Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርናውን ዘርፍ ከፖለቲካ ማስፈጸሚያነት በማፅዳት ማዘመን እንደሚገባ ተጠቆመ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ ለሚሆነው ሕዝብ የኢኮኖሚ መሠረት የሆነው የግብርና ዘርፍ፣ ከፖለቲካ ማስፈጸሚያነት ወጥቶ፣ ዘመኑ ያፈራቸውን የግብርና ቴክኖሎጂ ውጤቶች በመጠቀም የገበሬውን ሕይወት መታደግ ይገባል ሲሉ የግብርና ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

አርሶ አደሮች የተሻሻሉ ዘመናዊ የግብርና አሠራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙና ሙያን እንዲያዳብሩ ከማድረግ ይልቅ፣ ዘርፉ በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ለዓመታት ተጠላልፎ እንደነበር ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ይደግፋሉ ተብለው ከተቋቋሙ ተቋማት የሚገኘው መረጃ ለግብርናው ዘርፍ መለወጥ ከሚያደርጉት አስተዋጽኦ ይልቅ፣ የማይሰጡት እንደሚበልጥ የግብርና ኢኮኖሚ ተመራማሪው ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በግብርና ላይ ይሠራሉ ተብለው የተቋቋሙና የገበሬውን የአመራረት ዘዴና ሕይወት ለመቀየርና ምርት ማሳደግ ላይ ትኩረታቸው እንደሆነ ቢገልጹም፣ ለዓመታት ገበሬው ገበያን መሠረት ባላደረገ አመራረት ኑሮን ለማሸነፍ እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ከአገሪቱ ምርት 90 በመቶ የሚሆነው በተበጣጠሰ የግብርና ሥርዓት የሚገኝ፣ ይህ ዓይነቱ አመራረት ደግሞ የቤተሰብ ፍጆታ ላይ ብቻ የተመሠረተ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በቀደሙ የመንግሥት ሥርዓቶች በተለይ ለገበሬው ይቀርቡ የነበሩ የግብርና ግብዓቶች ከፖለቲካ ደጋፊነትና ወገንተኝነት ጋር የሚገናኙ እንደነበሩ፣ ችግሩ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ያልተቀረፈ በመሆኑ ወደፊት ግብርናውን ከየትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ጋር መጣመር እንደሌለበት አክለው ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮች በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ምክንያት ብቻ ማዳበሪያ ማግኘት የማይችሉበት ወቅት እንደነበር፣ በአሁኑ ጊዜ ምንም እንኳ ችግሩ የተቃለለ ቢሆንም ብዙ ይቀረዋል ሲሉ ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡

ለገበሬው ይቀርቡ የነበሩ የግብርና መረጃዎች ተዓማኒነት የጎደላቸው ከመሆኑም በላይ በተቋማት መካከልም ቅንጅታዊ አሠራር ባለመኖሩ፣ ገበሬው ያለ ምንም ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅርቦት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ እየገፋ እንደሚስተዋል፣ በቀጣይም መንግሥት ግብርናውን በጥናት ላይ በተመሠረተ አሠራር በመደገፍ ለአገር ማበርከት ያለበትን ሚና እንዲወጣ ሊደረግ ይገባል ሲሉ ጉቱ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት የነበሩ የመንግሥት ሥርዓቶች ግብርናን ማሳደግና ማዘመን የሚል መፈክር ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበረ ቢሆንም፣ አገሪቱ አሁንም በምግብ ራሳቸውን ካልቻሉ አገሮች ውስጥ የምትጠራ እንደሆነች የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ባለሙያው ጭምዶ አንጫላ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በዋነኛነት ለግብርናው ዘርፍ ቅርብ የሆኑ ምሁራን ዘርፉን እንዲመሩት ስላልተደረገና በፖለቲከኞች ይመራ ስለነበረ ነው ያሉት ጭምዶ (ዶ/ር)፣ ‹‹ግብርናና ፖለቲካ መደጋገፍ እንጂ መጠላለፍ የለባቸውም፤›› ብለዋል፡፡

ባለሙያዎቹ ይህን የተናገሩት አዋሽ አግሪ ቴክ የተባለ አገር በቀል የግብርና ድርጅት፣ ዮያ ግብርና የተባለ የጥሪ ማዕከልና በግብርና ላይ የሚሠራ ቴክኖሎጂ ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነበር፡፡

ቴክኖሎጂው አርሶና አርብቶ አደሩን ከግብርና ግብዓት አቅራቢዎች ጋር፣ አምራቾችን ከግብርና ምርት ተረካቢዎች ወይም ኢንዱስትሪዎች ጋር፣ አርሶ አደሮችን ከግብርና አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ማገናኘትና መሰል አገልግሎቶችን አዲስ ባስተዋወቀው 640 በተባለ አጭር ኮድ አማካይነት በመደወል ማግኘት እንደሚቻል፣ መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ባስተዋወቀበት ወቅት ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አዲስ በተፈጠረው የጥሪ ማዕከል አማካይነት አርሶ አደሮች በቀጥታ በመደወል ግብርና ነክ የሆኑ የምክር አገልግሎቶች፣ የገበያና የአየር ሁኔታን መረጃ የሚያገኙ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች