አራት ዓመታት ጠብቆ የሚመጣውን የኦሊምፒክ ጨዋታ በቴሌቪዥን መስኮት መመልከት የብዙኃኑን ስሜት ያነሳሳል የሚል አስተያየት ይሰጣል፡፡ ስፖርተኞች በተካኑበት አትሌቲክስ ውጤት ለማምጣት ሲጥሩ፣ ከአሠልጣኞቻቸው ጋር ሲመካከሩና ድንቅ ብቃታቸውን ሲያሳዩ ለተመልካች የሚሰጠው የራሱ የሆነ ስሜት እንዳለው ይነገራል፡፡ ይኼም ስሜት አገርን ከመውደድ ጋር የሚያቆራኘው አንዳች ነገር እንዳለው ይታመናል፡፡
ለዚህም ይመስላል ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውድድሩን በድል ካጠናቀቁ በኋላ የሽልማት ሠገነት ላይ ወጥተው የአገራቸው መዝሙር ሲዘመር እንባቸው የሚቀድመው፡፡
በኮሎምቢያ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲ በቀረበ ‹‹ኦሊምፒክና አገር ወዳድነት›› በተሰኘ አንድ መጣጥፍ፣ ኦሊምፒክ በአገር ወዳድነት ላይ አዎንታዊ እንዲሁም አሉታዊ ጎኖች እንዳሉት ያስቀምጣል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ለመግለጽ የሚጠቅሱት የፖለቲካና የብሔርተኝት መድረክ የሚያስተናግድ መድረክ ሆኗል በማለት ነው፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ መካፈል የአገርን ክብር በዓለም አቀፍ መድረክ ለመወከል ትልቅ ዕድል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ የማይዘነጉና የሚያኮሩ ጊዜያትን አሳልፋለች፡፡ በተለይ በአትሌቲክሱ የአገራቸውንና የራሳቸውንም አሻራ ማኖር የቻሉ በርካታ አትሌቶች አሏት፡፡
በአንፃሩ የኦሊምፒክ ጨዋታው በመጣ ቁጥር በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል አለመግባባትና እንካ ሰላንትያ መገለጫው ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ከሐምሌ 16 ቀን እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በቶኪዮ ለሚሰናዳው ኦሊምፒክ ጨዋታ ሁለቱ አካላት ገና ከአሁኑ ስድድብ ቀረሽ እሰጣ ገባ ውስጥ መግባታቸውን በግልጽ አስታውቀዋል፡፡
ሐሙስ መጋቢት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ‹‹አምባገነን በመሆኑ›› ምክንያት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት እክል ገጥሞታል ሲል ክስ አቅርቧል፡፡
‹‹ለኦሊምፒክ ዝግጅት አትሌቶች ሆቴል ሲገቡ እንክብካቤና ክትትል ማድረግ የሚገባው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ነው። ነገር ግን አትሌቶች ሌላው ቀርቶ ውኃ እንኳን በአግባቡ እያገኙ አይደለም፤›› ሲል ፌዴሬሽኑ አብራርቷል፡፡
በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ስለገባው ውዝግብ ሲገልጽ፣ ዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ኮታ ሳይልክ በሆቴል የሚገኙትን አትሌቶችን ለመቀነስ ሲሉ ፌዴሬሽኑን ሳያማክር፣ የ50 አትሌቶችን ዝርዝር ብቻ የመያዝ አካሄድ አግባብነት የለውም ይላል፡፡
የመጨረሻ ተመራጮች ወደ ሆቴል የማስገቢያና የበጀት ሁኔታ ግልጽነት የጎደለው መሆኑን የሚያወሳው ፌዴሬሽኑ፣ ኮሚቴው በተሳሳተና አወዛጋቢ በሆነ መልኩ በተደጋጋሚ የሚጣረሱ ሐሳቦችን በማምጣት በዝግጅት ሒደቱ ላይ ጫና መፍጠሩን፣ ፌዴሬሽኑንም እያሳሳተ እንደነበር ከወርልድ አትሌቲክስና በማናጀሮች በኩል ያገኘው መረጃ እንደሚያስረዳውም ጠቅሷል፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም ለአትሌቶችና ለአሠልጣኞች የላብ መተኪያ የሚሆን ገንዘብ ቃል ቢገባም፣ እስካሁን ግን ምንም ዓይነት ክፍያ ባለመቅረቡ ፌዴሬሽኑ ከአትሌቶች ከፍተኛ ቅሬታ ሲደርሰው ነበር፤›› በማለት የጉዳዩን መካረሩን የሚያስረዳ ወቀሳ አዘል ሪፖርት በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ቀርቧል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አትሌቶቹ በሦስት የተለያዩ ሆቴሎች ላይ ተከፋፍለው መገኘታቸው ተቀናጅቶ ለመሥራትና ለሥልጠና አመቺ እንዳልሆነ፣ እንዲሁም በተፈጠሩ ውዝግቦችና አለመግባባቶች የተነሳ በአትሌቶችና በአሠልጣኞች ሥነ ልቦና እንዲሁም የሥልጠና ሒደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩን በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቅሷል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የአሠልጣኞቹንና የአትሌቶቹን የአራት ወራት የላብ መተኪያ ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፍጸሙንም አስረድቷል፡፡
ውድድር በመጣ ቁጥር ግብግብ ውስጥ መግባትን ባህላቸው እያደረጉ የመጡት የሁለቱ ተቋማት ጉዳይ ለብዙኃኑ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ለሁለቱም ተቋማት ቅርበት ያላቸው አካላት አስተያየት ከሆነ፣ ክርክሩና ጉሽምያው የግለሰቦች እንጂ ከስፖርቱ ጋር አንዳች ግንኙነት የሌለው ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
በተለይ በሁለቱም ተቋማትና በተቋማቱ መሪዎች ሥር ያሉ፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ላይ የተሠማሩ አካላት የጥቅም ፍላጎት የሁልጊዜ የችግር መነሻ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡
የዘንድሮ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ ለመሳተፍ በሁሉም ርቀቶች ማለትም በመካከለኛ፣ በረጅም ርቀት፣ ዕርምጃና ማራቶን ጨምሮ 88 አትሌቶች ሥልጠና እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በአገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ አገር በሚደረግ ማጣሪያ ውድድር ተለይተው የመጨረሻዎቹ የሚለዩ ይሆናል፡፡ 17 አሠልጣኞችም በሆቴል ሥልጠና እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዓቃቤ ነዋይ በዛብህ ወልዴ (ዶ/ር)፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ ወ/ሮ ሳራ ሀሰን፣ ኮሎኔል ማርቆስ ገነቲ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ረዳት ኃላፊው አቶ ዮሐንስ እንግዳ ናቸው፡፡