የአዲስ አበባ ከተማ አስተደዳር በከተማዋ ያጋጠመውን የዋጋ ግሽበት ለማስተካከል በማለት የመደበውን የ500 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር፣ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ለሁሉም ክፍላተ ከተሞች የሸማቾች ማኅበራት እንደሚለቀቅ፣ የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አረጋ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የከተማ አስተዳደሩ በዚህ አስፈላጊ ወቅት የመደበውን የተዘዋዋሪ ብድር በተጨባጭ ለሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ለማዳረስ፣ ለሁሉም ክፍላተ ከተሞች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ግልጽ የሆነ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በዚህም ከተያዘው ሳምንት ጀምሮ በአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በኩል የሸማቸቾች ማኅበራት የባንክ ሒሳብ እየከፈቱ ለምርት ግዥ አገልግሎት የሚፈልጉት የገንዘብ መጠን በኤጀንሲው ተገምግሞ ከፀደቀላቸው በኋላ፣ ከባንክ የሚወስዱበት አሠራር እንደተመቻቸ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በፊት በአምራቾችና በሸማቾች መሀል የሚገባው ደላላ ለዋጋ ግሽበቱ መባባስ ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ በቀጣይ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በቀጥታ ከአምራቾች ወይም የግብርና ምርት ከሚያቀርቡ ከአዲስ አበባ ውጪ ከሚገኙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በሚፈጠር የገበያ ትስስር፣ የግብርና ምርቶችን ወደ ከተማ የማስገባት ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡
ጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በኅብረት ሥራ ማኅበራቱ እንደሚሠራጩ የገለጹት አቶ ሲሳይ፣ ሥርጭቱን ፍትሐዊ ከማድረግ አንፃር ኅብረተሰቡ የግብርና ምርቶችን በሚቀመጥለት የቀን ሰሌዳ ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ሱቆች ይሸምታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም ምርቱን በጥሬው ገዝቶ ብቻ መገልገል ስለማይቻል፣ በሸማቾች ማኅበራት በሚገኙ የወፍጮ ቤቶች በመገልገል አገልግሎቱን እንደሚያገኙ አስታውቀዋል፡፡
ሪፖርተር በተለያዩ የአዲስ አበባ ገበያዎች የምግብ ምርቶችን ዋጋ እንደተረዳው ነጭ ጤፍ ከ4,600 እሰከ 5,000 ብር፣ ሠርገኛ ጤፍ ከ4,300 እስከ 4,500 ብር፣ ቀይ ጤፍ ከ4,200 አስከ 4,400 ብር፣ በቆሎ ከ1,900 እስከ 2,000 ብር፣ እንዲሁም ስንዴ ከ2,800 እስከ 3,000 ብር በኩንታል እየተሸጡ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የዋጋ አለመረጋጋት ለማስታገስ የ500 ሚሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ብድር መፍቀዱ የሚታወስ ሲሆን፣ በተጨማሪም የሸማቾችን መብት ማስከበር የሚያስችሉ የሸማች ማኅበራትን ለማቋቋም ከተማ አቀፍ ንቅናቄ እያካሄደ መሆኑ ታውቋል፡፡