ከዕለት ወደ ዕለት እየተስፋፋ በመጣው የአህያ ቆዳ ፍላጎት ምክንያት፣ ከኢትዮጵያ በርካታ አህዮች በሕገወጥ መንገድ እንደሚወጡና የአገሪቱ አህዮች ቁጥር አደጋ ላይ መውደቁ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ብሩክ ኢትዮጵያ የተባለው የጋማ ከብቶችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ ሕገወጥ የአህዮች ግብይትን ስለመከላከል የሚገልጽ የውይይት መድረክ ሐሙስ ጥር 27 ቀን 2013 በአዳማ ከተማ ባከናወነበት ወቅት ነው፡፡
በውይይቱ ላይ የመነሻ ጥናት ያቀረቡት የብሩክ ኢትዮጵያ የፕሮግራሞች ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቃሲም እንዳሉት፣ ‹‹ኤጃዎ›› የተባለውን ባህላዊ የቻይና መድኃኒት ለማምረት ቁጥራቸው በርካታ አህዮች ከኢትዮጵያ በኬንያ ድንበር በኩል በሕገወጥ መንገድ እየወጡ እንደሆነ ገልጸው፣ በቁማቸው መውጣት ያልቻሉ አህዮች ድንበሮች ላይ እየታረዱ ቆዳቸው ተገፎ ከአገር እየወጣ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ተከፍተው ወዲያው የታገዱ ሁለት የአህያ ቄራዎች በቢሾፍቱና በአሰላ እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ዮሐንስ፣ ሆኖም ሌሎች የቻይና ባለሀብቶች በኬንያ የኢትዮጵያ አዋሳኝ ድንበር ላይ ያቋቋሟቸው ቄራዎች የኢትዮጵያ አህዮች መዳረሻ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
እርጅናን የሚከላከል የፊት ቅባትና ከፆታዊ ግንኙነት ጋር የተገናኙ ችግሮችን ያክማል ተብሎ በዓለም ላይ ፍላጎቱ ከፍተኛ የሆነውን ‹‹ኤጃዎ›› ለማምረት፣ በየዓመቱ እስከ አምስት ሚሊዮን የሚደርስ የአህያ ቆዳ ፍላጎት አለ የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ ይህ ፍላጎት ከጠኝ ሚሊዮን በላይ አህዮች ያሏትንና በዓለም ቀዳሚ የሆነችውን ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ሥጋት ላይ ጥሏታል ብለዋል፡፡
ለብሩክ ኢትዮጵያ የንቅናቄዎች ኃላፊ የሆኑት አቶ ዮናስ ታፈሰ እንዳስረዱት፣ ኬንያ በሁለት ዓመታት ብቻ 15 በመቶ የሚሆኑ አህዮቿን በዚህ ምክንያት አጥታለች፡፡ ችግሩ በኢትዮጵያ በስፋት እየተንሰራፋ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ዮናስ በጅግጅጋ፣ በነገሌ፣ በሻኪሶ፣ በያቤሎና በጂንካ በየቀኑ ከ1,000 እስከ 3,000 የሚጠጉ አህዮች በሕገወጥ መንገድ እየታረዱ ከአገር እየወጡ ናቸው ብለዋል፡፡ ሕገወጥ ተግባሩ አፋጣኝ የሆነ ምላሽ ካላገኘ በአጭር ዓመታት ውስጥ ለኢትዮጵያ አርሶ አደር ትልቅ ዋጋና አገልግሎት ያለው የአህያ ሀብት፣ ሊመለስ ከማይችልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ሲሉ የተፈጠረውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡
የብሩክ ኢትዮጵያ የእንስሳት ደኅንነት አስተባባሪ አቶ ፀጋዬ ነጋሽ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አህያ በተፈጥሮ የእርባታ እንስሳት ከሚባሉት ወገን እንዳልሆነ ገልጸው፣ ራሳቸውን የመተካት ፍጥነታቸው ደካማ ነው ይላሉ፡፡ አንዴ ከወለዱ በኋላ በድጋሚ ለመተካት ከሦስት ዓመታት በላይ ሊፈጅ እንደሚችል የሚገልጹት አስተባባሪው፣ ከአገር እየወጣ ካለው ሕገወጥ አህያ ንግድ አንፃር ሀብቱ የሚታጣበት የጊዜ ፍጥነት አጭር ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአዳማ ከተማ በተከናወነው ውይይት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ ከእንስሳት ሐኪሞች ማኅበር፣ እንዲሁም ከመገናኛ ብዙኃን የተወጣጡ ባለሙያዎች ችግሩን ለመከላከል ከግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እስከ የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ ሊዘጋጅ እንደሚገባ በመድረኩ አስታውቀዋል፡፡