Wednesday, June 19, 2024

በተስፋ ፋንታ በሥጋት መኖር እየከበደ ነው!

በኢትዮጵያ በተስፋ የተሞሉ መልካም ነገሮች እንዳሉ ሁሉ፣ በሥጋት የተሞሉ ክፉ ነገሮችም አሉ፡፡ የአገራቸው ዕጣ ፈንታ ከሚያሳስባቸው ቅን ዜጎች ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ የተባሉ ስመ ጥሩዎች ድረስ፣ የኢትዮጵያን ተስፋና ሥጋቶች በተለያዩ ፈርጆች ይተነትናሉ፡፡ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮቿን በመፍታት የአፍሪካ ቀንድን ማዋሀድ የሚያስችል አቅም እንዳላት ሲነገር፣ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ብትንትኗ ሊወጣ እንደሚችል መላምት ይቀርባል፡፡ የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታዋን በትኩረት የሚከታተሉ ደግሞ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንዳለች ይገነዘባሉ፡፡ ተስፋና ሥጋትን በእኩል ዓይን በማየትና ለመፍትሔ በመድከም፣ ኢትዮጵያን ከገጠሟት ችግሮች በማላቀቅ ታላቅ አገር የማድረግ ምኞትን ማሳካት አያቅትም፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያዊያን በቅን ልቦና ተነሳስተው ልዩነቶቻቸውን በማክበር አብረው መሥራት ከቻሉ፣ በዚህች ታሪካዊት አገር ተዓምር መፍጠር አዳጋች አይሆንም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን በሠለጠነ መንገድ እየተነጋገሩ ልዩነትን በማጥበብ፣ ለአገር ዘለቄታዊ ህልውና የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ልዩነትን እያከበሩና እንደ ወዳጅ እየተያዩ የጋራ አገር መገንባት ካልተቻለ፣ በመጠፋፋት ጎዳና ላይ እየጋለቡ አገርን ቀውስ መክተት በጣም ቀላል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የጥፋት ድርጊት ግን ለዚህ ዘመን አስተሳሰብ አይመጥንም፡፡ በዚህ መንገድ ሕዝብን ችግር ውስጥ መክተትም ከዚህ ትውልድ አይጠበቅም፡፡ የሥጋት ኑሮ ይብቃ፡፡

የፖለቲካ ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሬ ጉዳይ ከእኔ በላይ የለም ብሎ ሲነሳ፣ የለም ከአንተ በላይ አውቅልሃለሁ ብሎ ዘራፍ ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ ቀደም የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች የወጣቶችን ቁጣ አብርደው ሰላም እንዳሰፈኑት ሁሉ፣ አሁን ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን አለመግባባት መፍታት አማራጭ የለውም፡፡ በተለይ የአገር ሽማግሌዎችና የቤተ እምነቶች መሪዎች ለሰላም መስፈን በመተባበር መሥራት አለባቸው፡፡ ያጠፋውን መገሰፅና የተበደለውን ልቡ ለይቅርታ ክፍት እንዲሆን ማድረግ የአንጋፎች ኃላፊነት ቢሆንም፣ ወጣቶችም በተቻላቸው መጠን ከስሜታዊነት ርቀው በምክንያታዊነት ለሰላም መሥራት አለባቸው፡፡ ያልተረጋገጡ ወሬዎችን ጫፍ በመያዝ እርስ በርስ መጋጨትም ሆነ፣ ሌላውን ወገን ማጥቃት ኋላቀርነት ነው፡፡ ዓለም እንደ መንደር እየጠበበች የሰው ልጆች ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተቀራረቡ ባሉበት በዚህ ዘመን፣ ራስ ላይ አጥር መሥራት ወይም ግንብ መገንባት ጤነኝነት አይደለም፡፡ልጣን ለማግኘት ሲሉ ብቻ በሚቅበዘበዙ ራስ ወዳዶች እየተታለሉ አገርና ሕዝብን ማመስ ለፀፀት ይዳርጋል፡፡ ህልቆ መሳፍርት ተስፋዎች በሚታዩባት አገር ውስጥ ግጭት እየቀሰቀሱ፣ ሕዝብን በሥጋት አቅል ማሳጣት ከንቱነት ነው፡፡ ከሕዝብ ጋርም እስከ ወዲያኛው ያጣላል፡፡

