Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየአፍረን ቀሎ ፈርጥ

የአፍረን ቀሎ ፈርጥ

ቀን:

ሙዚቃን በኦሮምኛ፣ ሶማሊኛ፣ አፋርኛ፣ ሐረሪ፣ አማርኛና ሱዳንኛ አቀላጥፎ መጫወት መለያው ነው፡፡ የሕፃናት ልብ የመስረቅ አቅም ባለው ሰዋዊ የሙዚቃ ቅላጼው በሁሉም ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ ዓሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም. የተመሠረተውን የመጀመርያው የኦሮምኛ ቋንቋ የኪነት ቡድን ‹‹አፍረን ቀሎ››ን በመቀላቀል ነበር የሙዚቃ ሥራውን የጀመረው፡፡

ዓሊ በኪነ ጥበቡ ውስጥ በቆየባቸው ከ50 ዓመት በላይ የሙዚቃ ጉዞ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ሊታወስ የሚችልበትን በርካታ የሙዚቃ ሥራዎቹን ሠርቷል፡፡

የትውልድ ከተማው የሆነችው ድሬዳዋ ከአፉ የማትለየው ዓሊ፣  ድሬዳዋን በሙዚቃዎቹ ወስጥ ሲጠቅሳት ኖሯል፡፡

አፈንዲ ሙቲቂ ‹‹ኡመት ፈናን ኡመት ቀሺቲ ድሬዳዋ›› በሚለው ድርሳኑ ሲያብራራ፣ ዓሊ የድሬ ነገር እንደማይሆንለትና በየሙዚቃዎቹ ሁሉ በቦክስ ጊታሩ ደህና አድርጎ ያዜምላታል ሲል ይገልጻል፡፡ ይኼም ከበርካታ የዓሊ ሙዚቃዎች ውስጥ አንዱ የሆነውና ሌሎችም ሙዚቀኞች ዳግም የሠሩት ስለ ድሬዳዋ የተቀኘው ሙዚቃ መጥቀስ ይቻላል፡፡

“Alattin Dirree Dhawaa foon malee lafee hinnyaatina jetti

Magaalleen Diree Dhawa namalee hindubbisina jetti” የሚለው የኦሮምኛ ቋንቋ ሙዚቃው ጠንከር ያለ ቅኔ የሚያስተላልፍበት አንዱ ነው፡፡

ይኼም ሲተረጎም ‹‹የድሬዳዋ ጭልፊት ሥጋ እንጂ አጥንት አትብሉ፣ የድሬዳዋ ጉብልም ከእኔ በቀር ሌላዋን አታናግሩ ትላለች፤›› የሚል ነው፡፡  

 እንደ መጽሐፉ ማብራሪያ ከሆነ በግጥም ውስጥ ዓሊ ቢራ ድሬዳዋን በጥበብ ሥራዎቹ እንደዘከረ ያስረዳል፡፡ ዓሊ በዚህ ባህላዊ ግጥም ሁለት ተቃራኒ ባህሪያትን እንደ አንድ አምሳያ አድርጎ ለመግለጽ መፈለጉን  ይጠቁማል፡፡ የድሬዳዋ ጭልፊትና የድሬዳዋ ጉብል፡፡

ጭልፊቷን አጥንት አትብሉ ያለችው ለውንብድና ተግባሯ እንደሚያመቻት በማሰብ እንደሆነና ሰዎች ሥጋውን ትተው ወደ አጥንቱ ጎራ ካሉ እርሷ ጦሟን ማደሯ በማሰቧ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ስለዚህ ያ እንዳይሆን ለድሬ ነዋሪዎች ‹‹የምን አጥንት ማሳደድ ነው? ሥጋውን ጠንከር አድርጋችሁ ያዙ እንጂ›› እያለች ‹‹የብልጠት›› ምክር ለመስጠት አቅዳ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

የድሬ ቆንጆ ‹‹ከእኔ በቀር አታናግሩ›› የማለቷ ምስጢር ግን ከጭልፊቷ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› ብሂል ከሚለው እንደሚለይ ይጠቁማል፡፡ በዓሊ አንደበት ሊነገረን የተፈለገውም ይላል መጽሐፉ ‹‹የድሬዳዋ ጉብል ከሁሉም ትበልጣለች›› የሚል መልዕክት ነው እንጂ ‹‹የድሬ ጉብል ራስ ወዳድ ናት›› ለማለት አይደለም ይላል፡፡

ዓሊ ቢራ በ1940ዎቹ መጀመርያ ላይ ‹‹ገንደ ቆሬ›› በተሰኘው የድሬዳዋ ሰፈር ነው የተወለደው፡፡ ሙዚቃን በዚያች የትውልድ መንደሩ ውስጥ ሲጫወት ከቆየ በኋላ ወደ አዲስ አበባው ማዕከላዊ ዕዝ ኦርኬስትራ (የድሮው ‹‹ክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ››) መሻገሩን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በማዕከላዊ ዕዝ እያለም የመጀመርያ አልበሙን በሸክላ አስቀርጿል፡፡ ከማዕከላዊ ዕዝ ከለቀቀ በኋላ በ1970ዎቹ ዝነኛ በነበሩት ‹‹አይቤክስ›› እና ‹‹ኢትዮ-ስታር›› ባንዶች ሲሠራ ከርሞ በ1977 ዓ.ም. ስዊድናዊት ባለቤቱ ባደረገችው ጉትጎታ ሀገር ጥሎ ወጣ፡፡ በ1980ዎቹ መጀመርያ ላይ ወደ አሜሪካ ከተሻገረ በኋላ በሀገረ ካናዳ ኑሮውን ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከዓመታት የስደት ሕይወት በኋላ ወደ ትውልድ አገሩ ኢትዮጵያ መጥቶ ኑሮን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ዓሊ ቢራ በሙዚቃው አንቱታን ለመጎናፀፍ የበቃው ገና በታዳጊነቱ ነው፡፡ ከየትኛውም ሽልማት በበለጠ የሕዝብ ፍቅር ያለው ዓሊ፣ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትን ከማትረፉም በሻገር በቅርቡም በርካታ ዘፋኞች አብረውት ሲሠሩ መመልከት እየተዘወተረ መጥቷል፡፡ በሚሌኒየም አዳራሽ ከመሐሙድ አህመድ ጋር ተጣምረው ካቀረቡት የሰላም መልዕክት ካለው ዝግጅት በኋላ ከወጣቶቹም ጋር በጥምረት ሲሠራ እያተስተዋል ነው፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ከሔለን በርሄ ጋር ‹‹ሲያዴ›› የሚለው ነጠላ ዘፈኑ አድናቆትን ማትረፍ ችሏል፡፡ የሙዚቃውን ቪዲዮም ከ7.9 ሚሊዮን ተመልካች በላይ አጣጥሞታል፡፡ በቅርቡም ከአብርሃም በላይነህ ጋር በጋራ በመሆን ‹‹ዳርም የለው›› የሚለው የሙዚቃ ቪዲዮ የሕፃናት ቀልብ ሳይቀር መግዛት የቻለ ሥራ ሆኗል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለዓሊ ቢራ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የምስጋናና ዕውቅና መርሐ ግብር ማዘጋጀቱን የባህልና ቱሪዝም ቢሮው አስታውቋል፡፡ ቢሮው የምሥጋና መርሐ ግብሩ መዘጋጀት ያስፈለገው ድምፃዊ ዓሊ ቢራ ከስድስት አሠርታት በላይ በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ለኦሮሞ ሕዝብ ጥበብ ማበብ፣ ለባህልና ቋንቋ ዕድገት፣ ለሕዝቦች አብሮነትና መብት መከበር፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላበረከተው አስተዋጽኦ ዕውቅና ለመስጠት መሆኑን አመልክቷል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ በሰጡት መግለጫ፣ ድምፃዊ ዓሊ ቢራ የጥበብ ሥራዎቹን በጊዜያዊ ችግሮች ሳይሸነፍ በፅናትና በብቃት ለትውልድ በማስተላለፍ አርዓያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በምሥጋና መርሐ ግብሩ ላይ በሱራፌል ገልገሎ (ዶ/ር) የተዘጋጀው የድምፃዊው የሕይወት ታሪክና ሥራዎች መጽሐፍ ምረቃ እንደሚከናወንም ታውቋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል መንግሥት ኃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የጥበቡ ማኅበረሰብ፣ ጓደኞቹና አድናቂዎቹ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...