Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢትዮጵያን ሁኔታ ፀጥና ረጭ አድርጎ ለማስተዳደር የሚችል መንግሥት በአጭር ርቀት የሚመጣ አይመስለኝም›› በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ መምህር፣ ተመራማሪና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር

በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) በኢትዮጵያ የሦስት አሠርት የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ይታወቃሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲን ደግሞ በሊቀመንበርነት ይመራሉ። ፕሮፌሰሩ ለበርካታ ዓመታት በጋራ ሲንቀሳቀሱበት ስለነበረው መድረክ፣ ከኦፌኮ ጋር ስለተፈጠረው አለመግባባት፣ ስለአገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች፣ ስለቀጣዩ አገራዊ ምርጫ፣ ስለፓርቲያቸው፣ የምርጫ ዝግጅታቸውና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ከሲሳይ ሳህሉ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለረዥም ጊዜ በትግል ላይ ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋለውን የፖለቲካ ውጣ ውረድ እንዴት ያዩታል?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አሁን የምናየው ነገር እኔን ብዙም አያስገርመኝም፡፡ የፖለቲካ ውጣ ውረድ በኢትዮጵያ ብቻ የታየ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በዓለም ላይ ብዙ ታዳጊ አገሮች መንግሥታዊ ሥርዓታቸውን ለማደራጀት ሲሞክሩ ብዙ ዳር የወጡ ፅንፎችን ወደ መሀል ለማምጣት የሚያደርጉት ትግል ቀላል አልነበረም፣ አሁንም አይደለም፡፡ ስንት ውጣ ውረድ አለው፡፡ አሁን ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያው ተጨምሮበታል፡፡ እናም አሁን እንዲያው ፈጣን መፍትሔ ካላየን ብለው የሚፈልጉ ወገኖች ይገርሙኛል፡፡ የግንዛቤ ችግር አለባቸው እላለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ የህልውና ችግር ፈጣን መፍትሔ የለም፡፡ ማንም እንደ ጠንቋይ በአንድ ጊዜ መጥቶ መፍትሔ አምጥቻለሁ የሚል አካል ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ ዋናው የእኔ ፍልስፍና በኢትዮጵያ ጉዳይ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም፡፡ ስለሆነም ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል አለብን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን ጥረት ማድረግ ስንል የሚዋዥቅ የፖለቲካ ዓላማ ይዘን ሳይሆን፣ አምንበታለሁ ብለህ የምትለውን ይዘህና ከማወቅ ተነስተህ፣ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮውንም ኢትዮጵያዊ ልምዶችንም ባገናዘበ ሁኔታ የፖለቲካ መስመር ቀይሶ ያንን ዕውን ለማድረግ መጣር ነው፡፡ በትንሹ ኮሽታ ሁሉ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህም ፈጣን መልስ ለምን አልተገኘም ብዬ ተስፋ የምቆርጥ ሰው አይደለሁም፡፡ ሁኔታዎቹ ተስፋ አስቆርጠዋል፣ ምንም ዋጋ የለውም ብዬ ደግሞ እጄን አጣምሬ የምቀመጥ ሰው አይደለሁም፡፡ ለኢትዮጵያ ችግር እንግዲህ ፍቱን መድኃኒት የሚሆነውና ሊያስማማን የሚችለው፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በተለይም መድበለ ፓርቲያዊ ሥርዓት ዕውን ሲሆን ብቻ ነው፡፡ እንደዚያ ሲሆን ሕዝቡ በነፃነት የሚፈልገውን ይመርጣል፣ የማይፈልገውን ይጥላል፡፡ በነፃነት የሚለው ጉዳይ መሰመር አለበት፡፡

