛፍ ዓይነቶች በተለየ በቀላሉ የሚራባ ሲሆን፣ በአካባቢ ያሉ ዕፅዋቶች እንዳይበቅሉ ያደርጋል፡፡

እንስሳት ከተመገቡትም እስከ ሞት የሚያደርስ መሆኑንም አቶ ማሙሽ ይናገራሉ፡፡  

ለደን ሀብት መመናመን ምክንያቶቹ

የደን ሽፋን የመመናመን ዋነኛው ምክንያቱ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ መብዛት ለቤትና ለእርሻ መስፋፋት ተብሎ የዛፎች መጨፍጨፍ ከቀዳሚዎቹ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በዋነኝነት የመሬት አስተዳደር ሕግ አለመኖርም ለደኖች መመናመን ትልቁን ቦታ እንደሚይዝ አቶ ማሙሽ አስረድተዋል፡፡

ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የእርሻ፣ የግጦሽና የመኖሪያ ሥፍራ  በመስፋፋቱ የተከሰተው የደን መመናመን፣ ድሬዳዋን ለቀደመውም ሆነ ለሰሞነኛው ዝናብ ተጎጂ አድርጓታል፡፡

ከፍተኛ ዝናብ መዝነቡ እንደ ችግር የሚወሰድ አለመሆኑን፣ በዝናቡ ምክንያት የሚመጣውን ጎርፍ የሚቋቋም የደን ሀብት አለመኖሩ ችግሩን እንዳባባሰውም ተናግረዋል፡፡

ችግሮቹን ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን የደን ሀብቱ መልሶ እንዲያንሰራራ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታትም አካባቢው መልሶ እንዲያንሰራራ ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ ሥራ ቢከናወንም፣ የመሬት አስተዳደር ሕግ ባለመኖሩ ችግሮቹ እየተባባሱ መሆኑን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ የቱሪስት መስህቦች

የድሬዳዋ ዝቅተኛው ወይም ቆላማው ሥፍራ የግራር ዝርያዎች ያሉበት ሲሆን፣ ቦታውን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በአካባቢው ሚዳቋ፣ ቀበሮ፣ አጋዘንና ሌሎችም የዱር እንስሳት የሚገኙና ደን ሽፋኑም የተሻለ በመሆኑ ወደ ፓርክነት ለማሳደግ ከተማ አስተዳደሩ እየሠራ ይገኛል፡፡

ታችኛውን የድሬዳዋ ክፍል ወደ ፓርክነት ለመቀየር እየተሠራ ቢሆንም፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ በተወሰነ መልኩ ደኑን የመጨፍጨፍ ችግሮች መስተዋላቸው በደጋው ወይም በላይኛው የድሬዳዋ ክፍል ደግሞ ነባር የጥድ፣ የዋንዛ፣ የዝግባና ሌሎች አገር በቀል ዛፎች የሚገኙበት ነው፡፡

ነገር ግን ከዓመታት በፊት በከተማዋ ዙሪያ ከነበሩ ወንዞች የተወሰኑት ደርቀዋል፡፡ እንደ ባለሙያው፣ ከእነዚህ ወንዞች መካከል ለጋሐሬ ወንዝና ሌሎችም በደን መጨፍጨፍና በአየር ለውጥ ምክንያት ደርቀዋል፡፡ አሁን ላይ የድሬዳዋና አካባቢው የውኃ አቅርቦትም የከርሰ ምድር ውኃ ላይ ወድቋል፡፡

አቶ ማሙሽ እንደሚናገሩት፣ አሁን ላይ ወንዞች የነበሩ ቦታዎች ምልክታቸው ብቻ የቀረ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡም የከርሰ ምድርና ወራጅ ውኃ  እየተጠቀመ ይገኛል፡፡  

የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር መሠራትን ተንተርሶ እንደተመሠረተች የሚነገርለት የድሬዳዋ ከተማ፣ ልምላሜ ለብዙ ዓመታት በተረትና በትምህርት ማስተማሪያ መጻሕፍት ጭምር ሲነገትላት የኖረ ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ ይህንን መስህቧን እያጣች ነው፡፡

የባቡሩ ጉዞ መነሻና መዳረሻ ትዕይንት የድሬዳዋ እንስቶች ብርቱካን፣ ሎሚ፣ ትርንጎና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በሳጠራ ሞልተው በአናታቸው መሸከማቸው ጭምር እንደ መስህብ የሚገለጹም ነበር፡፡ ፍራፍሬ በመቸርቸር ኑሯቸውን የሚደጉሙም ብዙዎች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

