Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ሸቀጦች በንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በኩል ሊቀርቡ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግዥ አዋጅ ተሻሽሎ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኳል

ከጥቂት ሳምንታት በፊት መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ካደረገ በኋላ  ለተከሰተው የሸቀጦች አቅርቦት፣ እጥረትና የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት፣ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአለ በጅምላ መጋዘኖች አማካይነት ለኅብረተሰቡ እንደሚቀርቡ ገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

 ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት የተንዛዛውን የግዥ ሥርዓት በመተው ከትልልቅ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ሸቀጦች ተገዝተው ለትልልቅ የመንግሥት ድርጅቶች እንዲቀርቡና ለሕዝቡ በቶሎ የሚደርሱበት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ የገለጹት የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

‹‹ሥራው በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ በመሆኑ ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፤›› ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰተውን የዳቦ እጥረት ለመቅረፍ ከውጭ አገር ስንዴ ተገዝቶ እየገባ እንደሆነ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በገበያ ዋጋ እንደሚያቀርብ አስረድተዋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከየካቲት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ማስተካከያ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በዚህም በሁሉም በአገር ውስጥ በሚመረቱና ከውጭ አገር በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ሲታይ፣ አንዳንዶቹ ከገበያ እየጠፋ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

አጠቃላይ አገራዊ ምርቱን ከማሳደግ ባለፈ አንዱ የመንግሥት ኃላፊነት ገበያው ውስጥ የተለያዩ ክፍተቶች ሲፈጠሩ የማረጋጋት ሥራ ይከናወናል ሲሉ እዮብ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጋር በመሆን፣ የተፈጠረውን የዋጋ ጭማሪና የነዳጅ ዋጋ ያመጣውን ጫና እየገመገመ እንደሆነ አክለው ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የነዳጅ ዋጋ አሁንም ወደ 24 ቢሊዮን ብር እየተደጎመ በመሆኑ፣ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አስቸጋሪ እንደሆነ እዮብ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የተደገረው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አገሪቱ ከምታደርገው ድጎማ አንፃር መጠነኛ ማስተካከያ እንጂ፣ ነዳጅ ጨመረ በሚል የሚገናኘውንም የማይገናኘውንም ዋጋ እንዲጨምር እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ አካላት ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃ በመውሰድ፣ የንግድ ሰንሰለት ችግሩ ይፈታል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

እዮብ (ዶ/ር)  አገሪቱ አሁን እየተጠቀመችበት ያለው የግዥ አዋጅ ትልቅ ችግር ያለበት፣ የተንዛዛና ረዥም ሒደትን የሚጠይቅና በፕሮፎማ ላይ ያተኮረ በመሆኑ፣ መሠረታዊ ማሻሻያ ተደርጎበት አዲስ አዋጅ እንዲወጣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ገልጸዋል፡፡

ተሻሽሎ የቀረበው የግዥ አዋጅ አሁን በሥራ ላይ ያለውንና አላሠራ ያለውን አካሄድ በመቀየርና ዘመናዊ በማድረግ፣ በተለይም በግዥ ጨረታ ወቅት አቅም የሌላቸው ተወዳዳሪዎች ሲሳተፉበት የነበረውን አሠራር በመቀየር ትልቅ ለውጥ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡

በመጪዎች ጥቂት ሳምንታት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ፓርላማው ለክረምት ዕረፍት ከመውጣቱ በፊት ያፀድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አክለው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች