የኦሮሚያ ቡና አርሶ አደሮች ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ በ300 ሺሕ ብር ካፒታል በ1991 ዓ.ም. ሲቋቋም 25 መሠረታዊ ማኅበራት ብቻ ነበሩት፡፡ አሁን ላይ በኦሮሚያ ክልል ከወለጋ፣ ኢሉአባቡር፣ ጂማ፣ ጉጂ፣ አርሲ፣ ባሌ እና ሐረርጌ የተወጣጡ ከ402 በላይ መሠረታዊ ማኅበራትን በአባልነት አቅፏል፡፡ ማኅበሩ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በአባልነት ማሳተፍ የቻለ ሲሆን፣ ካፒታሉም 600 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ስለ ኅብረት ሥራ ማኅበሩ እንቅስቃሴ ዳዊት ቶሎሳ ምክትል ሥራ አስኪያጁን አቶ ደጀኔ ሂርጳን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ የቡና ምርቱን በዓለም ገበያ እንዲተዋወቅ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እንደሚሠራ ይታወቃል፡፡ እንቅስቃሴው ምን ይመስላል?
አቶ ደጀኔ፡- ማኅበሩ ከተቋቋመ በኋላ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካካል ከፊንላንድ በጎ አድራጎት ድርጅት ፌርትሬድ አፍሪካ ጋር በአጋርነት እየሠራ ይገኛል፡፡ ፌርትሬድ አፍሪካን ከመሠረቱት አራት የአፍሪካ አገሮች ተቋማት አንዱ የኦሮሚያ ቡና አርሶ አደሮች ኅብረት ሥራ ማኅበር አንዱ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከተለያዩ ዘጠኝ አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሥራቱ የምስክር ወረቀት ማግኘት ችሏል፡፡
በእነዚህም ምስክርነቶች ማኅበሩ የቡና ምርቱን በተሻለ ዋጋ እንዲሸጥና አርሶ አደሩ በቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ መክፈት ችሏል፡፡ የቡና ምርታችን በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተፈላጊ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ አርሶ አደሩ ምርቱን በዘመናዊ መንገድ እንዲያመርት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊትም ስኬታማ ሥራዎችን በመሥራቱ በአፍሪካ የጉና ሽልማትን መጎናፀፍ ችሏል፡፡
ሪፖርተር፡- ምርቱን በዓለም አቀፍ ገበያ ከማስተዋወቅ ባሻገር አርሶ አደሩና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረገበት አጋጣሚ አለ?
አቶ ደጀኔ፡- ማኅበሩ ለዓለም ገበያ በፌርትሬድ ስም በሚያቀርበው ቡና ላይ ከሚሸጥበት ዋጋ ተጨማሪ ብር በቀጥታ ማኅበሩ ያገኛል፡፡ ይኼ ሳንቲም ለገበያ በቀረበው የኩንታል ቡና መጠን የሚከፈል ‹‹ፕሪሚየም›› የተባለ ክፍያ ነው፡፡ ክፍያው በቀጥታ ለአርሶ አደሩና በአካባቢው ላለው ማኅበረሰብ አገልግሎት የሚውል ነው፡፡
ከእነዚህ አጋር ድርጅቶች በተገኘው የፕሪሚየም ገንዘብ አማካይነት አርሶ አደሩ በሚገኘበት አካባቢ የጤና ኬላ፣ ትምህርት ቤት፣ ውኃ፣ የቡና ማጠቢያ፣ የቡና መፈልፈያ፣ ተሽከርካሪዎችና የመንገድ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2019 ድረስም በአጠቃላይ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ከፕሪሚየም ክፍያ ተገኝቶ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
ለምሳሌ መንግሥት ሊገነባባቸው ያልቻለባቸው አካባቢዎች፣ እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ትምህርት ለማግኘት ረዥም መንገድ ሲጓዝ ከነበረበት ሥፍራ በቅርብ ቦታ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ተችሏል፡፡ እስካሁንም ድረስ ወደ 11 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጎ ከስድስት ትምህርት ቤቶች በላይ ገንብቷል፡፡ የጤና ኬላዎችን ለማግኘት ረዥም መንገድ ሲጓዝ የነበረውን ማኅበረሰብ ችግር ለመፍታትም ከሦስት በላይ ትልልቅና አነስተኛ የጤና ኬላዎችን መገንባት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም አርሶ አደሩ ምርቱን ቶሎ ለገበያ እንዲያቀርብ ከአንድ ኪሎ ሜትር እስከ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ መንገድ ተገንብቷል፡፡
ሪፖርተር፡- አርሶ አደሩ የቡና ምርቱን በዘመናዊ መንገድ የማምረት ሒደትና ማኅበሩ እየከወናቸው ያሉ ተግባራት ምን ይመስላሉ?
