Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተመራቂ ሐኪሞች ሥራ አጥነት መፍትሔዎች እስከ ምን ድረስ?

የተመራቂ ሐኪሞች ሥራ አጥነት መፍትሔዎች እስከ ምን ድረስ?

ቀን:

ኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ አጥ ምጣኔው እያደገ መጥቷል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ከድህነት ለመላቀቅ እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ እንደ አንድ ዓብይ ተግዳሮት ይታያል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የተመራቂ ሐኪሞች ሥራ አጥነት ሲታከልበት ተግዳሮቱን በይበልጥ ያባብሰዋል፡፡ በቅርቡ በወጣው አኀዝ መሠረት የሥራ አጥ ሐኪሞች ቁጥር በአሁኑ ጊዜ ከአምስት ሺሕ በላይ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡

የዓለም አቀፍ የጤና ሥጋት ከሆነው የኮቪድ-19 ቫይረስና ኤችአይቪ ኤድስን ጨምሮ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በተንሰራፉበት፣ እንዲሁም የሕዝብ ቁጥሩ እየጨመረ በመጣበት ኢትዮጵያ ውስጥ ተመራቂ ሐኪሞች ሥራ አጥተው ለእንግልት ሲዳረጉ ማየት ለሰሚ እንቆቅልሽ ነው የሆነበት፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት ተመራቂ ሐኪሞች በተለያዩ የጤና ተቋማት ያለምንም ችግር እየተመደቡ አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ ምደባውንም የሚያካሂደው መንግሥት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መንግሥት ምደባውን አቁሟል፡፡ ክልሎችም ለዚህ የሚሆን በጀት የለንም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ያለው አማራጭ ተመራቂ ሐኪሞች የራሳቸውን የሥራ ዕድል መፍጠር የግድ እየሆነ መጥቷል፡፡

አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ለተጠቀሱት ችግሮች ዕልባት ለመስጠት ያስችላሉ ብለው ያመኑባቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች ብቅ፣ ብቅ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ የመፍትሔ ሐሳቦችን ካንፀባረቁትም መካከል ፕሪሳይስ ኮንሰልት ኢንተርናሽናል (ፕኮ ኢንተርናሽናል) የተባለ አገር በቀልና መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ይገኝበታል፡፡

በአቶ ሔኖክ ባያብል የፕሪሳይስ ኮንሰልት ኢንተርናሽናል የጤና ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አነጋገር፣ ለተመራቂ ሐኪሞች መንግሥት ከሚያደርገው ምደባ ባሻገር የግሉ ዘርፍም በጤናው መስክ በመሳተፍ በምደባው የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችል እንደነበር አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን ዘርፉ በዚህ ላይ ያለው ተሳትፎ 20 በመቶ ብቻ መሆኑ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ተሳትፎው በእጅጉ ደካማ መሆኑን ነው፡፡

ይህም ሊሆን የቻለው የጤናው ፖሊሲ ክፍተት በማሳየቱ ነው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ከመንግሥት የሚሰጥ ማበረታቻ እንደሌለ፣ መንግሥት ባወጣው ስታንዳርድ መሠረት የጤና ተቋም ለማቋቋምም የቦታ ጥበት መሰናክል መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የግል ጤና ተቋማት ለአገልግሎት የሚጠይቁት ክፍያ ደግሞ ከኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም ጋር ያልተመጣጠነ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዥታን መፍጠሩንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የተመራቂ ሐኪሞች ሥራ ማጣት ደግሞ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንደሆነ፣ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ በየዓመቱ የሚመረቁ የሐኪሞች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የሥራ አጥነቱን ድባብ በይበልጥ እንደሚያባብሰው በመገንዘብ ተቋማቸው ሦስት የመፍትሔ ሐሳቦችን ማመንጨቱን ገልጸዋል፡፡

አንደኛው የመፍትሔ ሐሳብ አንድ ተመራቂ ሐኪም ከቻለ ከከፍተኛ ሐኪም ጋር፣ ካልቻለ ደግሞ ብቻውን ልክ እንደ ጠበቃ አንድ ክፍል ቤት ተከራይቶ ‹‹ኦፊስ ፎር ሜዲካል ፕራክቲስ›› በማቋቋም ሆድ ቁርጠት፣ ትውከት፣ ቁርጥማት፣ ራስ ምታት ወዘተ የመሳሰሉ በሽታዎችን መመርመር ይሆናል፡፡ እንዲሁም የላቦሪቶሪ ምርመራ ለሚያስፈልጓቸው በሽታዎች በአቅራቢያው ወደሚገኘውና የተሟላ የላቦራቶሪ አገልግሎት መስጠት ወደሚችል ጤና ተቋም መላክ፣ ከተቋሙ በሚደርሰውም ውጤት መሠረት ለታካሚው መድኃኒቶችን ማዘዝና ታካሚው ክትትሉን እንዳያቋርጥ በመንገር አገልግሎት መስጠት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛው የመፍትሔ ሐሳብ ከዚህ ዓይነቱ ሕክምና ጋር የተያያዘ ሆኖ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ዲጂታል የጤና አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ በዚህም ሐኪሙ በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ ሐኪሞችም ሆነ የጤና ተቋማት ጋር መረጃዎችን በመለዋወጥም የሕክምና ምርመራውን በጋራ ለማካሄድ ማስቻል ነው፡፡

አቶ ሔኖክ የጠቆሙት ሦስተኛው መፍትሔ ደግሞ በሳምንት አንድ ቀን በሚውለው የገበያ ቀን በቫን (ተሽከርካሪ) የታገዘ ተንቀሳቃሽ የሕክምና አገልግሎት መስጠትን ይመለከታል፡፡ በዚህም የሚሰጠው አገልግሎት ከፍ ብሎ ከተጠቀሱት ሕመሞች ጋር የተያያዘ መሆን እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

እንደ አቶ ሔኖክ ማብራሪያ፣ አራተኛው የመፍትሔ ሐሳብ በየክፍላተ ከተማ የሚገኙ ጤና ጣቢያዎችን ከሰኞ እስከ ዓርብ እንዲሁም ቅዳሜና እሑድን በ40/60 መርህ መሠረት መጠቀም ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ከገቢው 40 በመቶ ለጤና ጣቢያው ይሆንና ቀሪው 60 በመቶ ለተመራቂ ሐኪሙ በማድረግ ነው፡፡ የጤና ጣቢያው ድርሻ 40 በመቶ ሊሆን የቻለው ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉት ቁሳቁሶችና ልዩ ልዩ የመጠቀሚያ ክፍሎች የጤና ጣቢያው ንብረት በመሆናቸው ነው፡፡ ጤና ጣቢያውን በግል ወይም በኅብረት ሆኖ መጠቀም እንደሚቻልም አቶ ሔኖክ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

አንዳንድ ወገኖች አንድ ተመራቂ ሐኪም ከከፍተኛ ሐኪም ጋር አብሮ ሳይሠራና በዚህም ልምድ ሳይቀምስ ብቻውን እንዴት አድርጎ ነው የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚችለው? የሚል ሥጋት ተጭሮባቸዋል፡፡ አቶ ሔኖክ ለሥጋቱ ምላሽ አላቸው፡፡ ‹‹ሥጋቱ አግባብነት ያለው ቢሆንም አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ተመራቂ ሐኪሞቹ ሰባት ዓመት የፈጀ የሙያ ሥልጠና ጨርሰው የተመረቁ፣ በዚህም ዕውቅና የተሰጣቸውና ሲኦሲም ያለፉ መሆናቸውን መዘንጋት የለበትም፤›› ብለው፣ መንግሥትም ቢሆን እንደተመረቁ ብቻቸውን ለመሥራት በሚያስችል መልኩ በየጤና ተቋማቱ እንደሚመድቧቸው አመልክተዋል፡፡