አሁን ሕዝቡም ራሱ በፖለቲካ መድረክ ላይ ያሉት አማራጮች በአግባቡ ለመገንዘብ ግራ የሚጋባበት ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ የቱ ከየትኛው እንደሚሻል ለማለት ነው፡፡ አሁን ከየት ገንዘብ እንዳመጡ የማናውቃቸው ፓርቲዎች ብዙ ሲጮሁና ሲያስጮሁ እንሰማለን፡፡ ይህን ስታይ ሕዝቡ የሚያነሳውን ጥያቄ ያውቃሉ? ወይስ ብሶት ነው ብለህ ትጠይቃለህ ራስህን፡፡ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሲነዳ የመጣው በብሶትና በቁጭት ነው እንጂ፣ ከፖለቲካ መስመር ወይም ከርዕዮተ ዓለም በመነሳት አይደለም፡፡ ኅብረተሰቡ ውስጥ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ብዙ ምሬት አለ፡፡ ሕዝቡ ብዙ በደል ደርሶበታል፡፡ የንጉሡ ሥርዓት፣ ደርግም ኢሕአዴግም፣ ሌላም ሲመጣ የኢትዮጵያ ነገር የማያልቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰላማዊ መስመር ውስጥ ገብቶ መፍትሔ የተገኘበት ጊዜ ነው ለማለት ብዙ ይቀረናል፡፡ የለውጥ መንግሥት ነኝ ካለው ጋር እኛ ጥል የለንም፡፡ ነገር ግን የመፈጸምና የመተግበር አቅም እንዳነሰው ግን እናያለን፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች አሁንም ሲተውኑ ይታያው፡፡ በተለይም በዕድሜ ገፋ ያላችሁ ፖለቲከኞች ወጣት ፖለቲከኞችን ለምን ማቅረብ ተሳናችሁ? ወጣቱስ ወደ ፖለቲካው ለመግባት ለምን ፈራ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- የፖለቲካ ሕይወት የተመቻቸና አልጋ በአልጋ የሆነ አይደለም፡፡ ትልቅ መስዋዕትነት የሚያስከፍል ነው፡፡ በተለይም ሰላማዊ የፖለቲካ ሒደት የሚባለው ብዙ የማይነገርለት በመሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያውም ብዙ የተጋጋለውን ነገር በመሆኑ የሚፈልገው፣ በተለይም አስከሬኖች ሜዳ ላይ ሲደረደሩና ደም ሲፈስ ዓይነት ጉዳዮችን ነው በብዛት ሽፋን የሚሰጠው፡፡ በሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ውስጥ ብዙ የሰውን ልጅ የሚያዋርዱ፣ በሕይወት ውስጥ ብዙ ችግሮችን የሚጋርጡ ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ብዙም አይነገሩም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ከበሮ በሰው እጅ ያምር…›› እንደሚባለው፣ በቴሌቪዥን ነገሩ ሁሉ ሲደለቅ ዓይተውና ነገሩ አምሯቸው ወደ እዚህ የፖለቲካ ሕይወት ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሲገቡበት የሚደባልቅ ነገር እንዳለ ይታወቃል፡፡ በፖለቲካ ሕይወት ጠንካራ ትግል ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች ማንኛችንም ፖለቲከኞች እንደ አርዓያ ወስደው መንቀሳቀስ የለባቸውም፡፡ በራሳቸው ተነሳሽነት ራሳቸውን ገንብተውና ተዘጋጅተው መሆን አለበት፡፡

