ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋው እየናረ በመጣው የእንስሳት መኖ ግብዓት ሳቢያ፣ የእንስሳት ዕርባታ ድርጅቶች ህልውናቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ልማት ኢንስቲትዩት የመኖ ምርት ምርምርና ፕሮሰሲንግ ዳይሬክተር አቶ ደምሴ ነጋሽ እንደገለጹት፣ ከስንዴ ዱቄት ፉብሪካዎች የሚገኘው ፉርሽካና ከዘይት ፋብሪካዎች የሚገኘው ፋጉሎ ባለፉት አምስት ወራት ዋጋቸው በእጥፍ ጨምሯል፡፡ ዱቄት ፋብሪካዎች የስንዴ ዋጋ ጭማሪንና የምርት እጥረትን እንደ ምክንያት እንደሚያነሱ ገልጸው፣ በዚህም ሳቢያ በእንስሳት ዕርባታ ላይ የተሰማሩ በመካከለኛና አነስተኛ ደረጃ ያሉ የዕርባታ ድርጅቶች ችግር ላይ ወድቀዋል፡፡
ባለፉት አምስት ወራት የተመጣጠነ የእንስሳት መኖ ዋጋ ካሻቀበባቸው አንዱ የአኩሪ አተር ኬክ የሚባለው ሲሆን፣ ከወራት በፊት በኩንታል 1,400 ብር ሲሸጥ እንደነበረና አሁን ግን እስከ 2,700 ብር እንደሚሸጥ፣ ፉርሽካም ዋጋው በእጥፍ ጨምሮ አሁን ላይ ከ1,300 እስከ 1,400 ብር እንደሚሽጥና በሌሎችም መኖዎች ላይም እንዲሁ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዳለ ዳይሬክሩ አስረድተዋል፡፡
ደላሎች ገበያው ውስጥ ጣልቃ በመግባታቸው የመኖን ዋጋ መኖሩን ኢንስቲትዩቱ በጥናት እንዳወቀው እንደሆነ ተገልጿል። በርካታ የዱቄት ፋብሪካዎችን በመያዝ ተረፈ ምርት በመሰብሰብና በመጋዘን ውስጥ በማከማቸት፣ ምርት በገበያ ውስጥ በስፋት እንዳይገኝ፣ ወቅት እየለዩ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ደላሎች ገበያውን እንደሚያተራምሱት ተጠቁሟል።
በአገር ውስጥ የሚገኙ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ድርጅቶች ወትሮውንም በግብዓት ዋጋ ንረት ከአቅማቸው በታች እያመረቱ ነው ያሉት አቶ ደምሴ፣ የእንስሳት መኖ እጥረት ብቻ ሳይሆን የጥራት ችግር እንዳለ በተደጋጋሚ የሚነገር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በጥናት ባይረጋገጥም በኢትዮጵያ የተመጣጣነ የእንስሳት መኖ የሚመገቡ እንስሳት፣ ከሦስትና ከአራት በመቶ እንደማይበልጡ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በአነስተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የዶሮ ዕርባታ ድርጅቶች ለመኖ በሚጠቀሙት የበቆሎ እህል ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት እየተዘጉ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ደምሴ፣ በግብዓት ዋጋ ጭማሪ ምክንያት ለገበያ በሚያቀርቧቸው እንቁላሎችና ዶሮዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ አለማድረግ የማይታሰብ እንደሆነ አስታውቀዋል።
‹‹በአገር ደረጃ ለሰብል ግብርና እንጂ ለእንስሳት ግብርና ትልቅ ትኩረት እየተሰጠ አይደለም፡፡ ከእንስሳት ዘርፍም ስለሥጋና እንቁላል እንጂ የመኖውን አቅርቦት በተመለከተ ትኩረት ሰጥቶ በሰፋት የሚሠራ አካል አይታይም፤›› ብለዋል፡፡
መኖ ከሌለ እንስሳቱንም ሆነ የተዋጽኦ ውጤቱን ማግኘት ስለማይቻል ከኢንዱስትሪ የሚወጡ ተረፈ ምርቶች በምን ዓይነት ሁኔታ ለገበያ መቅረብ እንዳለባቸው፣ የእንስሳት ዕርባታ ድርጅቶች ለመኖ ማዘጋጃ ፍጆታ የሚጠቀሙባቸውን የሰብል እህሎች ሊያገኙ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚዳስስ የመንግሥት ክትትል እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
ተረፈ ምርቶችን በሚያከማቹ ደላሎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ፣ የመኖ ማቀነባበሪያ ድርጅቶች ሰፋፊ የእርሻ መሬት ባለባቸው ክልሎች መሬት ወስደው የመኖ ግብዓት እንዲያመርቱ ማድረግ፣ ሌላው በረዥም ጊዜ መፍትሔ ሊደረግበት የሚገባ አማራጭ እንደሆነ አቶ ደምሴ አስታውቀዋል።