Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹የአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱ ማንም መንግሥት ሆኖ ተመርጦ ቢመጣ ሊቀበለው የሚችል ነው›› ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽነር

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱ ማንም መንግሥት ሆኖ ተመርጦ ቢመጣ ሊቀበለው የሚችል ነው››

ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽነር

በመጪዎቹ አሥር ዓመታት በተለያዩ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ይተገበራል ተብሎ የተዘጋጀው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ፣ ምንም ዓይነት መንግሥትና የመንግሥት ሥርዓት ቢመጣ ሊቀበለው የሚችል ሆኖ እንደተዘጋጀ የፕላንና ልማት ኮሚሽነር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ኮሚሽኑ ባዘጋጀው መሪ ዕቅድ ላይ ከተለያዩ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር ለበርካታ ወራት ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይሁንታ አግኝቶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ እየተጠበቀ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የተዘጋጀውን የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ የክትትልና ግምገማ ሥርዓት በተመለከተ፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ጋር ዓርብ የካቲት 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ውይይት ተካሂዷል፡፡

ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የፕላንና ልማት ኮሚሽነር የተዘጋጀው የአሥር ዓመት ዕቅድ ከፖለቲካዊና ከፓርቲ ወገንተኝነት የፀዳ መሆኑን ማረጋገጫ ምን እንደሆነ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት ኮሚሽነሯ፣ ‹‹የአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱ ማንም መንግሥት ሆኖ ተመርጦ ቢመጣ ሊቀበለው የሚችል ነው፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ መሪ ዕቅዱ የአንድን መንግሥት በሥልጣን ላይ የሚያቆይ ዕድሜ ያላማከለ ከመሆኑም በላይ፣ መንግሥት ወይም መንግሥትን ከሚመራ ፓርቲ ጋር ያልተገኘ በመሆኑ የሕዝቡን የልማት፣ የዕድገትና የብልፅግና ፍላጎት ማሳካት እንዲቻል ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡

ዕቅዱን ለማስፈጸም በአካሄድ ረገድ ሊለያይ ይቻል ይሆናል እንጂ፣ የዕቅዱ አዘገጃጀት ማንም ሊቀበላቸው የሚችሉ የልማት ግቦችን መያዙን ኮሚሽነሯ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ እንደ ግብ የተያዘው የጋራ ዕድገትና ብልፅግናን እንዲሁም ልማትን ማምጣት የየትኛውም አገርና ሕዝብ ዕቅድ ፍላጎት መሆኑን ግምት ውስጥ ያስገባ ነው ሲሉ  ፍፁም (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ከፓርላማ አባላት ጋር እየተደረገ ያለው ውይይት ሥርዓትን ከመገንባት ዕሳቤ  የመነጨ እንደሆነ፣ ዕቅዱን በምርጫ አሸንፎ የሚመጣው መንግሥት በቀላሉ እንዲያስፈጽመው ተደርጎ መዘጋጀቱን ኮሚሽነሯ አስረድተዋል፡፡

የዕቅዱን ተቀባይነትና ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ሲባል በፊት ቢሮ ውስጥ ብቻ ተዘጋጅቶ ለትግበራ ሲቀርብ እንደነበረው ሳይሆን፣ ለበርካታ ወራት ከሕዝብና ከበርካታ የሚመለከታቸው የመንግሥትና የግል ዘርፍ ተዋንያን ጋር በበቂ ሁኔታ ውይይት እንደተደረገበት ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ስለአሥር ዓመት ዕቅዱ ገለጻ ሲያደርጉ በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት እንዲያግዝ፣ የዕቅዱን አፈጻጸም ለመከታተልና ድግግሞሽን ለማስቀረት ጠንካራ የሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት በመዘርጋት አፈጻጸሙን በሚገባ መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

‹‹ተቋማትን የምንቆጣጠርበትና ሀብት የምናስተዳድርበት ሥርዓት መገንባት ከቻልን፣ ማንም ሄደ ማንም መጣ አገርን ማስቀጠል ይቻላል፤›› ሲሉ አቶ ታገሰ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም የዕቅዱን ተግባራዊነትና አፈጻጸም፣ እንዲሁም ዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክትትልና የግምገማ ሥርዓቱን ጠንካራ ማድረግ ይገባል ሲሉ አፈ ጉባዔው አሳስበዋል፡፡

ከ2013 ዓ.ም. እስከ 2022 ዓ.ም. ድረስ የሚተገበረው የልማት ዕቅድ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ገበያ መር የኢኮኖሚ ሥርዓት በመከተል የግል ዘርፍን ተሳትፎ ማሳደግ፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ መፍጠር ምርታማነትን ማሳደግ፣ ጥራትና ተወዳዳሪነትን በማጎልበት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት፣ የማኅበራዊ መሠረተ ልማት ተደራሽነትን ማሳደግ፣ ሰላምና ፍትሕ የሚያረጋግጥ ጠንካራ ሥርዓት መገንባት የሚሉ ዓላማዎችን የያዘ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች