Saturday, March 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበመንግሥት ተቋማት ለንብረት ትኩረት በማይሰጡ ኃላፊዎች የሕዝብ ሀብት እየባከነ መሆኑ ተገለጸ

በመንግሥት ተቋማት ለንብረት ትኩረት በማይሰጡ ኃላፊዎች የሕዝብ ሀብት እየባከነ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

ከ10,000 በላይ ተሽከርካሪዎች ሜዳ ላይ ሳር በቅሎባቸዋል

በኢትዮጵያ በበርካታ የመንግሥት ተቋማት በኃላፊነት ደረጃ የተቀመጡ ግለሰቦች  ለሀብትና ለንብረት ትኩረት ስለማይሰጡና በክትትል ጉድለት ማነስ፣ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር የሕዝብ ሀብት እየባከነ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ፣ የንብረት አስተዳደርና የግዥ አፈጻጸም ሥርዓት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ተቋሙ በጉዳዩ ላይ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር ሐሙስ የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር አዳራሽ ውይይት አካሂዶ ነበር፡፡

በውይይቱ በመንግሥት ሀብት ማስተዳደርና ቁጥጥር ላይ ያሉ ችግሮችን አስመልክቶ፣ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የግዥና ንብረት አስተዳደር ዲፓርትመንት አስተዳደር መምህር ቢኒያም በርሄ (ዶ/ር) የመነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

በተለይ በጣም ዝቅተኛ የሆነ የሀብት ምዝገባ ሥርዓት፣ ያልተፈለገ ግዥ፣ ሥርዓት የሌለው የሀብት አጠቃቀም፣ የንብረት መሰረቅና መጥፋት፣ ድግግሞሽ የበዛበት ቆጠራና የሀብት አወጋገድ ሥርዓት አለመኖር በዋነኝነት ለሕዝብ ሀብት መባከን እንደ ዋና ምክንያት ናቸው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የተቋማት የበላይ ኃላፊዎች ለሚገዙ ንብረቶች እንጂ በመጋዘን ለተቀመጡና አገልግሎት ለማይሰጡ የሕዝብ ሀብቶች ተቆርቋሪ አለመሆን፣ ኃላፊዎች አባክነው ሲገኙም ግልጽ የሆነ የተጠያቂነት ሥርዓት አለመኖር እንደ ትልቅ ችግር ተጠቅሷል፡፡

በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚገኙና በከፍተኛ ሁኔታ ሳይቆጠሩ ወይም ሳይመዘገቡ ሜዳ ላይ ወይም አልባሌ የቆርቆሮ መጋዘን ውስጥ ይገኛሉ ተብለው ከተዘረዘሩት ንብረቶች ውስጥ፣ ተሽከርካሪዎች፣ ማሽነሪዎች፣ ኮምፒዩተሮች፣ የፎቶ ኮፒ ማሽኖች፣ ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮች፣ መደርደሪያዎች፣ ብረታ ብረት፣ ማሽነሪዎችና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

እነዚህ ንብረቶች በብድር፣ በዕርዳታ ወይም በዓመታዊ በበጀት የተገዙ መሆናቸው፣ አንዳንዶቹ አዳዲስ ሌሎች በትንሹ መጠገን የሚችሉ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ሊወገዱ የሚችሉ እንደሆኑ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ ተናግረዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ከ10,000 በላይ መኪኖች በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሜዳ ላይ ሳር በቅሎባቸው እንደሚገኙ አቶ ሃጂ አክለው ገልጸዋል፡፡

ያለ ምንም አገልግሎት በየመጋዘኑና በሜዳ ላይ ታጭቀው ይገኛሉ የተባሉት አብዛኞቹ ንብረቶች ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የተቀመጡ እንደሆኑ፣ ከዚያ ሲያልፍም አንዳንዶች በልጅ እያሱ ዘመን ተገዝተው የተቀመጡ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

ኤጀንሲው በአገር ደረጃ በየመንግሥት ተቋማቱ ያለ ምንም አገልግሎት የተቀመጡ የሕዝብ ሀብቶችን ለመመዝገብ ‹‹አገር አቀፍ የምዝገባ ሳምንት›› ከሚያዝያ 4 እስከ ሚያዝያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚያካሂድ፣ ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...