ለእነዚህ ፍራፍሬዎች መገኘት ምክንያት የነበረው የደን ሽፋን መጠናከር ከሕዝብ ቁጥሩ አነስተኛ መሆን አስተዋጽኦ እንደነበረውም ይታሰባል፡፡ የደን ሽፋኑ መመናመኑ የዱር እንስሳቱ እንዲሸሹ አድርጓል፡፡

በ1970ዎቹና 1980ዎቹ አካባቢ የአማርኛ መማርያ መጽሐፍ ላይ የነበረው ‹‹ሽልንጌን›› የሚለውና በድሬዳዋ በባቡር መስመርና መዳረሻ አካባቢ በሳጣራ ውስጥ ብርቱካንና ሎሚ ይዛ የምትሸጥ እንስት ታሪክም የድሬዳዋን ውበትና መስህብነት በምናብ ያሳይ እንደነበር በዘመኑ የነበሩ ተማሪዎች ትውስታ ነው፡፡

አሁን ላይ ድሬዳዋ ላ ብርቱካን፣ ሎሚና ትርንጎ የሚነግዱንስቶችን አብዝቶ ማግኘት ብርቅ ከሆነ ሰንብቷል የሚሉት የአካባቢ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ በአካባቢው ላይ እየተመናመነ የመጣው የደን ሽፋን፣ የወንዝ መድረቅና መሰል ችግሮች ለድሬዳዋ መስህብ የነበረውን አካባቢያዊ የፍራፍሬ የንግድ መስተጋብር ከማጥፋቱ በተጨማሪ ከተማዋ በጎርፍና በመሬት መንሸራተት እንድትመታ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የመሬት መንሸራተትና ጎርፍ በተለያዩ ጊዜያት እየፈተኗትም ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ ተከስቶ የነበረው ከባድ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት በሺዎች የሚቆጠሩ እንዲፈናቀሉ፣ የሰው ሕይወት እንዲቀጠፍና ንብረት እንዲወድም አድርጓል፡፡ ሰሞኑንም የመሬት መንቀጥቀጥና ጎርፍ ገጥሟታል፡፡

የኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያ ማዕከል ከሚያዝያ 26 እስከ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚኖረውን ትንበያ አስመልክቶም፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ኬንያ ከፍተኛ ዝናብ እንደሚከሰት ገልጿል፡፡ ይህም በተለይ ከ200 ሚሊ ሜትር በላይ የሚለካ ከባድ ዝናብ በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በጅግጅጋና ደገሃቡር እንደሚበረታ አሳውቋል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ 515 ኪሎ ሜትር፣  ከጂቡቲ 315 ኪሎ ሜትር፣ ከሐረር 55 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘው ድሬዳዋ፣ የቆዳ ስፋቷ 128‚802 ሔክታር ነው፡፡ ከአጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ ውስጥ ሁለት በመቶውን የሚይዘው ከተማ ሲሆን፣ 98 በመቶው ደግሞ የገጠር መሬት ነው፡፡ 62 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በከተማ የሚኖር ሲሆን፣ 38 በመቶ ደግሞ በገጠራማ ክፍሎች ይገኛል፡፡ ድሬዳዋ አስተዳደር ዘጠኝ የከተማና 38 የገጠር ቀበሌዎች አሏት፡፡ የገጠር ቀበሌዎቹ በአራት ወረዳ (ክላስተር) ውስጥ 38 ቀበሌዎች የሚጠቃለሉ ናቸው፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ከአምስት ዓመት በፊት የነበረው የሕዝብ ብዛት 426‚080 ሲሆን፣ አሁን ላይ ከ600‚000 በላይ ሕዝብ ይኖራል ተብሎ እንደሚገመት ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ራሱን መመገብ ያልቻለ ሕዝብና አገር የሌሎች ተላላኪ ይሆናል›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ

በጀኔቫ በተካሄደ የዕርዳታ ማሰባሰቢያ መድረክ 21 አገሮች ለኢትዮጵያ ድጋፍ...

አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ሲታወሱ (ከ1932 እስከ 2016 ዓ.ም.)

በፋና ገብረሰንበትና ዮናስ ታሪኩ  ቅዳሜ ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም....

የሐረር ድምቀት

ሐረሪዎች ዓመታዊ ባህላዊ በዓላቸውን ሸዋሊድን ከሚያዝያ 8 ቀን ጀምሮ...

ኦቲዝም በደሃዎች ጓዳ

ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆችን እንደ ባህሪያቸው ተንከባክቦ ማሳደጉ እንኳን...