በተመሳሳይ የአንድ ፖለቲከኛ ከፖለቲካው ዘወር ማለት ደግሞ ራሱን የሚያስገምተው እንጂ፣ ሌላውን ተስፋ የሚያስቆርጥ መሆን የለበትም፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካ ውስጥ ስንገባ የወሰደውን ያህል ወስደን፣ የሚያስከፍለውን ያህል መስዋዕትነት ከፍለን ለሕዝባችንና ለአገራችን የሚበጁ አማራጭ እናመጣለን ብለን ነው የገባነው፡፡ ከዚያ በኋላ በማን ላይ አኩርፈህ ነው የምትተወው፡፡ ወጣቱ በአሁኑ ጊዜ በቂ ግንዛቤ ሊጨብጥበት የሚችልባቸው ሰፊ ዕድሎች አሉ፡፡ ስለዚህ በሚመቸው መንገድ ቀርቦ ማየትና መገምገም እንጂ፣ እንዲያው ዝም ብሎ የሚነገረውን ነገር ሰምቶ አበባ እንዳየች ንብ መብረር የለበትም፡፡ ቆም ብሎ የፓርቲዎችን ፕሮግራምና ይዘት ማጥናት መመርመር አለበት፡፡ ስለዚህ ወጣቱ በእነ እገሌ ምክንያት ተስፋ ቆርጬ ሳልሳተፍ ቀረሁ ቢለኝ ይህ ከንቱ እምነት ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ተፈጥሮ በሰጠችው ብቃት ልክ መመርመርና ማየት ያስፈልገዋል፡፡ አጀንዳው ኢትዮጵያ ላይ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን ከዚያ ባጠረ ሁኔታ በሌላ መንገድ ተደራጅቶ ለውጥ አመጣለሁ ማለት የበሽታና የቁጭት ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ፓርቲ ሲኬድ በደፈናው መሆን የለበትም፡፡ ቀርቦ፣ ገምግሞና ውስጥ ገብቶ ታግሎ እንጂ እንዲያው የተመቻቸ ቤት ውስጥ ዘው ብሎ አይገባም፡፡ የሚገባበት ቤት ንትርክም ጭቅጭቅም ያለበት ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም ወጣቱ ሁሉንም ማየትና መሞከር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ያደረጉትን አስተዋጽኦ እንዴት ይገልጹታል?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ብዙ አስተዋጽኦ አለ፡፡ የሽግግር መንግሥት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እኛ ከኢሕአዴግ ውጪ የምናስብ ሰዎች ባደረግነው ጥረት፣ ለኢትዮጵያ መብትና ለሕዝቦቿ ክብር ተጋድለናል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ዋዛ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ይህ የሚዘከርበት ወይም የሚዘፈንለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሳይመቸንም ተፅዕኖ ውስጥ ወድቀንም በፅናት ኢሕአዴግን ፍርደ ገምድል ሙሰኛ ብለን አጋልጠን፣ ራሳቸው የኢሕአዴግ ሰዎች በኋላ በሙስና ተዘፍቀናል ሌላ ሆነናል እስከሚሉ ድረስ አድርሰናል፡፡

የእኛ ዓይነት ድምፆች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥርዓት ባይኖሩ ኖሮ ሁኔታው እጅግ በጣም የከፋ ይሆን ነበር፡፡ እኛ የኢሕአዴግን እንከን በአገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማደራጀት ስናጋልጥ ነው የቆየነው፡፡ ድጋፍ ስንሻ አይደለም የቆየነው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልማት፣ ዴሞክራሲ፣ መብትና ክብር እንዲኖር ለማድረግ እንጂ፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ሕዝባችንን አንቅተነዋል፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ጥቅም ጥብቅና ስንቆም ነበር የቆየነው፡፡ በተለይም በኢትዮጵያና በኤርትራ ጦርነት ወቅት፣ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያውያንን ከሥራቸው ሲያሰናብት (ሲያፈናቅል)፣ ኢሕአዴግ በደርግ ጊዜ የነበረውን የኢትዮጵያን ሠራዊት ወንጀለኛ ነው ብሎ ሲያሰናብትና ሲከስ፣ እንደ አየር ኃይል ያሉ ተቋማትን ሲያፈርስና በመሰል ጉዳዮች ላይ ቆመን ተከራክረን የብዙ ኢትዮጵያውያንን ጥቅምና መብት አስከብረናል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሲመራው የነበረው መንግሥት ተፍረክርኮ እንዲወድቅና እንዲንኮታኮት ያበቃው መቼ የተሠራው ሥራ ነው?

