Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በባዮ ቴክኖሎጂ እመርታ

በጥቂት ቦታ ምርታማነትን ለማምጣት፣ የሰብል ምርት እንዲጨምር ለማድረግ፣ ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚገኙ ንጥረ ነገሮችን ለማግኘት ከሚረዱት ዓይነተኛ ዘርፎች ተጠቃሹ ባዮ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችን በመረጃ፣ በዕውቀትና በመሰል ሥልጠናዎች ለማብቃትና አገራዊ አስተዋጽኦን ለማበርከት የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ሶሳይቲ (ማኅበር) ከተቋቋመ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በቅርብ ጊዜ የተመሠረተ ቢሆንም ዘርፉን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ ስጦታው ይገልጻሉ፡፡ ማኅበሩ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የባዮ ቴክኖሎጂ ጥቅም ምንድነው?   

አቶ ዮሐንስ፡- በዓለም በየጊዜው የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ ድህነት፣ ሥራ አጥነትና የአየር ብክለት ሌሎችም ችግሮች አሉ፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር ድምር ያለው ተፈጥሯዊ ሀብት በቂ ላይሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ባዮ ቴክኖሎጂ ደግሞ በጥቂት ቦታ ምርታማነት እንዲኖራቸው በቴክኖሎጂ በማገዝ እንዲብቃቃ ያደርጋል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ በምግብ ራስን ለመቻል እጅግ ፈተና ከሚሆኑባቸው አገሮች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ እነዚህና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት በመጠቀም በትንሽ ቦታ ብዙ ማልማት እንዲያስችል ባዮ ቴክሎጂ ዕገዛ ያደርጋል፡፡ በዚህም በትንሽ ቦታ የዘራናቸው የእህል ዓይነቶች በምንም ተባይ እንዳይበሉ የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል የባዮ ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ የሚኖረው ጥቅም ብዙ ነው፡፡ የዘረመል ምሕንድስናና የባዮ ቴክኖሎጂ ትምህርት ለኢትዮጵያ በስፋት በመስጠት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ምርምርና ልማት ላይ በማሳተፍ የኅብረተሱን የሳይንስ ዕውቀትና ትክክለኛ ግንዛቤ ለማጎልበት ላይ እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባዮ ቴክኖሎጂ ሶሳይቲ ማኅበር መመሥረት ለምን አስፈለገ?  

አቶ ዮሐንስ፡- ማኅበሩ የተመሠረተበት ዋና ዓላማ በዋናነት በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን በመረጃ፣ በዕውቀትና መሰል ሥልጠናዎች በምክክር ለማብቃት ነው፡፡ በሌላ በኩል ባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ወደ አንድ ዕርምጃ ለማሳደግ ማኅበሩ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው፡፡ በመንግሥት በሚያወጣቸው ባዮ ቴክኖሎጂና ተያያዥ መመርያና ደንቦች ፖሊሲን ጭምር ከሙያ አንፃር ግብዓት ለመስጠት ማኅበሩ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ መጠቀም ያለበትን ያህል እየተጠቀመች ባለመሆኑ ማኅበሩ ደግሞ ከባለሙያዎች፣ ከኢንስቲትዩት እንዲሁም ተዛማጅ ከሆኑ ሴክተሮች ጋር በመሆን ተጠቃሚነትን ለማጉላት የሚሠራ ማኅበር ነው፡፡ በዘርፉ የተለያዩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ፣ ተመራማሪዎችን ለማፍራትና ለማገዝ፣ በተመሳሳይ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የውጭ ድርጅቶች የልምድ ልውውጥ ማድረግና ሌሎችንም ጥቅም የሚሰጥ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ግብርናውን ከማዘመን አንፃር ምን ይሠራል? ምንስ ታቅዷል?

አቶ ዮሐንስ፡- ግብርናን ከማዘመን አኳያ ሰፊ ሥራ አስበናል፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የግብርና ሒደት ረዥም ጊዜ በመሆኑ ባዮ ቴክኖሎጂ ደግሞ ይህንን ሒደት በማዘመን ረገድ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አስተዋጽኦ የሚያደርገው ቴክኖሎጂው ነው፡፡ በቅርበት የሚሠሩ የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሚያስፈልገውን ሙያዊ ዕገዛ ለማድረግ ማኅበሩ ይሠራል፡፡ አሁንም በዘርፉ የሚደረጉ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የቲሹ ካልቸርና ሌሎችም ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ዘመናዊና አዳዲስ የባዮ ቴክኖሎጂ ዕውቀቶች እየመጡ በመሆኑ እነዚህ ላይ በትኩረት የሚሠራ ማኅበር ነው፡፡ ዘረመል ምሕንድስና ዘረመል ሳይቀየሩ እዚያው የማስተካከልና የማዘመን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የጥጥ ዝርዎች ማዘመንና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምሩና ድርቅን እንዲቋቁሙ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር እየተሠራ ይገኛል፡፡ ተመሳሳይ የሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች በጋራ እንዲሠሩ የሚያመቻችና በተለያዩ ተቋማት የሚሠሩ ምርምሮች ወጥነት ባለው መንገድ እንዲካሄዱ ማኅበሩ ዕገዛ ያደርጋል፡፡   

ሪፖርተር፡- በዘርፉ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር ምን ይሠራል? በተለይ ከውጭ አገሮች በልምድ ለመቅሰም ስምምነቶች አላችሁ?

አቶ ዮሐንስ፡- ዘርፉ እንዲያድግ በዩኒቨርሲቲዎች በርካታ የትምህርት ዓይነቶች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ እነሱንም በማቀናጀት ዕውቀትንና ልምድን በመለዋወጥና በጋራ በመሥራት አቅም ያሰጣሉ፡፡ ማኅበሩ በቀጣይ የሌሎች አገሮች ተምክሮዎች ከአገር ጋር በማጣጣም የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ይሠራል፡፡ በተለይም የግብርና ዘርፉን በይበልጥ ለማሳደግ የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚደረገው ከፍተኛ ቦታውን ይይዛል፡፡ በግብርና ላይ የሚሠሩ በርካታ የምርምር ተቋሞች አሉ፡፡ ነገር ግን ባዮ ቴክኖሎጂ አዲስ ቴክኖሎጂ ይዞ ሲመጣ የተሻለ ነገር እንዲኖር ስለሚያግዝ ነው፡፡ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ባዮ ቴክኖሎጂ ዕገዛ ያደርጋል፡፡ ባዮ ቴክኖሎጂ ወደ ግብርና የገባበት ዋና ምክንያት በአገር ውስጥ ያለው ምርትና ምርታማነት ዝቅተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ባዮ ቴክኖሎጂ አስፈላጊ በመሆኑ እየተጠቀምንበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበረሰቡ ስለባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለው ግንዛቤ ምን ይመስላል? ግንዛቤውን ከፍ ለማድረግስ ምን ይሠራል?

አቶ ዮሐንስ፡- ማኅበረሰቡ በዚህ ዘርፍ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ አንዱ የማኅበሩ ዓላማ ነው፡፡ ማኅበረሰባችን ቀደምት አባቶቹ ድረስ ሲጠቀሙበት የነበረው ልማዳዊ የሰብል አጠባበቅ ዘዴዎች አሉት፡፡ በሌላ በኩል የምግብና የመጠጥ አሠራር ዘዴዎች ይጠቀሙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ እርሾና መጠጥ ላይ የምንጠቀማቸው ነገሮች በጠቅላላ የአባቶቻችን የማዘመን ሒደት ነው፡፡ በዚህም ኑሯቸውን በቀላሉ እንዲኖሩ ያግዛቸው ነበር፡፡ በዚህ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰባችን ዘንድ ያለውን ዕውቀት ለማሳደግና ለማዘመን ማኅበሩ የባዮ ቴክኖሎጂ ዕውቀትን በማስገንዘብ ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ምን ያህል አባላት አላችሁ? አባላቱስ ምን ዓይነት ሥልጠናዎችን ያገኛሉ?

አቶ ዮሐንስ፡- ማኅበሩ ከ200 በላይ አባላት አሉት፡፡ ከውጭ አገሮች ጋር ዘርፉን ለማሳደግ በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል፡፡ ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የባዮ ቴክኖሎጂ ሶሳይቲ ‹‹ለአገራዊ ልማት ግቦች ስኬት›› በሚል መሪ ቃል የመጀመርያውን ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዷል፡፡ ይህም ማኅበሩ በቀጣይ ለኢትዮጵያ ማድረግ ስላለበትና ሌሎች ጉዳዮች የመከረበት መድረክ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን

ቢሻን ጋሪ ፒውሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ውኃ የማከም ቴክኖሎጂ ሥራ የገባው በየጊዜው በኢትዮጵያ የተከሰቱ ውኃ ወለድ በሽታዎች መደጋገምን ዓይቶና ጥናት አድርጎ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. ቢሻን...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...

ሕይወትን ለመቀየር ያለሙ የቁጠባና ብድር ማኅበራት

ወ/ሮ ቅድስት ሽመልስ በግሎባል ስተዲስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ሠርተዋል፡፡ በኮርፖሬት ፋይናንስ ካናዳ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ...