Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለተፈናቃዮች ትኩረት ያልተሰጠው የሥነ ልቦና ሕክምና

ለተፈናቃዮች ትኩረት ያልተሰጠው የሥነ ልቦና ሕክምና

ቀን:

በኢትዮጵያ በተለይ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች የተከሰተውና አሁን ላይ በዚያን ጊዜ ከነበረው አድማሱን ያሰፋው የእርስ በርስ ግጭት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡

የሚያርሱ እጆች እንዳያርሱ፣ የሚሠሩ እጆች እንዲታጠፉ፣ ይለግሱ የነበሩ እጆች ተመፅዋች እንዲሆኑ፣ ተማሪዎች ከትምህርት እንዲፈናቀሉ፣ ሙሉ አካል ያላቸው የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው አድርጓል፡፡ ሴቶችና ሕፃናትን የበለጠ የጎዳው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ እንዲሞቱም ምክንያት ሆኗል፡፡

መንግሥት በርካታ ተፈናቃይ የነበረበትን ኮንሶ ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉትን ወደ ቀደመ መኖሪያቸው እንዲመለሱና ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ድጋፍ በማድረግ፣ የተከሰቱ ችግሮች በውይይት ይፈቱ ዘንድ የየአካባቢውን ማኅበረሰብና የአገር ሸማግሌዎች በማሳተፍ ተፈናቃዮች እንዲቋቋሙና መደበኛ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡ ችግሮቹ አሁንም ድረስ በየሥፍራው በመዝለቃቸው የድጋፍ ሥራው አሁንም እየተከናወነ ነው፡፡

ከችግሩ ስፋትና በየአካባቢው ከሚከሰቱ ግጭቶች አንፃር፣ አሁንም ድረስ ያላባሩ መሆናቸው እንዲሁም በተፈጥሮ አደጋም መፈናቀል በማጋጠሙ በውጥረት፣ በችግርና በሥጋት ውስጥ ያሉትን ማኅበረሰቦች ከመከራቸው ማውጣት አልተቻለም፡፡

በመንግሥትና በተለያዩ ረጂ ተቋማት በተለይ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ምግብ፣ መጠለያና አልባሳት ማሟላቱ ላይ ርብርብ የተደረገውን ያህልም፣ ከዚህ ባልተናነሰ  ዘላቂ አዕምሯዊ ጉዳት ሊያደርስባቸው ከሚችለው የሥነ ልቦና ጉዳት ለማውጣት የረባ ሥራ ሲሠራም አልተስተዋለም፡፡

ነገር ግን በየትኛውም ዓለም ቢሆን በጦርነት፣ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ ለችግር የተጋለጡ በተለይ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ዳግም ወደቀደመ ሕይወታቸው እንዲመለሱና የመንፈስ ዕረፍት ያገኙ ዘንድ፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ ከሰብዓዊ ድጋፍ ጎን ለጎን አብሮ መሰጠት እንዳለበት በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

የእርስ በርስ ግጭትም ሆነ ጦርነት በተከናወኑባቸው ሥፍራዎች ሲገደሉ፣ ሲሳደዱ፣ ንብረት ሲቃጠልና ሲወድም ማየቱ፣ የቅርብ ቤተሰብ አባት፣ እናት፣ ወንድም ወይም እህት ሲደበደቡ አሊያም ሲገደሉ ማስተዋሉ፣ መደፈርና መደፈርን ማየቱ፣ በሽሽት ጊዜ የሞቱና የተጎዱ ሰዎችን ማየቱና የሰዎችን ሰቆቃ መስማቱም ሆነ አጠቃላይ ግጭት ይዞት በሚመጣው መከራ ውስጥ ማለፉ፣ አዕምሮ ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳም ቀላል አይደለም፡፡ ሰዎች ሌሎችን እንዳያምኑ፣ እንዲሸሹ፣ እንዲጠራጠሩ፣ እንዲበቀሉ፣ እንዲያቄሙ፣ በጥላቻ እንዲዋጡ በማድረግ ሰዋዊነታቸውን ይነጥቃቸዋል፣ አምራችነታቸውን ያሳጣቸዋል ብሎም የአዕምሮ ሕመምተኛ ያደርጋቸዋል፡፡

በጉራፈርዳ ተፈናቃዮች በሚገኙበት ሥፍራ ከሳምንታት በፊት ለሥራ የተሰማራ ባለሙያ፣ በሥፍራው እንደሰብዓዊ ዕርዳታው ሁሉ የሥነ ልቦና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው በርካቶች እንዲሆኑ ነግሮናል፡፡

በሥፍራው ከተጠለሉት ሙሉ ቤተሰቦቹ ሲገደሉ ከተደበቀበት ሥፍራ ሆኖ የተመለከተ ታዳጊ ወጣት ሰዎች ሲያዋሩት መልስ የሚሰጠው እየተንቀጠቀጠ፣ እየፈራና እየተደበቀ መሆኑን ታዝቤያለሁ ብሏል፡፡ ልጁ ቤተሰቦቹን አጥቶ መጠለያ ቦታ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ፍርኃት ውስጥ መዘፈቁን በዚህም ምክንያት መናገር እንኳን እንደሚያቅተውም አስተውሏል፡፡ ይህ ወጣት ብቻ ሳይሆን በርካቶች የቤተሰባቸውን አባላት አጥተዋል፡፡ ባለሙያው በሥፍራው በተገኘበት ወቅት በመጠለያው የሚያለቅሱ ይበዙ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በተለይ ቤተሰብ ሲሰቃይና ሲገደል ያዩ ሕፃናት የመንፈስ ስቃይ ውስጥ መሆናቸውን ታዝቤያለሁም ይላል፡፡

 በመቐለ የተፈናቃይ መጠለያዎች ውስጥ ካሉ ሰዎችም በፍርኃት ከነበሩበት ቀዬ የሸሹ፣ እርሻቸውን ያጡ፣ ቤተሰብ የሞተባቸው ይገኛሉ፡፡ ሥራና ንብረት ኖሯቸው ዛሬ ላይ በዕርዳታ የሚኖሩት ሁኔታውን መቀበል አቅቷቸዋል፡፡ በሕክምና መስጫ ውስጥ ከሚገኙት የመደፈር ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ደግሞ አካላዊው ብቻ ሳይሆን ሥነ ልቦናዊ ስቃያቸው የበዛ ነው፡፡ አካላዊ ጉዳቱን ለማከም ከሚደረገው በተጨማሪ በጥቂት የሥነ ልቦና ድጋፍ ለማድረግ እየተሞከረ ቢሆንም፣ ተጎጂዎቹ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነባቸው መታዘቡን ባለሙያው ነግሮናል፡፡

‹‹በስቃይ ውስጥ ያሉትና በውስጡ ያለፉት ተጎጂዎችን በሥራ አጋጣሚ በማየቴ ብቻ አሞኛል፡፡ ለብዙ ቀናት ራሴን ታምሜያለሁ፣ ዛሬም በተለያዩ ሥፍራዎች የያኋቸው ተፈናቃዮች የደረሰባቸው ሰቆቃ እኔም ውስጥ ቀርቷል፤›› ብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ሐኪምና መምህር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) እንደሚሉት፣ ሰዎች ላይ የአካል አደጋ ሲደርስ ወይም ግጭት ተፈጥሮ እስከመፈናቀል ሲደርሱና አዕምሮ ላይ ጫና የሚፈጥር ችግር ሲገጥማቸው ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች በርካታ ናቸው፡፡ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች አካላዊና አዕምሯዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ አካላዊ አደጋ ደግሞ ብዙ ጊዜ ለአዕምሮ ችግር ያጋልጣል፡፡

ከግጭት ጋር ተያይዞ የሚከሰተው አዕምሯዊ ጉዳት በሦስት እንደሚከፈል  መስፍን (ፕሮፌሰር) ያብራራሉ፡፡ አንደኛው አደጋ ሊደርስ ነው ብሎ መፍራት፡፡ ለምሳሌ አደጋ ሊደርስ ነው ተብሎ ከተነገረ በኋላ፣ በሥፍራው የሚገኙ ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍርኃናትና ጭንቀት ውስጥ የሚገቡበት ነው፡፡ ሁለተኛው አይቀሬ የሆነው አደጋ ሲከሰት ከፍተኛ የአዕምሮ መረበሽ ይኖራል፡፡ ሦስተኛው አደጋው ከደረሰ በኋላ የሚከሰት ከፍተኛ የሆነ የአዕምሮ ጤና መዛባት ሲሆን፣ እነዚህ ከቀላል እስከ ከባድ የአዕምሮ ጤና ችግር የሚያስከትሉ ክስተቶች ናቸው፡፡

በቅድመ አደጋው ጦርነት ሊነሳ ነው፣ ሰዎች ሊያባርሩን ነው፣ ችግርም ሊያደርሱብን ነው የሚለው ቀድሞ በቤተሰብ ውስጥ የሚከሰት ነው፡፡ ይህም ወላጆች ለልጆቻቸው፣ አባት ለሚስቱና ለቤተሰቡ፣ ከሁሉ በላይ ከልጆቿ ተነጥላ የማትሄደው እናት ላይ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ያደርሳል፡፡ እናቶችና ሴቶች በተለይ የችግሩ ሰለባ ይሆናሉ፡፡

ችግሩ ሲከሰት ደግሞ የአዕምሮ ችግሩ በተለይ በሴቶችና ሕፃናት ላይ ይጎላል፡፡ በአሁኑ ዘመን ደግሞ ወንዶችም ለአካላዊ ብቻ ሳይሆን ለሥነ ልቦናዊ ችግር ይጋለጣሉ፡፡ አካላዊው የወሲብ ትንኮሳ፣ ይህ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ መደፈር፣ መደፈሩ ደግሞ ልጆች በወላጆቻቸው ማለትም በእናት፣ በአባት፣ በወንድም ፊት ሊሆን ስለሚችል፣ ይህ ከባድ የአካል ቁስል ያደርሳል፣ የአካል ቁስሉ ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሕክምና ቢያገኝም ዕድሜ ልክ የሚዘልቅ የአዕምሮ ቁስል ጥሎ ያልፋል፡፡ የአዕምሮ ቁስሉ ዕድለኛ ሆኖ ከሻረ፣ የአዕምሮ ጠባሳ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነቱ ችግር ባለበት ጉዳቱ ጉልህ ደረጃ ሳይደርስ ማከም የሚቻለው ከሥር ከሥር እየተከታተሉ እንደ ሰብዓዊ ድጋፉ የሥነ ልቦና ድጋፍ ማድረግ ቢቻል ነበር፡፡

‹‹በእኛም አገር በአሁኑ ሰዓት ችግሮቹ መከሰታቸው እውነት ሆኗል፤›› ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፣ እነዚህ ሲከሰቱ ሕፃናት ከወላጆች መለየት፣ በሕይወት የተረፉ ካሉ ደግሞ አብሮ መሰደድ ይኖራል፡፡ መሰደዱ በራሱ የአዕምሮ ጠባሳ ያሳድራል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የለመዱትን ቀዬ፣ ቁስ፣ ያደጉበትን አካባቢ ጥለው ወደ ሌላ ሲሄዱ ለአካባቢው ባይተዋር ይኮናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ምን ይመጣ ይሆን? የሚለው በየጊዜው በአዕምሯቸው ይከሰታል፡፡ ከዚህ ባለፈ በአደጋው ጊዜ ያሳለፏቸው መከራዎች በቅዥትና በህልም መልክ መከሰት ይጀምራሉ፡፡ ይህ ከፍተኛ የሆነ ፍርኃት ያመጣል፣ አደጋውን የሚያስታውሱ ነገሮችም ይከሰታሉ የሚሉትን በምሳሌ ያነሳሉ፡፡

‹‹የአውሮፕላን ድብደባ ተከስቶ ከነበረ፣ ካለፈ በኋላም በሰማይ ወፍ ቢበር የአውሮፕላን ድብደባ ይመስላቸዋል፡፡ አውሮፕላን ባለፈ ቁጥር ቦምብ የሚጥል ይመስላቸዋል፡፡ ከፍተኛ የሆኑት የዚህ ዓይነት ጭንቀቶች ቀንም ለሊትም መከሰት ይጀምራሉ፤››፡፡

እንደ ፕሮፌሰር መስፍን፣ ሕፃናት ከሆኑ ስሜታቸውን የሚገልጹበት አቅም ስለሌላቸው በፍርኃት፣ በጭንቀት፣ በቅዥት የተሞላ ሕይወት እንዲኖሩ፣ ያለፈን ክስተት አሁንም እንዳለና እየተፈጸመ እንደሆነ እንዲቆጥሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ሐዘናቸውና ጭንቀታቸው ልክ የሚሰብር ይሆናል፡፡ ይህም በእንቅልፍ ልባቸው ሽንት መሽናት ያቆሙ ሕፃናት ዳግም እንዲጀምሩ፣ የጭንቀትን አካላዊ ምልክት እንዲያሳዩ፣ ትኩረት እንዲያጡ፣ እንዲረበሹ፣ እንዲጮኹ ያደርጋል፡፡ ይህም ለከፍተኛ ፍርኃትና የአዕምሮ መዛባት ሊያደርስ ይችላል፡፡ የሕፃናትን ከባድ የሚያደርገው የሕፃናትን አዕምሮ ጠንቅቆ ካለማወቅም ነው፡፡

አዋቂዎች ላይ ደግሞ ሕፃናቱ ላይ ከሚስተዋለው በተጨማሪ ቁጣ፣ የበቀል ስሜት፣ ቁጭት፣ እኔ ተርፌ እህቴ፣ ወንድሜ፣ ዘመዶቼ አልቀው የሚል የበዳይነት ስሜት ይመጣል፡፡ ከቀላል እስከ ከባድ የአዕምሮ ችግር ድብርትና ከዚህም በላይ ይከሰታል፡፡

በአገራችን በሰሜኑም፣ በምዕራቡም እንደተከሰተው ዓይነት ግጭት፣ በተፈጥሮ፣ በናዳ፣ በጎርፍ፣ በእሳት፣ መንደር ሲጠፋ መፀፀት፣ ማዘንና ሌሎች፣ ችግሮች ለየትኛውም ዓለም ሕዝቦች የሚስተዋል ነው፡፡

ነገር ግን የአውሮፕላን መከስከስን ጨምሮ የተለያዩ አደጋዎች ሲደርሱ የምዕራቡ ዓለም ዕርዳታ ሰጪዎች ፈጥነው ይደርሳሉ፡፡ ድንኳንና ምግብ ያቀርባሉ፡፡ ተጨማሪ አደጋ እንዳይደርስ ደግሞ የየአካባቢ ፀጥታ ኃይሎች ጥበቃ ያደርጋሉ፡፡ ይህ በአብዛኛው አካላዊ ዕርዳታ ማለትም ማረፊያ፣ ምግብ፣ ልብስ ማቅረብ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ነገር ግን የአዕምሮ ድጋፍ ዕርዳታ ከመጀመርያው ጀምሮ መቅረብ አለበት፡፡ ይህ ደረጃው የተለያየ ነው፡፡ ለሕፃናት ለብቻቸው እንደየደረሰባቸው የሥነ ልቦና አደጋ መጠን ድጋፍ ሊደረግ ይገባል፡፡ ሕፃናቱ ቤተሰብ አጥተው ከሆነ፣ ቤተሰብ እንደሚፈጠርላቸው ቤተሰብን ተክተው የሚያሳድጓቸው እንደሚኖሩ በመንግሥት፣ በግብረ ሰናይ ድርጅቶችና በበጎ ፈቃደኞች ደረጃ ቢያንስ በሙያው በሠለጠኑ ባለሙያዎች አማካይነት እንዲረጋጉ ይደረጋል፡፡ ይህ ከአካላዊ ዕርዳታው ጎን ለጎን የሚሰጥ ዕርዳታ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ለምሳሌ ከሦስትና ከአራት አሠርታት በፊት የእስራኤል መንግሥት ዘመቻ (ኦፕሬሽን) ሰለሞንና ዘመቻ ሙሴ በሚል ቤተ እስራኤላውያን ከጎንደር በእግር ተጉዘው ከዚያም ከሱዳን እስራኤል እንዲገቡ ሲያደርግ (ከአዲስ አበባ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የተጉዙትን ጨምሮ)፣ ሰዎቹ በመንገዳቸው ብዙ አደጋና የሚረብሽ ነገር ደርሶባቸዋል፡፡ በሕመምና በሌላም ልጆቻቸውን ያጡ አሉ፡፡ እስራኤል በሚገቡበት ጊዜ አካላዊ እንክብካቤ ሲደረግላቸው ከዚሁ ጎን ለጎን እስራኤል ካለው ማኅበረሰብ በቀላሉ እንዲዋሃዱና ከሥነ ልቦና ጫናቸው እንዲያገግሙ ለየቤተሰቡ የሥነ ልቦና አማካሪ ተመድቦ ነበር፡፡