የፕኮ ኢንተርናሽናል የፖሊስ ኢኖቬሽን ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ቡሽራ፣ አማካሪው ድርጅት በ1998 ዓ.ም. እንደተቋቋመና ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር በመቀናጀት በጤና እና በግብርና፣ በፋይናንስ አገልግሎት ፖሊሲዎች ላይ ያጋጠሙ ማነቆዎችን የመለየት፣ ቅደም ተከተል የመስጠት ሥራ እንደሚያካሂድ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ጥናትና ምርምር ማድረግም፣ የሌሎችንም አገሮች መልካም ተሞክሮ በመውሰድና ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ የደረሰበትን አማራጭ የፖሊሲ ሐሳቦችን እንደሚያመነጭም አስረድተዋል፡፡

‹‹የሕዝብ ቁጥር እያደገና ልዩ ልዩ በሽታዎች በተንሰራፋበት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተመራቂ ሐኪሞች ሥራ ማጣት በእጅጉ አስደንጋጭና ተስፋ አስቆራጭ ክስተት ነው፤›› የሚሉት የኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኤሞን ብርሃኔ ናቸው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው የተመራቂ ሐኪሞች ቁጥር እየጨመረ እንደመምጣቱ ከዚሁ ጋር ተያያዥ የሆኑ የጤና ተቋማት፣ ወይም መሠረተ ልማቶች ባለመስፋፋታቸው መሆኑን አስረግጠው ይናገራሉ፡፡

ሌላው ምክንያት ደግሞ ሥራ አለመኖር ብቻ ሳይሆን፣ ለጤናው ዘርፍ የሚመደበው በጀት በቂ ካለመሆኑም በላይ ያለውንም ቢሆን በአግባቡ የመጠቀም ችግር፣ የጤናው ፖሊሲ ክፍተት፣ እንዲሁም ተመራቂዎች ሌሎች የሥራ ቦታዎችን እንዴት ማስተዳደር እንደሚችሉ አለማወቃቸውና መረጃም በማጣታቸው መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በኢትዮጵያ አንድ ሐኪም ለ20 ሺሕ ሰዎች ሲመደብ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ስታንዳርድ መሠረት ግን አንድ ሐኪም ለ10 ሺሕ ሰዎች ብቻ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት የሚገልጽ ስታንዳርድ ማስቀመጡን ከፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

ፕራሳይስ ኮንሰልት ኢንተርናሽናል ያመነጫቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች እንዴት እንደሚያዩት፣ በስልክ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ተግባር ይግዛው (ዶ/ር) ምላሻቸውን እንደሚከተለው ሰጥተዋል፡- ‹‹ጤና ሚኒስቴር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በተጠቀሱት ሐሳቦች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አካሂዷል፡፡ አንዳንድ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል፡፡ ከተቀመጡትም አቅጣጫዎች አንደኛው ኦፊስ ፎር ሜዲካል ፕራክቲስ የሚሠራው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሊሆን እንደሚገባ አስምሮበታል፡፡››

በጤና ጣቢያዎች በተጠቀሱት ቀናት የሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶች መልካም ዕይታ ቢሆንም፣ ከአሠራር ጋር ተያይዞ መስተካከል የሚገባቸው አካሄዶች የማቃናት ሥራ እንደሚጠይቅና ይህም ዕውን ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

ተመራቂ ሐኪሞችን በሥራ ላይ ሊያሰማራ በሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በቅርቡ ስምምነት መፈራረማቸውን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አስታውሰዋል፡፡

ከፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ሥራ አጥ የሆኑ ተመራቂ ሐኪሞችን ሥራ ለማስያዝ ጤና ሚኒስቴር በርካታ ጥረቶችን አድርጓል፡፡ ካከናወናቸው ጥናቶችም መካከል ለጤናው ዘርፍ ተጨማሪ በጀት መመደቡ፣ በተለይ በአማራ ክልል የሚገኙ 200 የሚጠጉ ተመራቂ ሐኪሞችን በየጤና ተቋማት መመደቡ ይገኝበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...