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ሽልማት ተበርክቶልዎታል፡፡ እስኪ ስለተደረገልዎት ሽልማት ይንገሩኝ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- እንግዲህ ሁለት ነገሮች አሉ ለበየነ ዕውቅና እንስጥ የተባለበት፡፡ አንደኛው በዳያስፖራ ውሎዬ የሚያውቁኝ ሰዎች ያደረጉትና እናመሠግንዎታለን ባለፉት ዓመታት ላደረጉት አስተዋጽኦ የሚል ነው፡፡ ግማሾቹ የእኔንም ምክር አግኝተው ውጭ አገር ሄደው የስደተኝነት መብት ያገኙ በርካታ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ ወደ ውጭ በምንሄድበት ጊዜ የኢትዮጵያን ማኅበረሰብ አነጋግር ተብዬ የማገኛቸው የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ በራሳቸው ተነሳሽነት ተነስተው ዕውቅና እንስጠው ብለው ገንዘብ አግኝተው፣ በእኔ አቅም ልገዛ የማልችለውን መኪና ገዝተው ሰጥተውኛል፡፡ ሌላው እዚሁ አገር ውስጥ ራሳቸው የተነሳሱ፣ የእኔን ውሎና አካሄድ ሲታዘቡ የነበሩ ነገር ግን በፖለቲካ ሕይወት ምንም ግንኙነት የሌለን ፍቀድልን ላንተ ዕውቅና ለማድረግ ፈልገናል  ብለው ነው፡፡ በተለይ እኔን እንደ ሞዴል ተጠቅመው ለሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በየነ ምን አደረገ? ሌሎች ሰዎችስ ምን ይላሉ? የሚለውን ዓይነት ሐሳብ ይዘው ድጋፍ ለማሰባሰብ በራሳቸው መስመር የጀመሩት ሥራ አለ፡፡ ትልቅ ገንዘብ አሰባስበዋል፡፡ በተመሳሳይ ድግሞ የእኔን ሕይወት የሚዳስስ ዶክመንተሪ ፊልም እያዘጋጁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋለውን የሕግ ጥሰት እንዴት ያዩታል?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አብዲ ኢሌ የሚባለውን ሰው ከሥልጣን ለማውረድ ገብተነው የነበረውን ቀውስ እኛ ነን የምናውቀው፡፡ ከእሱ የባሰው ደግሞ የሕውሓቶች መጣ፡፡ ስለዚህ ነገሮችን አርቀን ማየት አለብን፡፡ ምንድናቸው ይህን ሁሉ ችግር የሚፈጥሩብን የሚለውን፡፡ መንግሥት መቼም ገንቢ የሆነ አቅጣጫ እንዳለው በአደባባይ በሚናገረውም፣ በሚሠራውም እንደምናየው ፈልጎ የሚያጠፋ አይደለም፡፡ አንዳንድ ነገሮች ደግሞ ከአቅም በላይ በመሆናቸው ጊዜ የሚፈልጉና የሚጠብቁ ናቸው፡፡ እውነቱን ለመናገር አሁን ያለው መንግሥት ከሚያደርጋቸው ጥረቶች አልፎ የሚሄድ፣ የኢትዮጵያን ሁኔታ ፀጥና ረጭ አድርጎ ለማስተዳደር የሚችል መንግሥት በአጭር ርቀት የሚመጣ አይመስለኝም፡፡

ይህ ደግሞ እኔ ከሽግግር ወቅት ጀምሮ ያለውን ሁኔታ በማየቴ ነው፡፡ ጥያቄዎቹ አስቸጋሪ ናቸው፡፡ በማትጠብቃቸው ጊዜ ነው የሚፈነዱት፡፡ አንተ ያኛውን መሣሪያ አስፈታለሁ ብለህ ስትታገል ሌላ ቦታ ብቅ ይላል፡፡ መንግሥት ትዕግሥቱስ እንዲያው በንፁህ ህሊና ሲታሰብና ወያኔዎቹ የደረሱበት ሲታይ መንግሥት አልታገሰም? አልሞከረም? በሽምግልና አልጠየቀም? ይህን? ነገር ከቅርብ ርቀት ስለማውቅ ነው የምናገረው፡፡ ፀብ ከሚፈልግ ቡድን ጋር ምን ታደርጋለህ? ሆነ ብሎ ሊጣላህ ይፈልጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ኡ… ኡ… ኡ… ይላል፣ ፈጁን ጨረሱን ለማለት ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ከ28 ዓመታት በላይ የገዙትን ሕወሓቶቹን ራሳቸውንም እየበላቸው ነው፡፡ እኔ ቆም ብዬ ሳስብ በእውነት ኢትዮጵያ በእነዚህ ሰዎች ነበር እንዴ ስትመራ የነበረው እላለሁ፡፡ ይህ ራሱን እንኳ ተደራድሮ ማዳን የማይችል ቡድን፡፡ ከመጀመርያው እንዳልኩህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በእልህ ነው እንጂ በግንዛቤ የሚመራ አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንደኛ ቁጥር ከሚባሉ ዲፕሎማቶች ጋር የዋሉ ሰዎች፣ የኢትዮጵያን አልፎ የአፍሪካን ዲፕሎማሲ በመምራት አገሮች በአኅጉሩ ውስጥ ሲጣሉና ሲቆራቆሱ፣ እገሌ መርቶ መፍትሔ ይፈልጋል ሲባልላቸው የነበሩ ሰዎች በእልህ ምክንያት ራሳቸውን ማዳን አልቻሉም፡፡ እኔ ራሴን ሥልጣን ላይ ባሉ ሰዎች ቦታ ሆኜ ሳስበው የሚያደርጉትን ነገር ዝም ብሎ መፍረድም፣ መፈረጀም ሰማይ አውርድ ዓይነት ነገር ይሆንብኛል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ከምሁራን ጋር ያለውን ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ኢትዮጵያውያን በጣም አስቸጋሪ ሕዝቦች ነን፡፡ በተለይም የተማረ የሚባለው ክፍል፡፡ የፖለቲካ ተጫዋቾቹ ደግሞ ብዙ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፍላጎቱ ደግሞ ጎልቶ የወጣ አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ የሰምና ወርቅ ዓይነት ባህሪ ያላቸው የፖለቲካ አቋሞች ናቸው ያሉዋቸው፡፡ አንዳንዶቹ ለመገመት አስቸጋሪ ናቸው፡፡ በአደባባይ የሚናገረው ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርግ ብዙ ኃላፊነት የተሞላበት ንግግርና ዲስኩር ሲሆን፣ ከጀርባ ደግሞ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሲያደርግ ታያለህ፡፡ ይህን ስታይ ደግሞ የተደበቁ የፖለቲካ አጃንዳዎች የታመቁበት አገር እንደሆነ ታያለህ፡፡ ሁሉም ፖለቲከኛና ክልል ለአደባባይና ለጭብጨባ የማይወጣ ውስጡ አምቆ የያዛቸው ልዩነቶች አሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ አመራር ላይ ያለው አካል እነዚህ ሰዎች ጋር ነው ሙሉቀን ሲወያይ የሚውለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መሪ መሆን የዋዛ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ብለው ያምናሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ምርጫ ማለት ሁልጊዜም መለኪያው ብዙኃኑ ሕዝብ ድምፅ መስጠት ይቻላል ወይ ነው፡፡ ይመዘገባል ተብሎ ከሚጠበቀው 50 ሚሊዮን መራጭ ሕዝብ ስታስበው፣ የትኛውም አገር ቢሆን የተመዘገበ ሁሉ ድምፅ አይሰጥም፡፡ ሰላም አለ ተብሎ በተረጋገጠበት አገርም ቢሆን ሕዝቡ በየራሱ ምክንያት ሄዶ ለምርጫ መሠለፍ ላይፈልግ ይችላል፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ ውስጥ በሚታዩት ችግሮች ምክንያት ሁሉም በየአካባቢው መስጠት ስላልቻለ ምርጫ አይካሄድም ብሎ ማለት አይቻልም፡፡ ድምፅ እሰጣለሁ ብሎ ከተመዘገበው ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ መስጠት ከቻለ ብዙኃኑ መርጧል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያን በማውቃት ልክ በዓይነ ህሊና ብዳስስ መንግሥት ሠራዊቱን ለጥበቃ ማሰማራት ይችላል፣ በየኮሽታው የፀጥታ ኃይሉን ማስፈር ይችላል፡፡ ስለዚህ ምርጫውን ላደናቅፍ ብሎ የሚነሳ ኃይል ይንቀሳቀሳል የሚል ጥርጣሬ ቢኖር የመንግሥትም ኃይል የዋዛ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢሶዴፓ የፖሊሲ አማራጮች፣ የምርጫ ዝግጅቱና እንቅስቃሴው ምን እንደሚመስል ሊነግሩኝ ይችላሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ማንፌስቶ አዘጋጅተን ጨርሰናል፡፡ ለማስተዋወቅ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ የፖለቲካ መስመራችን በተለይም ዋናው ሶሻል ዴሞክራሲ ሲሆን፣ ይህ ማለት ደግሞ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ለዜጎች የሚል ነው፡፡ ከበርቴ ባለሀብቶች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉ ይመሩታል የሚል እምነት የለንም፡፡ መንግሥት በጣም ወሳኝ በሆኑ መስኮች ሚና ሊኖረው ይገባል የሚል አቋም ነው ያለን፡፡ አለበለዚያ ነጋዴው ማኅበረሰብ አብዛኛው ሕዝብ ላይ የፈለገውን ዋጋ እየቆረጠ ከሄደ በኅብረተሰቡ ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡ ወሳኝ ከሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ መንግሥት ጨርሶ መውጣት የለበትም ብለን እናስባለን፡፡ ነፃ ገበያን እንቀበላለን፣ ነገር ግን ይህ ኢኮኖሚ ቁጥጥር ያስፈልገዋል፡፡ አሁን እንደሚታየው ዘይት 400 ወይም 500 ብር ገባ እየተባለ የሚገረውን ነገር ስንሰማ እንዴት አንድ የግል ከበርቴ እናምናለን? በመጋዘን አስቀምጦና አሽጎ ሕዝብን የሚያጉላላና ለረሃብ የሚዳርግ፣ ሰብዓዊነት የሌለውና አገሩን የማይወድ ዓይነት ዜጋ እያየን ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚውን ይምራው የሚባለው የቄንጥ ንግግር ከስንት መቶ ዓመት በኋላ አሜሪካኖቹም ትልቅ ተግዳሮት እየገጠመው ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ገበያን መልቀቅ አያዋጣም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሶዴፓ በምን ያህል የምርጫ ወረዳዎች ይሳተፋል? እርስዎስ የት ይወዳደራሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- እኛ እንደ ፓርቲ ይህ የሶሻል ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ኅብረተሰቡ እስከሚደርስ ድረስ እንታገላለን፡፡ ደላሎችና የውጭ አገር ከበርቴዎች መጥተው በአገሪቱ ልማትን ሳይሆን ሀብታቸውን አካብተው መውጣት የሚፈልጉ፣ በተለይም ትንሽ ዶላር ይዘው ይመጣሉ በሚል የታወረ አስተሳሰብ እናያለን፡፡ ስለዚህ ይህ ዓይነት አመለካከት ለኢትዮጵያ እንደማይበጅ እስኪሰርፅ እንቆያለን፡፡ በዚህ ምርጫ አሸንፈን መንግሥት እንሆናለን የሚል እምነት የለንም፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ አባላት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ በታችኛው ዕርከን ላይ ገብተን ይህን አስተሳሰባችን ለማስረፅ እንሠራለን፡፡ የምንወዳደርባቸው ወረዳዎች ተመዝግበው አልቀው ዋና ቢሮ አልደረሰንም፡፡ ነገር ግን በደቡብ ክልል እስከ 75 በመቶ ድረስ ሊሸፈኑ የሚገባቸውን የምርጫ ክልሎች እየሸፈንን ነው፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ በጅማ ዞን በምዕራብ አርሲ፣ በሐዋሳና ወንዶ ገነት፣ በድሬዳዋ ዕጩዎች አቅርበናል፡፡ እኔ የምወዳደረው 245 ኪሎ ሜትር ርቄ ወደ አርባ ምንጭ ስትሄድ ምሥራቅ በደዋቾ የተወለድኩበት ሾኔ የምትባል ከተማ ነው፡፡ እኛ አቅማችን የተመጠነ ነው፣ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ገንዘብም የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- ከኦፌኮ ጋር በአንድ ላይ መድረክን መሥርታችሁ ስትንቀሳቀሱ ነበር፡፡ አሁን ግን ከኦፌኮ ጋር ባለመስማማት እንደ ወጣችሁ ይነገራል፡፡ ምን ገጠማችሁ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ይህ የመርህ ልዩነት ነው፡፡ መድረክን ሐሳብ ከማመንጨት ጀምሮ አመራር እስከ መስጠት ድረስ ብዙ መስዋዕትነት የከፈልንበት ስብስብ ነው፡፡ መጀመርያ ስምንት ፓርቲዎች ነበርን