Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለከፍተኛ ወጪ የተዳረጉት ክለቦችና ሊጉ ያለበት መልካም ጎን

ለከፍተኛ ወጪ የተዳረጉት ክለቦችና ሊጉ ያለበት መልካም ጎን

ቀን:

በዓመታዊ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ክሶች፣ ንትርኮች፣ ውንጀላዎች እንዲሁም የማይፈጸሙ ግን ቃል የሚገቡ በርካታ ሪፖርቶችን ማቅረብ የሊጉ መለያ እስኪመስል ድረስ አብሮት ዘልቋል፡፡ በሜዳ ላይ ከሚታየው ጨዋታ ይልቅ የፖለቲካ እንዲሁም የክለቦች የእርስ በርስ ጉሽሚያዎችን በየመድረኩ መመልከት የተለመደ ነበር፡፡ በያንዳንዱ ጨዋታ እንደ ቀልድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብሮች የሚፈሱበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ የፖለቲካና የብሔር መሸሸጊያ ሆኖ ነበር፡፡

ተሳታፊ ክለቦች ‹‹ጠላቴ ነው፣ ወዳጄ ነው›› የሚሏቸውን ክለቦች በኪሳቸው ይዘው ከቦታ ቦታ እየዞሩ፣ በደጋፊዎች አይዞህ ባይነት የመወዳደሪያ ሜዳዎችን ወደ ግጭት ዓውድማ መቀየራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ከጀመረ 23ተኛ ዓመቱን የያዘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣ ራሱን በካምፓኒ መሠረት ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ፣ በአንፃሩም ቢሆን የራሱን ችግር መመልከትና ችግሩንም በራሱ መፍታት የቻለበት አቅም ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል፡፡

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት 17ተኛ ሳምንት ላይ ተቋርጦ የነበረው የዓምናው የሊጉ ውድድር፣ ዘንድሮ በ13 ክለቦች በአዲስ ፎርማት እንዲሁም በዲኤስቲቪ ጭምር መተላለፍ ጀምሯል፡፡

ዓምና የተመሠረተው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒ ከዲኤስቲቪ ጋር የአምስት ዓመት የስፖንሰርሺፕ ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል፡፡ ይኼም ስምምነት በሊግ ካምፓኒው ሥር የሚተዳደሩ ክለቦች የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች በቴሌቪዥን መስኮት ከመተላለፋቸው በሻገር፣ በየዓመቱ በሚከፈላቸው ክፍያ አማካይነት የጥቅም ተቋዳሽ መሆን ችለዋል፡፡

በዘንድሮው ውድድር በተለያዩ ከተሞች እየተሳተፉ የሚገኙት 13 ክለቦች በአዲስ አባባ ስታዲየም የጀመሩትን ጨዋታ፣ በጅማ ከተማ፣ በባህር ዳር እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ ቆይታቸውን አድርገው የመጨረሻ የሊጉን ጨዋታቸውንም በሐዋሳ ከተማ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሊግ ካምፓኒው የጥናት ቡድን የተገመገሙት እነዚህ ከተሞች እያንዳንዳቸው የአምስት ሳምንት ጨዋታዎችን ያስተናግዳሉ፡፡ በዚህም መሠረት በአንድ ከተማ ላይ ከ28 ቀናት በላይ ይቆያሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከሜዳቸው ውጪ ለሚኖር ጨዋታ በእንግድነት በሚያመሩበት ከተማ ቢበዛ የአምስት ቀናት ቆይታ ብቻ ይኖራቸው ነበር፡፡

ሊግ ካምፓኒው ከጤና ሚኒስቴር ጋር ባደረገው ውይይት መሠረት፣ የኮሮና ወረርሽኝ ፕሮቶኮልን ለመጠበቅ በመረጣቸው አምስት ከተሞች ጨዋታዎቹ እንዲደረጉ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ክለቦች በተለያዩ ከተሞች ለሳምንታት ቆይታ በማድረግ ውድድሮችን እንዲያከናወኑ ቢደረግም ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋቸው እንደሆነ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

የዘንድሮ የመጀመርያ አምስት ሳምንታት ጨዋታን በአዲስ አባባ ካከናወኑ በኋላ፣ ወደ ጅማ ያቀኑት ክለቦቹ በ28 ቀናት ቆይታቸው እያንዳንዱ ክለብ ከ650 ሺሕ ብር እስከ 900 ሺሕ ብር ድረስ ማውጣቱ ተገልጿል፡፡

የጅማ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የጅማ ሆቴል ባለንብረቶች ፕሬዜዳንት አቶ ቴድሮስ ደበላ አስተያየት ከሆነ፣ በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሉች ክለቦችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያስተናገዱ ማድረጋቸውን ያብራራሉ፡፡ ምንም እንኳ ሆቴሎቹ በኮሮና ወረርሸኝ ምክንያት ለወራት በደንበኛ ድርቅ ተመትው መቆየታቸውን የሚገልጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ሆቴሎቹ ቁርስ፣ ምሳ፣ ራትና አልጋን ጨምሮ ከ650 ብር እስከ 1,000 ብር ድረስ አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹የከተማችን በጎ ገጽታ ለማሳየት እንዲሁም፣ የተሰጠንን ዕድል መጠቀም እንዳለብን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሆቴሎቻችን ክለቦችን ሳይጎዱ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፤›› በማለት አቶ ቴድሮስ ደበላ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ክለቦች ጨዋታ ከማድረጋቸው አስቀድሞ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው በሚጠቅሰው የጤና ሚኒስቴር ፕሮቶኮል መሠረት ክለቦች ለምርመራ ብቻ ክፍተኛ ወጪ እንደሚያወጡ ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ለአንድ ጊዜ ምርመራ ብቻ ከ1,200 ብር እስከ 1,800 ብር ድረስ ሲያወጡ እንደነበር ያብራራሉ፡፡ በአንፃሩ በጅማ በነበራቸው ቆይታ የከተማው እግር ኳስ፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ በጅማ ከተማ ካለው የማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት ጋር በመነጋገር ክለቦቹ ለአንድ ጊዜ ምርመራ 500 ብር ብቻ እንዲጠየቁ  መወሰናቸውን አቶ ቴድሮስ ያስረዳሉ፡፡

ውድድሮች በየከተማው መደረጋቸው ለከተማዎቹ ምጣኔ ሀብት እንደ መልካም ጎን ቢታይም፣ በአንፃሩ በመንግሥት ካዝና ለሚተዳደሩ በርካታ ተሳታፊ ክለቦች ግን ወጪው ምጥ እንደሆነባቸው አልሸሸጉም፡፡ በዘንድሮ ውድድር ጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ፋሲል ከነማ ጅማ በነበረው የ28 ቀናት ቆይታ፣ ከ800 ሺሕ  እስከ 900 ሺሕ ብር ድረስ የሚገመት ገንዘብ ማውጣታቸውን አቶ ሀብታሙ ዘውአለ የፋሲል ከነማ ቡደን መሪ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ለዚህም ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ምክንያቶችን ሲያስቀምጡ በአንድ ከተማ ላይ ለሚኖራቸው ቆይታ ሙሉ ተጫዋቾችን ጨምሮ፣ የቡድን መሪ፣ በቂ የሕክምና ባለሙያን ጨምሮ ከ32 በላይ የቡድኑ አባል አብሮት የሚጓዝ ሲሆን፣ የሜዳ ክፍያ ወጪንም ማካተቱ ወጪውን ክፍተኛ እንደሚያደርገው ይጠቅሳሉ፡፡ እንደ ቡድን መሪው አስተያየት ከሆነ፣ በተለይ የሜዳ ክፍያ የበለጠ ውጪውን ከፍ እንደሚያደርግና ከዚህ ቀደም ባለሜዳው ሜዳውን ስለሚፈቅድ ተጨማሪ ክፍያ ሆኖ እንደማያውቅ ያስታውሳሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ መርሐ ግብር መሠረት ጨዋታ ለማድረግ ወደ አንድ ከተማ ሲያቀኑ፣ እንደ ርቀቱ ከ100 ሺሕ ብር እስከ 500 ሺሕ ብር አጠቃላይ  ወጪ እንደሚያደርጉ ይነገራል፡፡ ይኼም ሆቴልን ጨምሮ፣ የአውሮፕላን፣ የዳኛ ክፍያ፣ የሜዳና የተለያዩ ወጪዎችን ያካትታል፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ክለቦች በከፍተኛ በጀት ዕጥረት ምክንያት ከተጫዋቾች ክስ ሲቀርብባቸውና ውጤታቸው እያሽቆለቆለ ሲመጣ መመልከት እየተለመደ የመጣ ቢሆንም፣ ሊግ ካምፓኒው ከምንጊዜውም በላይ ቀድሞ የነበሩበትን ችግሮች በመጠኑም ቢሆን መፍታት መቻሉና ራሱን በራሱ ማስተዳደር መቻሉ እንደ መልካም ጎን እየታየ ይገኛል፡፡

እንደ አቶ ሀብታሙ አስተያየት ከሆነ፣ በየጨዋታው ላይ ፈሰስ ከሚያደርገው  ከፍተኛ ገንዘብ ባሻገር አሁን ላይ ለዘመናት በሊጉ ላይ ሲታዩ የነበሩ የዳኝነት ችግሮች መቀረፍ መቻላቸውና ተጫዋቾችም ራሳቸውን ለዓለም አቀፍ እግር ኳስ ገበያ ማቅረብ መቻላቸው መልካም ጎኑ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

ከዚህም በተለየ ሊግ ካምፓኒው ከዲኤስ ቲቪ ጋር ለአምስት ዓመት  በተፈራረመው ስምምነት  መሠረት 22.5 ሚሊዮን ዶላር ክፍያን ያገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ በዚህ የውድድር ዓመት ከሚከፍለው ክፍያ ውስጥ ከታክስ በኋላ 50 በመቶ ለ13 ክለቦች እኩል የሚከፋፈል፣ 25 በመቶ ደግሞ ክለቦች በሚያስመዘግቡት ውጤት መሠረት የሚከፈል ሆኖ፣ ቀሪው 25 በመቶ ከፍያ ደግሞ 15 በመቶ ለሊግ ካምፓኒው፣ አሥር በመቶ ደግሞ ለባለሜዳ ክለቦች የሚከፋፈል ይሆናል፡፡

በዚህም መሠረት የሊግ ካምፓኒው የመጀመርያውን የሁለት ሚሊዮን ዶላር ክፍያ በመጀመርያው ዙር ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ይኼ ለሦስት አሠርታት ለዘለቀው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጉዞ ውስጥ አንድ ዕርምጃ መራመድ የቻለበት ወቅት እንደሆነ ሁሉም ይስማማል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...