ይህን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በቂ ባለሙያ የለንም፣ ድሆች ነን፡፡ ተፈናቃይ ባሉባቸው አካባቢዎች በተለይም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ባሉበትና ብዙዎቹ አስከፊ ነገር ባዩበት ሁኔታ፣ ለእነዚህ ሁሉ በቂ አማካሪ ማቅረብ የሚታሰብ እንዳልሆነ የገለጹት ፕሮፌሰር፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ ጠንካራ የእስልምና፣ የክርስትና የዋቄፈታና ሌሎች ሃይማኖቶች ስላሉዋት በእነዚህ መጠቀም እንደሚቻል ያብራራሉ፡፡

የአገር ሽማግሌዎችንና በየአካባቢው ያሉ ጠንካራ እናቶች በመጠቀም በየቦታው ራሳቸውን እንዲያደራጁ፣ በእምነታቸውና ለራሳቸው ሲሉ በየአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን እንዲረዱ፣ ድጋሚ ችግሩ እንዳይፈጠርም የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ጥበቃ እንዳለ ሆኖ የየአካባቢው አዋቂዎች እንዲሳተፉ በቅንጅትና በዘላቂነት መሥራት ይገባል፡፡ በተለይ ልጆች፣ ሕፃናትና እናቶች ሊጎዱ እንደሚችሉ በመገንዘብ ትክክለኛ ሕክምና ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወደ ሕክምና፣ የምክር አገልግሎት ወይም የአዕምሮ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ዕርዳታ እንዲያገኙ ማስቻልም ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ ከግጭት ጋር ተያይዞ ሊሠሩ የሚገቡ ወሳኝ ነገሮችም ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በባህልና በሃይማኖት ጠንካራ ሕዝብ አላት፡፡ የሃይማኖት አባቶች ለእምነታቸው፣ ለሃይማኖታቸው ከሁሉም በላይ ለፈጣሪያቸው ተገዥ ከሆኑ በማናቸውም ሰው ላይ የሚደርስ አደጋ በራስ ልጅ ላይ እንደደረሰ ቆጥረው ምግብና ልባሽ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የሥነ ልቦና ድጋፍ እንደ አቅማቸው ማድረግ አለባቸው፡፡ ሁሉም ሰው መሆኑን ተገንዝበው የማረጋጋት ሥራ ከሠሩም ተጎጂዎች ባለሙያ እስኪያገኙ ተረጋግተው እንዲኖሩ የማድረግ አቅም አላቸውም ብለዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰር መስፈን ማብራሪያ ሁላችንም ሰዎች ነን፡፡ ጎሳ የሚባለው በሶሻሊስቶቹ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ እየተባለ የተሸነሸነው በሙሉ በእኛው በሰዎች የመጣ ነው፡፡ ጎሳ ከመሆናችን በፊት ሰዎች ነን፡፡ ይህንን የሚገነዘቡ ሰዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና እናቶችን ማስተባበር ከቻልን ቀላሉና የተሻለው መንገድ በሥነ ልቦና ጉዳትን በዚህ በኩል ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡

ባለሙያዎች ሊያደርጉ የሚችሉትን ድጋፍ በተመለከተ እሳቸው ከጠቅላላ ሐኪምነት ተነስተው የተለያዩ ትምህርቶችን በመማር የአዕምሮ ሐኪም ጭምር እንደሆኑ በማስታወስ፣ የሥነ ልቦና ትምህርት የወሰዱ ሁሉ በትራዎማ (አደጋ) ላይ ልዩ ሥልጠና ያገኙ ላይሆኑ ስለሚችሉ፣ የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን በአስቸኳይ አሰባስቦ በአደጋና ዝግጁነትም ሆነ በሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት ትራዎማ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በማዘጋጀት የሥነ ልቦና ጉዳቶችን እንዲያክሙ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ መከላከል፣ ሕክምናና ጥናትና ምርምር ላይ ያተኮሩ ባለሙያዎችን አዘጋጅቶ ማይካድራ፣ መተከል፣ መቐለ፣ አክሱም፣ ኮንሶ፣ ጉራፈርዳና ሌሎችም ሥፍራዎች በመላክ አስፈላጊውን ዕርዳታ እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ የሥነ ልቦና ድጋፍ ሊሰጥ የሄደ ባለሙያም ከራሱ አዕምሮ በላይ የሆነ የሌሎች ችግር ቢያጋጥመው አዕምሮው ሊፈርስ ይችላል ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹ብዙ ጉዳት የደረሰበት ሥፍራ የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን ባለሙያ ስለሆኑ ብቻ ሳይዘጋጅ ቢላኩ ራሳቸው ታካሚ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ የቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳዩ የሚመለከተው ክፍል አደጋዎች እየደረሱ ስለሆነ በባለቤትነት ይዞ መሥራት ነው፤›› ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ባለቤት ማን ነው? ሲባል፣ የኢትዮጵያ የአዕምሮ ሐኪሞች ማኅበር ነው? የኢትዮጵያ ሥነ ልቦና ባለሙያዎች ማኅበር ነው? ሌላ መንግሥታዊ አካል ነው? ወይስ በጋራ ከአካባቢው የዕርዳታ ድርጅቶች ጋር አብሮ መሥራት ነው? የሚለው መስተካከል እንዳለበት የሚገልጹት ፕሮፌሰር መስፍን፣ ይህ ካልሆነ ከማኅበራዊ ሚዲያ ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ወቅት የተከሰተው ከፍተኛ ስለሆነ የሚፈናቀሉ ሰዎችን ከሕፃናት ጀምሮ እስከ አዋቂዎች የተለየ ትኩረት ሰጥቶና ዘርፍን የሚመራ አካል አዋቅሮ፣ ከሰብዓዊ ዕርዳታው ጎን ለጎን የሥነ ልቦና ድጋፍ መስጠት ሊሠራበት እንደሚገባም ፕሮፌሰር መስፍን አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ ተፈናቃዮች በሠፈሩባቸው ሥፍራዎች የሥነ ልቦና የመጀመርያ ዕርዳታ ከሰብዓዊ ዕርዳታው ጎን ለጎን ማቅረብ ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ያስፈልጋል በሚል የተወሰኑ ተቋማት እንቅስቃሴ ቢጀምሩም ሥራው ወደ ታች አልወረደም፡፡ ሆኖም ተከስተዋል ከተባሉ ዘግናኝ ድርጊቶች አንፃር የሥነ ልቦና ድጋፍም በተራድâ ሥራዎች ውስጥ ተካቶ መሥራት እንዳለበት መገንዘብ ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...