አቶ ደጀኔ፡- አብዛኞቹ ማኅበራት ፋብሪካ አልነበራቸውም፡፡ አሁን 222 የደረቅና ርጥብ ቡና መፈልፈያና ማጠቢያ ፋብሪካዎች ተገንብተዋል፡፡ እነዚህ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ ቀድሞ አርሶ አደሮቹ የነበረባቸውን ችግሮች ማቃለል ችለዋል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ 25 ማኅበራት የችግኝ ማፍያ ፕሮጀክቶችን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የማኅበሩ ዓለም አቀፍ የቡና ገብያ ድርሻ እንዴት ይገመገማል?
አቶ ደጀኔ፡- አጠቃላይ የኢትዮጵያ የቡና ገበያ ከዓለም የቡና ገበያ አንፃር ሲገመገም፣ እንደሌሎቹ አገሮች እያደገ ነው ማለት ያዳግታል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ብራዚል፣ ኮሎምቢያና ቬይትናም በአማካይ የሚያቀርቡትን ቡና ስንመለከት የኢትዮጵያ አነስተኛ ነው፡፡ በአንፃሩ የኢትዮጵያ ቡና ውድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ምርቱ ዝቅተኛና ውድ መሆን የገበያ መጠኑ ላይ ተፅዕኖ አድርጓል፡፡ ይኼም በሔክታር ከሰባት ቶን በላይ ማለፍ አላስቻለንም፡፡ ሌሎች አገሮች ከ16 እስከ 18 ቶን ድረስ ያመርታሉ፡፡ ጎረቤት አገሮች ኬንያና ዑጋንዳ እንኳ ከኢትዮጵያ በምርት ይበልጣሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የኦሮሚያ አርሶ አደሮች ኅብረት ሥራ ማኅበር ያለፉት አምስት ዓመታት ጉዞ ስንመለከት ይኼ ነው የሚባል የመጠን ለውጥ አለው ማለት አይቻልም፡፡
ማኅበሩ በዓመት ሰባት ሺሕ ቶን ቡናን ያቀርባል፡፡ ይኼም ማለት በዓመት 1.2 ቢሊዮን ብር ገቢ ያስገኛል ወይም ያንቀሳቅሳል፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታትም 36 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ አስገኝቷል፡፡ ይኼ ማለት ግን የዓመት የሽያጭ መጠኑ ጨምረዋል ማለት አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ማኅበሩ ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካይ 70 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡
ሪፖርተር፡- ቡናን በጥሬው ለገበያ ከማቅረብ ባሻገር እሴት ጨምሮ ከመሸጥ አኳያ የነደፈው ዕቅድ አለ?
አቶ ደጀኔ፡ ማኅበሩ ላለፉት አምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ውጥን ወጥኖ የቡና ፋብሪካ ለመገንባት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ዓምና በ50 ሚሊዮን ብር ግንባታውን አጠናቆ ቡናን ቆልቶ፣ ፈጭቶና አሽጎ ማቅረብ ጀምሯል፡፡ ‹‹ዋን ኮ ኮፊ›› የሚል ስያሜ ያለው የተፈጨ ቡናው፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርፖርት ሱቅ ውስጥ ለሽያጭ አቅርቧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ የተለያዩ ሥፍራዎችና በድሬዳዋ ካፌዎችን ከፍተናል፡፡ ስለዚህ ቡናን በጥሬው ከመሸጥ ባሻገር እሴት ጨምረንም በመሸጥ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሠራን እንገኛለን፡፡