የቻይና መንግሥት ለኢትዮጵያ ያበረከተውና ለኮቪድ-19 መከላከያ የሚውለውን 300 ሺሕ ዶዝ ሲኖፋርም ክትባት ርክክብ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ተከናወነ፡፡ በቻይና የተመረተውን ይህንኑ ክትባት የተረከቡት የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ሲሆኑ ያስረከቡት ደግሞ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣዎ ዢውሃን ናቸው፡፡
ከርክክቡ በኋላ ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ 20 በመቶ ያህሉን ዘንድሮ ለኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽ ለማድረግ እየተተገበረ ላለው ዕቅድ ውጤታማነት ከቻይና የተበረከተው ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ድጋፉ የመጀመርያ መሆኑንና ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የቻይና መንግሥት ቃል እንደገባ፣ ይህም ሆኖ ግን ወረርሽኙን በክትባት ብቻ መከላከልና መቆጣጠር እንደማይቻል፣ ከዚህ አኳያ ቀደም ሲል ሲካሄዱ የቆዩት መከላከያ መንገዶች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት፡፡
ከመከላከያ መንገዶቹም መካከል አንዱና ዋነኛው ሲተገበር የቆየውና አሁን ደግሞ ተጠናክሮ የቀጠለው መመርያ መሆኑን ያወሱት ሚኒስትሯ፣ ይህም በመሆኑ ማኅበረሰቡ በመመርያው መሠረት የራሱን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አበክረው ጠይቀዋል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ወረርሽኙን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በተሰጠው ምላሽ የቻይና መንግሥት ልዩ ልዩ የሕክምና መሣሪያዎችንና የኮቪድ-19 መከላከያ ኪቶችን በመርዳት እንዲሁም የሕክምና ቡድኖችን በመላክ አጋርነቱን ማስመስከሩን ሚኒስተሯ አስታውሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዢውሃን ባለፈው ዓመት ቻይና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በታመሰችበት ወቅት ወንድም የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎኗ በመቆም ያበረከተው ዕገዛና ድጋፍ ምንጊዜም እንደማይረሳ ተናግረዋል፡፡
ቻይና ለአፍሪካ አገሮች የሕክምና ቡድኖችን ባሰማራችበት ወቅት ኢትዮጵያ የመጀመርያዋ መዳረሻ እንደነበረች፣ አሁንም ቻይና ለ80 ታዳጊ አገሮች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶች መርዳቷንና እየረዳችም መሆኑን ከአምባሳደሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያና ከቻይና ወደ አፍሪካ የሚሄዱትን የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶችን በማጓጓዝ ረገድ ቁልፍ ሚና መጫወቱን አምባሳደሩ አመልክተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ ያደጉም ሆነ በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል በጋራና በትብብር ካልተንቀሳቀሱ በስተቀር በየፊናቸው የሚያደርጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ እንደማይሆን ነው የተናገሩት፡፡
ከዚህ አኳያ ከአንድ ዓመት በፊት ቻይና በወረርሽኙ በታመሰችበት ወቅት ኢትዮጵያ በትብብር የመሥራትን አጋርነትን እንዳሳየች፣ በአፍሪካ ውስጥ ካሉት አየር መንገዶች መካከል የቻይና አፍሪካን ትስስር በማስፋት ረገድ ጉልህ ሚና የሚጫወተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ እንደሆነ አምባሳደሯ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎና ሎጀስቲክ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ፍጹም አባዲ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶችን በመላው ዓለም በማጓጓዝ ረገድ በአርአያነት እንደሚታይ፣ አሁንም ይህንኑ አገልግሎት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