Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትኮሮና የፀናባት ጃፓን የዘንድሮውን ኦሊምፒክ ልትሰርዘው ከጫፍ ደርሳለች

ኮሮና የፀናባት ጃፓን የዘንድሮውን ኦሊምፒክ ልትሰርዘው ከጫፍ ደርሳለች

ቀን:

ጃፓን በኮቪድ-19 ምክንያት የዘንድሮውን ኦሊምፒክ የምትወጣበትን መንገድ እየፈለገች መሆኑ መነገር ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ዓምና ሊከናወን የነበረው 32ተኛው ኦሊምፒያድ ለአሥር ወራት ሊራዘም ቢችልም ከሰሞኑ የጃፓን ከተሞች በሁለተኛው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማዕበል እየተመቱ በመምጣታቸው የኦሊምፒክ ውድድሩ ሊሰረዝ የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል፡፡

ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) እንዲሁም የቶኪዮ ኦሊምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ ‹‹ጃፓን የዘንድሮውን ኦሊምፒክ ልትሰርዘው ነው፤›› የሚለውን ወሬ ውሸት ነው በማለት ቢያስተባብልም አዘጋጇ አገር ግን ውድድሩን እ.ኤ.አ. 2032 ለማድረግ በውስጥ ለውስጥ ውሳኔ ላይ መድረሷ እየተነገረ ነው፡፡

እንደ ዘ ታይምስ ዘገባ ከሆነ የጃፓን መንግሥት የዘንድሮውን ኦሊምፒክ ለመሰረዝ ከአገሪቷ የገዥው ጥምረት ከፍተኛ አባል ጋር እየመከረ እንደሆነና ከተማዋ ጨዋታውን 2032 ማዘጋጀት የምትችልበትን መንገድ ለማመቻቸት እየወጠኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም አሁን ላይ የቀረው ዘንድሮ እንደማይደረግ ለሕዝብ ማሳወቅ መሆኑን ዘ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ አገኘሁት ያለው መረጃ ያመለክታል፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀችው ጃፓን፣ የወረርሽኙ ሁለተኛ ዙር ማዕበል የታማሚዎችን ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱ ገልጻለች፡፡

ይሄም አገሪቷ ሥጋት ውስጥ መግባቷና ከ200 በላይ አገሮች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቀውን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ልትሰርዝ እንደምትችል አሥግቷል፡፡

ጥናቶችና የባለሙያዎችን ግምት ተከትሎ ጨዋታው ሊሰረዝ የሚችልበትን አጋጣሚ የሚጠቁሙ ሚዲያዎችን መረጃ እየተከተለ ማስተባበያ የሚያወጣው የጃፓን ኦሊምፒክ ኮሚቴና ዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተለያዩ ዕቅዶችን በመንደፍ፣ ግብረ ኃይል አዋቅረው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በቅርበት እየሠሩ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡

ሐምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የቶኪዮ ኦሊምፒክ 206 አገሮች በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባህ አስተያየት ከሆነ፣ ከሁሉም ተሳታፊ አገሮች ጋር መነጋገራቸውና በጨዋታው ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ እንዲሁም የጃፓን መንግሥትም ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ጠቅሰዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ቶኪዮ ከሚገኘው ኪዮዶ የተባለ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መሠረት ‹‹ሁለተኛ አማራጭ ወይም ዕቅድ›› ብሎ ነገር እንደሌለና ጨዋታውን ለማከናወን አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ በጃፓን እየተባባሰ የመጣው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ አገሪቷ ለማንኛውም የውጭ ዜጎች ድንበሯን መዝጋቷን አስታውቃለች፡፡

አገሪቷ በየቀኑ ከ1,000 በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 እየተያዙባት ሲሆን፣ ካለፈው ወር ጀምሮ በተከታታይ ቀናት ከ2,400 ሰዎች በላይ መያዛቸው ተገልጿል፡፡

የኦሊምፒክ ጨዋታን ተከትሎ በጃፓን የተለያዩ ጥናቶች የተደረጉ ሲሆን በጥናቱም መሠረት 80 በመቶ የሚሆኑት የአገሪቷ ነዋሪዎች የኦሊምፒክ ጨዋታው ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ ወይም ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ፍላጎት እንዳላቸው ጥናቱ ያመለክታል፡፡

በስልክ በተደረገ የድምፅ አሰጣጥ መሠረት 35.3 በመቶ የሚሆኑት ጨዋታው ይሰረዝ፣ እንዲሁም 44.8 የሚሆኑት ደግሞ ወደ ሌላ ጊዜ ይተላለፍ የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ከአሥር ወራት በፊት የተራዘመው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ዳግም በኮቪድ ሥጋት የተለያዩ አገሮች ‹‹ይሰረዝ›› የሚል አስተያየት እየሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም መሠረዙ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴንና ጃፓንን ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል ይገመታል፡፡

የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎችን መሰረዝ ጃፓንን ከፍተኛ ኪሳራ ሊያስከትልባት እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፣ ለዝግጅቱ ከ25 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማውጣቷ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም አገሪቷ ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት ውስጥ ሊከታት እንደሚችል ይገመታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከሁለት ዓመት በላይ ልምምድ ሲያደርጉ ለቆዩት አትሌቶች ውድድሩን ዳግም መሰረዝ ወይም ለሌላ ጊዜ ማሳወቅ መርዶ እንደማርዳት ያህል ይቆጠራል፡፡

የኦሊምፒክ ጨዋታው እንደሚካሄድ በእርግጠኝነት እየተናገሩ ከሚገኙት አዘጋጆችና ውድድሩ መሰረዙ አይቀርም የሚሉትን ወገኖች እውነትነት የሚያረጋግጥ ውሳኔ በቅርቡ ይደመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...