ኢትዮጵያ የሰከነ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ገብታ ፍትሕ፣ ነፃነትና እኩልነት እንዲረጋገጡ መሥራት የእያንዳንዱ ዜጋ የውዴታ ግዴታ መሆን አለበት፡፡ ለፍትሕ፣ ለነፃነትና ለእኩልነት እታገላለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ ስብስብ የዴሞክራሲን የጨዋታ ሕግ ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ይኼንን ሕግ ሳያውቁ የመጫወቻ ሜዳው ውስጥ መግባት የሕዝብ ድምፅ ያሳጣል፡፡ በዚህ ዘመን ሕዝብን በጠመንጃ አግቶ የፈለጉትን ማድረግ አይቻልም፡፡ ከዚህ በፊት ሠርቶ ነበር በማለት ለመሞከር መንገታገትም ይዋል ይደር እንጂ በሕዝብ ያስተፋል፡፡ ሕዝብ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ የአገሩን ሰላም ነው የሚፈልገው፡፡ ኢትዮጵያን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ለመከላከል በርካታ ትውልዶች በደማቸው መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ አገርን በራሳቸው ፍላጎት ብቻ እንደፈለጉ ለማድረግ የሚሹ ምኞታቸው ሳይሳካ ሲቀር አተራምሰው መበታተን የሚፈልጉ ኃይሎች የማይሳካላቸው፣ ሕዝብ ሐሳባቸውን ስለማይፈልገው ብቻ ሳይሆን ስለሚፀየፈው ጭምር ነው፡፡ ይኼንን የተከበረና ጨዋ ሕዝብ ፍላጎቱን በሚገባ ተረድቶ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ፉክክር መዘጋጀት ሲገባ፣ አጓጉል ድርጊቶች ውስጥ መዘፈቅ አደገኛ ነው፡፡ ሕዝብ በነፃነት እንጂ በሥጋት መኖር ሰልችቶታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ችግሮችን ለይቶ መፍትሔ ለማግኘት የሚያስፈልገው ቅን ልቦና ነው፡፡ ቅን ልቦና ሲባል በማንም መነዳት ሳይሆን፣ ብልኃትንና አስተዋይነትን በመጎናፀፍ የመርህ ሰው መሆን ማለት ነው፡፡

ሴረኞች እናገኘዋለን ብለው ከሚያስቡት ጥቅም በታች አገርን ሲያወርዱ፣ ተላሎች ደግሞ በየዋህነት ዓላማዎቻቸውን ሲያሳኩላቸው እየታየ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን ደካማነትና ቅን ልቦናን በፍፁም ማወዳደር አይገባም፡፡ ነገር ግን አቅሙና ዝግጅቱ ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስላሉ፣ እነዚህ ወገኖች ደግሞ ልዩነትን አጣጥሞ ማስኬድ ስለሚችሉበት፣ እዚህ መሀል ልቦናን ቅን አድርጎ መነጋገር ሲቻል ሥጋት እየመነመነ ተስፋ ያብባል፡፡ ሴረኞችና መሰሪዎች እንደ እባብ እየተሹለከለኩ የአገር ተስፋን ማጨናገፍ አይችሉም፡፡ በተለይ ወጣቶች አረጋውያንን፣ እንዲሁም ሕፃናትንና አቅመ ደካሞችን የበለጠ ተጠቂ የሚያደርጉ ጥቃቶች ውስጥ ከመሳተፍ በመቆጠብ፣ ለአገራቸው ሰላምና ህልውና ዘብ መቆም ግዴታቸው መሆኑን ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው፡፡ ለአገር ደንታ የሌላቸው የሚሸርቡት ሴራ ሰለባ ላለመሆንም ንቁ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ያላት አገር ስለሆነች በሥጋት ተከቦ መኖር ማብቃት አለበት፡፡ በዚህ ዘመን ምራቃቸውን የዋጡ ሰዎች የወጣቶች መካሪ፣ የአገር ሽማግሌ፣ የትውልድ አርዓያና የተጣመመውን የሚያቀና መሆን ሲገባቸው፣ እንደ ሠፈር ጎረምሳ የብጥብጥና የሁከት ምንጭ ሲሆኑ ያሳዝናል፡፡ በፖለቲካው መስክ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ፖለቲከኞችና የሚመሯቸው ድርጅቶች አድረው ቃሪያ ሲሆኑ ያሳፍራል፡፡ ለዓመታት በመሣሪያ ያልተሳካላቸውንና በሰላማዊ መንገድ ያገኙትን መልካም አጋጣሚ የሚያበላሹም ያሳቅቃሉ፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ አመለካከቶችና አጀንዳዎች ያሉዋቸው የፖለቲካ ኃይሎች በነፃነት የሚፎካከሩበትን ምኅዳር ለማመቻቸት በጋራ እንረባረብ ሲባል፣ በተሳሳተ መንገድ ለመንጎድ የሚሞክሩ ወገኖች ቆም ብለው ቢያስቡ ይበጃል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች በሕዝብ ስም እየተንቀሳቀሱ ለሕዝብና ለአገር የማይበጅ ድርጊት ሲፈጽሙ አይሆንም ብሎ የማስገደድ ኃይል ያለው ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ እንደ ልጆች ጨዋታ ተጀምሮ ‹ጨዋታው ፈረሰ…› ተብሎ የሚያልቅ ስላልሆነ፣ ሕዝብ በስሙ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞችንም ሆነ ድርጅቶችን መገሰፅ አለበት፡፡ በአገር ቀልድ የለምና፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኢትዮጵያውያን ከስሜታዊነት ይልቅ፣ ለምክንያታዊነት ትኩረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደ ዋዛ ያመለጠ መልካም አጋጣሚ ተመልሶ የመገኘቱ ዕድል እጅግ በጣም የመነመነ በመሆኑ፣ የአገር የጋራ ጉዳይን በምክንያታዊነት ላይ በተመሠረተ ኃላፊነት መወጣት ይገባል፡፡ ፖለቲከኞች ከሥልጣን በላይ ሕዝብና አገርን ካላስቀደሙ፣ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች አገርን ከቡድን ፍላጎት በታች ካሳነሱ ራሳቸውን መመርመር አለባቸው፡፡ ሥልጣን የሚገኘው ከጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን ከዴሞክራሲያዊ ምርጫ መሆኑን የሚገነዘብ ማንኛውም ጤነኛ ሰው፣ በሕዝብና በአገር ላይ የሚቆምሩ ቁማርተኞችን በይሉኝታ ማለፍ የለበትም፡፡ ተስፋ እየመከነ ሥጋት መንሰራፋት የለበትም፡፡

ሕዝብን ወደ ጎን ገፍትረው የሚወዳት አገሩን እንደ ብድር ማስያዣ ቁስ የሚደራደሩባት ፖለቲከኞችም ሆነ አክቲቪስት ተብዬዎች፣ የተለመደውን የፖለቲካ ቁማር ትተው የተሻለ ሐሳብ ቢያመነጩ ይከበራሉ፡፡ አገር በማንም ፈቃድ ተሠርታ የምትፈርስ የእጅ ሥራ አይደለችም፡፡ በበርካታ ውጣ ውረዶችና መስዋዕትነት የተገነባች መሆኗን መዘንጋት አይገባም፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ማበጀት የሚገባቸው ልሂቃን ተብዬዎችም፣ በሕዝብ ውስጥ ውዥንብር እየፈጠሩ ቀውስ ባያባብሱ ይመረጣል፡፡ በተለይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በየዕለቱ በሚዋዥቅ ሐሳባቸውና ቅስቀሳቸው መንታ ሰብዕና የተላበሱ አክቲቪስት ተብዬዎች በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ ለጋራ አገር የሚጠቅም ሐሳብ አፍላቂዎች መሆን ሲገባቸው፣ በተከመሩ ችግሮች ላይ ተጨማሪ እየፈበረኩ ሕዝብን ውዥንብር ውስጥ እየከተቱ ነው፡፡ በሕዝብ ተቀባይነት ማግኘት የሚቻለው በዚህ መንገድ አይደለም፡፡ ለጊዜው ተሳክቶ ከሆነም አያዛልቅም፡፡ የሚያዛልቀው ይኼንን ጨዋና አገሩን የሚወድ አስተዋይ ሕዝብ ሰላምና ዴሞክራሲ ማጎናፀፍ ነው፡፡ ሕዝብ ሁሉንም ነገር በቅርብ ርቀት ስለሚያውቅ መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ ይህ አገሩን የሚወድ የተከበረ ሕዝብ በአገሩ ህልውና ከማንም ጋር አይደራደርም፡፡ ስለዚህ አገርን ውጥረት ውስጥ መክተት አያዋጣም፡፡ የተገኘውን መልካም ዕድል ማበላሸት አይገባም፡፡ ይልቁንም ይህንን መልካም ዕድል የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሚፈልገው ዓላማ ማዋል ያስከብራል፡፡ በተስፋ ፋንታ በሥጋት መኖር እየከበደ ነውና!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...