Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሴቶች ሐኪሞችን ሙያዊ አቅም የማሳደግ ርዕይ

የሴት ሐኪሞችን ሙያዊ አቅም ማሳደግ፣ ለሴት የሕክምና ባለሙያዎች በመብቶችና የሥነ ምግባር መርሆች ላይ ግንዛቤን ለመፍጠርና ተያያዥ ጉዳዮችን ለመፈጸም ከአራት ዓመታት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሴት ሐኪሞች ማኅበር ነው፡፡ ‹‹በሴት ሐኪሞች አመራር የጤና እንክብካቤን መለወጥ›› በተሰኘ መሠረተ ሐሳብ ሚያዝያ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. የተመሠረተው ማኅበሩን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩ ነቢያት ሰመርዲን (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ስለማኅበሩ እንቅስቃሴ ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሴት ሐኪሞች ማኅበር እንዴት ተመሠረተ?

ዶ/ር ነቢያት፡- የኢትዮጵያ ሴት ሐኪሞች ማኅበር የተቋቋመው በ2009 ዓ.ም. ነው፡፡

ሐሳቡ የመጣው ማርች ኤይት የሴቶች ቀን ሲከበር የተሰባሰብን 40›› ሐኪሞች ማኅበሩን ለመመሥረት ተስማማን፡፡ ማኅበሩ ዓላማ አድርጎ የተነሳው ሴት ሐኪሞች ያለምንም ገደብና ጫና እኩል በሥራ መሳተፍና ማገልገል ችለው፣ እንዲሁም ውሳኔ ሰጪነታቸው ጠንክሮ በዘርፉ ዕምቅ አቅማቸውን የሚያወጡበትን ባህል ለማዳበር ነው፡፡ ሴቶች በሕክምና ሙያ የላቀ ብቃት እንዲኖራቸውና ኅብረተሰቡን በተሻለ ሁኔታ እንዲያገለግሉ የማስቻል ተልዕኮንም አንግቧል፡፡ የማኅበሩን ራዕይና ተልዕኮ በማንገብ ሰኔ 2010 ዓ.ም. የመጀመርያ የመመሥረቻ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ ማኅበሩን ሕጋዊ የማድረግ ሒደት ጊዜ በመውሰዱና ፈንድ የማግኘት ሒደቱ ምክንያት ለአንድ ዓመት ሊጓተት ችሏል፡፡     

ሪፖርተር፡- የማኅበሩን ተልዕኮና ራዕይ ለማሳካት ምን ዓይነት ሥራዎችን ትተገብራላችሁ?

ዶ/ር ነቢያት፡- ሴት ሐኪሞች የላቀ ብቃት እንዲኖራቸውና ወደ አመራርነት ለማምጣት አራት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጠናል፡፡ የሴት ሐኪሞችን ሙያዊ አቅም ማሳደግ የመጀመርያው ሲሆን፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሴት ሐኪሞች አቅጣጫ ማሳየት፣ እንዲሁም መብቶችና የሥነ ምግባር መርሆችን ግንዛቤ መፍጠር ዋነኞቹ ናቸው:: መብቶችና የሥነ ምግባር መርሆዎች ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትኩረት ለማድረግ የታሰበው በሙያ ውስጥ ሲያልፉ በሥነ ምግባር አብረው ማደግ ስላለባቸው ትኩረት ተደርጎ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ በሕክምና ሙያ የማኅበረሰብ አገልግሎትና የበጎ ፈቃድ ትብብርን እንዲያጎለብቱ ማድረግ ሌላው ተግባር ነው፡፡ ብዙ  የሚጠይቁና ትብብር የሚሹ ሥራዎችም ይኖሩናል፡፡    

ሪፖርተር፡- ከምሥረታው በኋላ ማኅበሩ ያከናወናቸው ተግባሮች ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ነቢያት፡- ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ መካከል የማኅበሩ በሌሎች የመንግሥትም ሆነ በማኅበረሰቡ ያለው ዕይታ እንዲጨምር ጠቅላላ ጉባዔዎችን አከናውኗል፡፡ ብዙ የማኅበር አባሎች እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ በኋላ የተለያዩ ይዘት ያላቸው ጥናታዊ ጽሑፎች አዘጋጅተናል፡፡ አዲስ ተመራቂ የሴት ሐኪሞች ሥር አጥ ሆነው ስለተቀመጡ እነርሱን በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ምን ማድረግ እንዳለብን መፍትሔ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረግን እንገኛለን፡፡   

ሪፖርተር፡- የሙያ ማኅበሩ ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባት ከተሰማ በኋላና አሁንም ለሕክምና ካላችሁ ቅርበት አንፃር ምን እየሠራችሁ ነው?

ዶ/ር ነቢያት፡- ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ለማገዝ የተለያዩ መልዕክቶችን በመቅረፅ፣ በዌብናር ውይይቶች እስካሁን ድረስ ሰባት ውይይቶችን በማካሄድ ለአባላት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከጤና ሚኒስቴር የኮቪድ ምላሽ ኮሚቴ ውስጥ የማኅበሩ ሦስት ሐኪሞች ይገኙበታል፡፡ እኔን ጨምሮ የውስጥ ደዌ ሐኪሞች በኮቪድ ምላሽ አሰጣጥ ላይ የተለያዩ የሕክምና ጋይድ ሳይኖችን በማዘጋጀት እየተሳተፍን ነው፡፡ ከዚያ ውጪ በግል ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል እየሠራሁ ሲሆን፣ በቀጥታ የኮሮና ቫይረስ ሕሙማን እያከምኩ እገኛለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ከማኅበሩ ባሻገር በግል ኃላፊነቴን እየተወጣሁ ሲሆን ሌሎቹም በግል በያሉበት የጤና ተቋም ኃላፊነታቸው እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደረጃ ዶት ኮም ከተባለ ድርጅት ጋር በመሆን የተለያዩ ሥልጠናዎች በተለይም የሕይወት ተሞክሮ ሥልጠና ራሳቸውን እንዴት ማሳደግ እንዳለባቸው በተከታታይ ሥልጠና እንዲያገኙ እያደረግን እንገኛለን፡፡  በተለያየ መልኩ ሴት ሐኪሞች ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ ሥልጠና እየተሰጠ ሲሆን፣ በጤና ሚኒስቴር በኩል ዕድል አግኝተን በጋራ ለመሥራት በሒደት ላይ እንገኛለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የሕክምና ማኅበራት በሚገኝ የገንዘብ ዕርዳታ የሴቶችን አቅም የማጎልበት ተግባራት ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶች ተፈጻሚ እንዲሆኑ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ሁለተኛው የትኩረት አቅጣጫ የሆነው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሴት ሐኪሞችን ማብቃት ላይ ነው፡፡ ይህም በምን መልኩ ራሳቸውን የበቃ ሐኪም ማድረግ ይችላሉ? የሚለውን ጋይድ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ይህን ስል እኔ ወደ ሕክምና ስገባ ማንም ጋይድ (መምርያ) የሚያደርገኝ ሰው ባለማግኘቴ ብዙ አስቸጋሪ ጊዜዎችን እንዳሳልፍ አድርጎኛል፡፡ በእኔ የሆነው በሌሎች ሴት ሕክምና ተማሪዎች እንዳይደርስ ስለ ትምህርቱ፣ በሥራ ዓለም ሊገጥማቸው የሚችለው ፈተናና፣ እንዴት መወጣት እንዳለባቸው ምክረ ሐሳብና ተሞክሮ እንዲያገኙ የሚደረግበት መንገድ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት ስትራቴጂክ ፕላን ስለተዘጋጀ፣ በምን መልኩ ሴት ሐኪሞችን ማብቃት እንዳለብንና ማኅበረሰቡን የሚያገለግሉበት መንገድ እየተመቻቸ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሮና ቫይረስ በሴት ሐኪሞች ላይ በተለየ መልኩ ጫና አሳድሯል?

ዶ/ር ነቢያት፡- ሴት ሐኪሞች በብዙ መልኩ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ቤተሰብ፣ እናት ስለሆኑ ከልጆቻቸው ጋር ቁርኝነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩን ውስብስብ ያደርግባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ብዙ ጓደኞች ነፍሰ ጡር ሆነው የኮሮና ቫይረስ ታካሚ የሚያክሙ አሉ፡፡ ኮሮና ቫይረስ ደግሞ ነፍሰ ጡር ላይ እንደሚጠና በሳይንስ ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ይኼንን ሁሉ እየሠሩ ሕመሙ የያዛቸው ብዙ ጓደኞቻችን አሉ፡፡ ሁለት ነፍስ ይዘው ሌላውን ሰው ከማገልገላቸው ደግሞ በሽታው ሲይዛቸው ምን ያህል ጫና እንደሚበዛ ለመገመት አያዳግትም፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ ግጭት የተከሰተባቸው ቦታዎች ሴት ሐኪሞቻችን እየሄዱ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ ችግሮች ደርሶባቸው ሪፖርት ያደረጉም ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ የአስገድዶ መድፈር ጭምር የደረሰባቸው አሉ፡፡ ሌሎች ችግሮች እንዳሉ ሆነው፡፡ ስለዚሀ ሴት ሐኪሞች ከሌላው በተለየ የሚደርስባቸው ተጨማሪ ጫና አለ፡፡

ሪፖርተር፡- እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲከሰቱ ምን መደረግ አለበት? እንደ ማኅበሩ ምን አደረጋችሁ?

ዶ/ር ነቢያት፡- እንደ ጀማሪ ማኅበር እየሄድንባቸው ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡፡ መደፈርን ጉዳይ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ሴቶች የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት ሒደት ላይ ነን፡፡ ከዚህ ባሻገር እንደዚህ ዓይነት ጥቃት የደረሰባቸውን እህቶቻችን የሥነ ልቦና ችግር እንዳይገጥማቸው እናሳክማለን፡፡ ዕገዛ የሚያስፈልጋቸውን ደግሞ በተቻለ መጠን ገንዘብን ጨምሮ ዕርዳታ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከሕክምና ጋር በተያያዘ የሚወጡ ፖሊሲዎች ግብዓት ከመስጠት አንፃር ምን ዓይነት ሚና ይጫወታል?

ዶ/ር ነቢያት፡- ፖሊሲን ለማስቀየርና ግብዓት ለመስጠት በጣም ጠንካራና የሚታይ ማኅበር መሆን አለበት፡፡ እንደ ወጣት ማኅበር ፖሊሲ ማውጣት ላይ እየተወከልን እንገኛለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋል›› አቶ አበራ ሉሌሳ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ጸሐፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት 89 ዓመታት በመላ አገሪቱ የሰብዓዊነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በድርቅ፣ በበሽታና በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠለያ፣ የመድኃኒትና የ24 ሰዓት...

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን እንክብል

ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሦስት ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምር ያደረገበትንና ለገበያ ያበቃውን ዶባ-ቢሻን እንክብል የውኃ ማከሚያ...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...