Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የምግብ ዘይት ችግርን ያቃልላል የሚል ተስፋ የተሰነቀበት ፋብሪካ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ያለውን የምግብ ዘይት እጥረትና የዋጋ ግሽበት ያረጋጋል የተባለው የዘይት ፋብሪካ ዕውን ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያን 60 በመቶ የምግብ ዘይት ፍላጎት ይሸፍናል የተባለው የምግብ ዘይት ፋብሪካ የተገነባውም በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ነው፡፡

በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ቡሬ ከተማ የተገነባውና የተለያዩ ፋብሪካዎችን የያዘው ፊቤላ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ተመርቋል፡፡

ቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክና የፌቤላ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስን የመረቁት ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ በርካታ ባለሃብቶች ቢኖሩም፣ ሁሉም ወደ ባለፀግነት ደረጃ ላይ አለመድረሳቸውንና ባለሃብት ገንዘብ ያለው ባለፀጋ ደግሞ ልብም ያለው ሰርቶ የሚያሰራ፤ አትርፎ የሚያካፍል፤ ለወጣቶች ተስፋና ስራ የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ፖለቲከኞች አገልጋይ፣ ባለሃብቶችም ባለፀጋ ከሆናችሁ ኢትዮጵያን ማሻገር እንችላለን›› ብለዋል፡፡

ፍራፍሬ ውጭ ተልኮ ጭማቂ መምጣት እንደሌለበት፣ ሰሊጥና ኑግ ተልኮ ዘይት ሲገባ መቆየቱን በማስታወስም፣ ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር ይህን ማስተካከልና ግብርናን እሴት ጨምሮ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

የምግብ ዘይት ችግርን ያቃልላል የሚል ተስፋ የተሰነቀበት ፋብሪካ

 

30 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው ኮምፕሌክሱ፣ 4.5 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ከምግብ ዘይት በተጨማሪም የሰሊጥ ጥሬ ምርትን ወደ ውጭ መላክን አስቀርቶ ዕሴት በመጨመርና በመላኩ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ያስገኛል ተብሏል፡፡

የዘይት ፋብሪካው የኢትዮጵያን ፍላጎት 60 በመቶ ይሸፍናል የተባለ ሲሆን፣ ዕለታዊ የማምረት አቅሙም 1‚500 ቶን ዘይት ነው፡፡

ፌቤላ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ በውስጡ ሰባት ፋብሪካዎች አሉት፡፡ ከነዚህም ፋብሪካዎች ውስጥ ቀድሞ ሰሊጥን አበጥሮ ብቻ ሲልክ የነበረው ይገኝበታል፡፡ ይህ አሁን ላይ ተፈትጎና ተቆልቶ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ከሚያስችል አቅም ላይ ደርሷል፡፡ ሁለተኛው ፋብሪካ ምርትን አጣርቶ መዳመጥ የሚያስችል ነው፡፡ ይህም ቀደም ብሎ ከማሌዥያ ታሽጎ ሲመጣ የነበረውን የምግብ ዘይት ከታሸገበት ጊዜ አንስቶ፣ በኮንቴነር ተጭኖ ወደ አገር ውስጥ እስኪገባ ድረስ አምስት ወራት ይፈጅ የነበረውን ሒደት ማስቀረት የሚያስችል ነው፡፡

ፋብሪካው በቀን ከ600 እስከ 700 ቶን ድረስ የማጣራትና ከ800 እስከ 1‚000 ቶን የመዳጥ አቅም አለው ተብሏል፡፡ ማጣራት ከሚችላቸው የቅባት እህል ዓይነቶችም ተልባና ሱፍ ይገኙበታል፡፡ የአትክልት ዘይትን በመዳመጥ ለገበያ ማቅረብ የሚያስችልም ነው፡፡

ዘይቱን እዛው መሙላትና ማሸግ የሚያስችል ቴክኖሎጂም በውስጡ አካቷል፡፡ የምርት ሒደቱ ከተጠናቀቀ በኋላም ለማሸግ የሚያስችል የካርቶን ፋብሪካ አለው፡፡

ኮምፕሌክሱ የምግብ ዘይት ከማምረት በተጨማሪ በቀን 200 ቶን የሚደርስ ሰሊጥን በተለያየ ደረጃ አጣርቶ እና እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡ በቀን 96 ቶን ያህል ማምረት የሚችል የሳሙና ፋብሪካ እና የአትክልት ቅቤና ማርጋሪን ፋብሪካዎች አሉት፡፡

በተለያየ መጠን በቀን ከ10 ሺህ በላይ የጀሪካን እና ፕላስቲክ ጠርሙሶች ማምረቻ ፋብሪካ እና የካርቶን ፋብሪካዎችን በአንድ ያጠቃለለ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስም ነው

የወቅቱን ቴክኖሎጂ ደረጃ እንዳሟላ የተነገረለት ፋብሪካው፣ ሁሉንም ሒደት በተቀላጠፈ መልኩ መከወን እንደሚያችል የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ክንዴ አስረድተዋል፡፡