መድረክን ያቋቋምነው፡፡ እየቆየ አንዳንዱ በየምክንያቱ ተስፋ እየቆረጠ እየተሸራረፈ አራት ደርሰን ነበር፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል ኦፌኮ አንዱ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው የሞቀ እንቅስቃሴ ሰበብ ብዙ ኃይሎች ወደ አገር ቤት ገቡ፡፡ አንዳንድ አክቲቪስቶች ሥራቸውን ትተው የፓርቲ አባል ሆኑ፡፡ ይህ ደግሞ ድሮ አብረን ስንሠራበት የነበረውን መንፈስ ቀየረው፡፡ ኦፌኮ ሄዶ ሄዶ አጀንዳው የአንድ ክልል እስከሚሆን ድረስ ወረደ፡፡ መድረክን ያቋቋምነው አገራዊ አጀንዳ ለማራመድ ነበር፡፡ ነገር ግን ኦፌኮ ከዚያ ወርዶ ጉዳዩ በሙሉ የአንድ ክልል እየሆነ ሲመጣ ስንታዘብ ቆየን፡፡ በውስጥ ትግልም ስንታገልበት ቆይተናል፡፡ በፊት አናስፋው እንጂ እንዲያውም እንዋሀዳለን የሚል አቋም ይዘን ነበር፡፡ ነገር ግን ኦፌኮ አልችልም፣ አልዋሃድም፣ አልተዘጋጀሁም እያለ አሥር ዓመት ሞላው፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በአደባባይ ቃል የገባነው መድረክን መጀመርያ ቅንጅት፣ ቀጥሎ ግንባር፣ ከዚያ ውህድ ፓርቲ እናደርጋለን ብለን ነበር፡፡ ግንባር ድረስ ደርሰን ከዚያ በኋላ አምስት ዓመት አልፈን መቼ ነው ይህ ውህደት የሚመጣው ስንል፣ ኦፌኮ ለውህደት ዝግጁ አይደለሁም ሲል የመለያየት ሥጋት ውስጥ ገባን፡፡

      ያ እንዳለ ሆኖ አሁን በለውጡ ጊዜ የነበሩ ጥሩ ሁኔታዎችን ዓይተን ከመጣው ጋር ሁሉ እየተጣሉ መሄድ አያስፈልግም በሚል፣ ዶ/ር ዓብይ ለሚመራው መንግሥት ድጋፍ ስንሰጥ ቆይተን ነበር፡፡ በመጨረሻ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መጣ፣ ተያይዞም አዋጅ ታወጀ፣ ምርጫው በታቀደለት ጊዜ አይካሄድም ተባለ፡፡ ምርጫ ካልተካሄደ መንግሥት ደግሞ የአምስት ዓመት ዕድሜው ሊያበቃለት እንደሆነ ተረዳን፡፡ ይህንንም ተከትሎ እንደዚህ ዓይነቱ ነገር ሲፈጠር ሕገ መንግሥቱ ምንም ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡ ምንድነው የሚሻለው? ኢትዮጵያን በአሁን ሁኔታ መንግሥት እንደሌላት በማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀምጠውና ተከራክረው በእውነቱ ሊስማሙ ይችላሉ የሚለው ነገር ስናስብ፣ አራምባና ቆቦ የሚናገረው ሕወሓት መቐለ አኩርፎ ተቀምጦ ሌሎችም እዚህ ጦርነት አለ እያሉ እየተነታረኩ ባለበት ጊዜ ይህች አገር ለትልቅ ችግር ትጋለጣለች የሚል ወሳኝ ሁኔታ ላይ ደረስን፡፡ ስለዚህ ከሕገ መንግሥቱ መንፈስ ተነስቶ ይተረጎም የሚለውን ነገርና ተቀበልን፡፡ ኦፌኮ ግን ይህን ሊቀበል አልፈለገም፡፡ እንዲያውም ሌላ አዲስ መንግሥት ይቋቋም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይወያዩ አለ፡፡ የእኛ ሐሳብ ደግሞ ምን ላይ ተቀምጠህ ነው ስለመንግሥት መቋቋም የምትነጋገረው የሚል ነበር፡፡ ኦፌኮ የሚለው ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ መንግሥት የለም ነው፡፡ ያለው መንግሥት ሕገወጥ ነው የሚል ነበር፡፡ የሕገ መንግሥቱ ተርጓሚ ያመጣውን ሐሳብ መተው ደግሞ እኛ ለዚህች አገር ህልውና እንሳሳለን፣ የማይሆን አተካራና ከዚያም ከዚህም ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳረፍ የሚፈልጉ ብዙ ኃይሎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ በሕገ መንግሥት ትርጉም የተባለው ምርጫው በዚህ በአንድ ዓመት ውስጥ መካሄድ አለበት ነው፡፡ በኢሶዴፓ በኩል ለአንድ ዓመት መራዘሙ ምን ሥጋት ያመጣል የሚል እምነት ነበር፡፡ በዚህ አለመግባባት ምክንያት ወደ ምርጫ ለብቻችን መግባታችንን ስንወሰን ወደ መድረክ ስብሰባዎች መሄድ አቆምን፣ በዚያው ተለያየን፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በአሁኑ ጊዜ የፓርቲ ሊቀመንበር፣ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ሥራ አስፈጻሚና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነዎት፡፡ ሥራዎቹን እንዴት ነው የሚያስኬዱት? በተለይም የመንግሥት ተቀጣሪና የተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ሆኖ መቀጠል አይጋጭም ወይ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- እነዚህን ሦስት ነገሮች አጣጥሞና ሰዓት መድቦ መሄድ የነበርኩበት ነው፡፡ ሁሉንም አገናኝቶ ለእያንዳንዱ ሰዓት በመስጠት ብዙ ሥራዎችን ትሠራለህ እየተባልኩ፣ መደበኛ ሥራዬን በሙሉ ጊዜ እየሠራሁ፣ ፓርላማ እየተሰበሰብኩ የኖርኩ ሰው ነኝ፡፡ ለራሴ የማርፍበት ጊዜ አጣ እንደሆን እንጂ በ24 ሰዓት ውስጥ ብዙ ሥራ ለመሥራት የሚያስችለኝ የተፈጥሮ ፅናት አለኝ፡፡ ይህች አዲስ ነገር ተፈጠረች የተባለችዋ የፖሊሲ ጥናት ኃላፊነት አግዘን በሚል ጥያቄ ነው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበልኝ፡፡ ይህ ተቋም ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ውስጥ አይደለም፡፡ ያሉት ተመራማሪዎች ናቸው፡፡ የጥናት ተቋም ነው፡፡ ይህን ተቋም መቀላቀልና ተከታተል የሚል ኃላፊነት መውሰድ እኔ ይህን ያህል የፖለቲካ ሹመት አድርጌ አልወሰደውም፡፡ ሌላ የፖለቲካ ይዘት ቢኖረው ኖሮ እኔ ራሴ ልዩነት ይኖረኝ ነበር፡፡ የዴሞክራት ፓርቲ ተመራጭ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ስለተመረጡ እኮ ሙሉ ለሙሉ የዴሞክራቶችን ተመራጭ ብቻ ይዘው የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትን አያባርሩም፡፡ እኛ ባለን አቅም አገራችን እናገልግል ከተባለ ከተለያዩ ፓርቲዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች መሳተፍ አለባቸው፡፡ በሌላው ዓለም የተለመደ ነው፣ በኢትዮጵያም መለመድ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው›› ሆላንደር ሆላንደር፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና...

ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ክፍለ ዘመንን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሰሞኑን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን...

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል›› ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ተቋማት መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ በበርካታ አጀንዳዎች አማካይነት በተለይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን...

‹‹ኢትዮጵያ ብዙ ፈተና እየገጠማት ቢሆንም ከፈተናው ውስጥ ቀስ እያልን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ›› ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ መካሄዱን ተከትሎ  በቀደሙት ጊዜያት ከተቋማዊ ስሙ ባለፈ በሚያከናውናቸው ተግባራት፣ ተቋሙን ይመሩት በነበሩ ኮሚሽነሮች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ተቋማዊ ባህሪው ከአስፈጻሚው...