ደረጃ መዳቢና ተስማሚነት ምዘና ጥራቱን መርምረው ፈቃድ መስጠታቸውን ተከትሎ መንግሥት በየክልሉ እንዲሠራጭ ባስቀመጠው ኮታ መሠረት፣ ለገበያ እንደሚቀርብ አቶ በላይነህ አስታውቀዋል፡፡

በወቅታዊ የምግብ ዘይት የዋጋ ተመን መሠረት በማሌዥያ አንድ ሌትር ዘይት አንድ ዶላር ከአምስት ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተቀመጠው ተመን መሠረት፣ ፊቤላ የተጣራ የምግብ ዘይት በሌትር ከ40 እስከ 42 ብር እንደሚሸጥ ተገልጿል፡፡

በውጭ አገር ታሽጎ የሚመጣው የምግብ ዘይት የትራንስፖርትና ተያያዥ ወጪዎች ያሉበት በመሆኑ በአገር ውስጥ መመረት መቻሉ፣ ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲጠቀም ያስችለዋል ብለዋል፡፡

የተጣራ የምግብ ዘይቱን ለማምረት ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ የቅባት እህል ግብዓት ስለሌለ የድፍድፍ ግብዓት ከውጭ የሚመጣ ይሆናል፡፡ አገሪቷ ከአንገር ጉቴ እስከ ሁመራ ድረስ ለቅባት እህል አመቺ መሬት ቢኖራትም፣ በዓመት የሚመረተው ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነው፡፡

አዲስ የተገነባው የፊቤላ የተጣራ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ደግሞ በዓመት 20 ሚሊዮን ኩንታል የቅባት እህል እንደሚፈልግ ቦርድ ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ በላይነህ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ግብዓት በቂ እስኪሆን ድረስ  ድፍድፉ ከውጭ የሚመጣ ይሆናል፡፡ ፊቤላ አሁን ለገበያ የቀረበውን የተጣራ የምግብ ዘይት ለማምረት ድፍድፉን በቶን 752 ዶላር ያወጣበት ሲሆን፣ በንፅፅር የታሸገውን ለመግዛት በቶን ከ1‚000 እስከ 1‚500 ዶላር ድረስ ሲያስወጣ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ይህም የታሸገውን አምጥቶ ከመሸጥ ይልቅ ድፍድፉን አስመጥቶ በማምረት በዓመት መቶ ሚሊዮን ዶላር ማዳን ያስችላል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የምግብ ዘይት ፍላጎት ሰፊ በመሆኑ፣ ለጊዜው የሽያጭ ሽፋኑን በአገር ውስጥ እንደሚያደርግና የሰሊጥ ዘይት ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊና  ለኢትዮጵያ የሚያመጣው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ በመሆኑ ለውጭ ገበያ ብቻ እንደሚቀርብ አቶ በላይነህ አክለዋል፡፡

ሰሊጥን ዳምጦና አጣርቶ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ የነደፈው ድርጅቱ፣ ሰሊጥ ሲቆላና ሲፈጭ 50 በመቶ ጭማሪ እንደሚኖረውና ይህም በዋጋ ሲተመን በቶን እስከ 2‚000 ዶላር እንደሚያስገኝ፣ በአንፃሩ ታሽጎ ለገበያ ሲቀርብ በቶን እስከ 3‚000 ዶላር ድረስ ዋጋ ሊኖረው እንደሚችል ተገልጷል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከ50 እስከ 75 ቶን ሰሊጥ ብቻ የማጣራት አቅም የነበራት ሲሆን፣ አሁን 1‚500 ቶን በቀን የማጣራት አቅም ያለው ፋብሪካ መኖሩ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ለማስገኘት ያስችላል፡፡

ፋብሪካው አሥር ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈልግ ነው፡፡ አሁን እየተጠቀመ ያለው አራት ሜጋ ዋት ኃይል ብቻ ነው፡፡ ይህን አስመልክቶ የኃይል መቆራረጥና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ቀዳሚ ችግር እንደሆነ የገለጹት አቶ በላይነህ፣ ችግሮቹን ለመፍታት ከመንግሥት ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በትራንስፖርት፣ በግንባታ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በአምራች ዘርፍ፣ በእርሻ፣ በመኪና መገጣጠም፣ በወጪ እና ገቢ ንግድ ላይ የተሰማራና ከ3‚000 በላይ ሠራተኞች ያሉት ተቋም ነው፡፡

የምግብና የዘይት ኢንዱስትሪውን የማስፋፋት ዕቅድ መኖሩን ያስረዱት ቦርድ ሰብሳቢው በሆቴል፣ በእርሻው ዘርፍ በሰፊው እየሠሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

በሆቴል ዘርፍ በባህር ዳር ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን ሒልተን ሆቴል ጨምሮ ኢትዮጵያ ሆቴል ባለበት ሁኔታ ዕድሳት፣ በአዳማ ከተማ የሚገኘው አዳማ ራስ ሆቴል ማስፋፊያ ይደርግላቸዋል ተብሏል፡፡

ከዚህም ባሻገር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል፣ ጃዊ እንዲሁም በደቡብ ክልል ግብርናውን የማስፋፋት ሥራ ላይ እንደሚገኙ አቶ በላይነህ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች