Thursday, April 18, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥኑ ድርጊቶች እየበዙ ነው!

የዘመኑ ትውልድ በማስተዋል ሁኔታዎችን ከተከታተለ ባለበት 21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ለማመን የሚያዳግቱ አስገራሚ ቴክኖሎጂዎች እየተፈጠሩ መሆናቸውን ይገነዘባል፡፡ የሰው ልጅ ምጡቅ አዕምሮ ውጤት የሆኑ የቴክኖሎጂ ገፀ በረከቶች ሕይወትን ቀለልና ዘና እያደረጉ ነው፡፡ የዘመኑ ዕውቀት በበለፀጉ የሳይንስ ንድፈ ሐሳቦችና የተግባር ልምምዶች የተጠናከረ ሲሆን፣ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሰው ልጅ አዕምሮ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዳብሯል፡፡ አስቸጋሪውን የኑሮ ውጣ ውረድ በማቅለል ላይ ያሉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ የሰው ልጅ ፍላጎትን በመጨመር አስተሳሰቡን በማዘመን ላይ ናቸው፡፡ ይህ ዘመን ለኋላቀርነትና ለስንፍና ሥፍራ ስለማይሰጥ፣ የሰው ልጅ የበለጠ ለማግኘት ከፍተኛ ውድድር ውስጥ ገብቷል፡፡ ይህ ውድድር በጥራትና በፍጥነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑም፣ የጭንቅላት ጨዋታው ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሯል፡፡ 21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ በአረጀ አስተሳሰብና በኋላቀር ልማድ ለመኖር መሞከር ከተፎካካሪነት መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ለብዙ ነገሮች ባዕድ ያደርጋል፡፡ በዚህ ዘመን አንድ ግለሰብ አዕምሮውን በሚገባ ከተጠቀመበት፣ ከራሱ አልፎ ለአገር ብሎም ለዓለም ይተርፋል፡፡ ይህ ዘመን የሚያንቀላፉ ሳይሆኑ ለአፍታ የማያሸልቡ ብርቱዎች ተዓምር የሚሠሩበት ነው፡፡ የምጡቅ አዕምሮ ባለቤቶች የሚከብሩበትና የሚከበሩበት ነው፡፡ ከዚህ ዘመን ጋር መዘመን አለመቻል እንዳለመኖር ይቆጠራል፡፡

በፖለቲካው መስክም ተመሳሳይ ነው፡፡ አገር የሚመሩ፣ በዲፕሎማሲ ውስጥ የተሰማሩ፣ የፖለቲካ ፓርቲ የሚያደራጁም ሆኑ ሌሎች መገንዘብ ያለባቸው ድርጊቶቻቸው በሙሉ ለሕዝብ ጠቃሚ እንዲሆኑ መሥራት እንጂ፣ ዘመኑን የማይመጥን ተግባር አለመፈጸም ነው፡፡ በዚህ ዘመን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አማካይነት አስደማሚ ነገሮች እየተከናወኑ ነው፡፡ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማሽኖች እንደ ሰው እያሰቡ ችግሮችን መፍታት ብቻ ሳይሆን፣ መረጃ ሳይቀር በመለዋወጥ ተገቢውን ዕርምጃ ይወስዳሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንድ ሰው ሥራ ቦታ ሆኖ በተንቀሳቃሽ ስልኩ አማካይነት፣ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ የሚደረገውን ማናቸውም እንቅስቃሴ መከታተል ጀምሯል፡፡ ብዙ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የዚህን ዘመን ዕውቀትና የቴክኖሎጂ ግስጋሴ ከመጋራት ይልቅ፣ ፋይዳ በሌላቸው ጉዳዮች ውስጥ ተዘፍቆ አገርን መበደልና ሕዝብን ማወክ ያሳዝናል፡፡ የተዛቡ መረጃዎችን እየለቀቁ ንፁኃንን ማስፈጀትና ማፈናቀል ይህንን ዘመን አይመጥንም፡፡ መያዣ መጨበጫ የሌላቸው ሐሰተኛ መረጃዎች በማሠራጨት የወጣቶችን አዕምሮ መበከል፣ ለዚህ ዘመን የማይመጥን ኋላቀርነት ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ግጭት በመቀስቀስ ንፁኃንን ካላስፈጁ የእንጀራ ገመዳቸው የሚበጠስ እየበዙ ናቸው፡፡ በሐሰተኛ ወሬዎች አገር ካላተራመሱ የሚኖሩ የማይመስላቸው ከንቱዎች መብዛት ለአገር ህልውና ጠንቅ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡

ፖለቲከኞች ኅብረተሰብን የማነፅ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህንን ኃላፊነት መወጣት የሚችሉት ግን፣ በአርቆ አሳቢ ምሁራንና በአገር ወዳዶች ሲመሩና ከምንም ነገር በበለጠ ለሰው ልጅ መብትና ክብር ሲኖራቸው ነው፡፡ በገዛ ወገኑ ላይ ጥላቻና ቂም ያለው ፖለቲከኛ ወይም የመንግሥት አመራር፣ እንዴት ሆኖ ነው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዝግጁ የሚሆነው? ለሥልጡን ፖለቲካዊ ውይይትና ድርድር ያልተዘጋጀ ኃይል አገር ለማፍረስ እንጂ፣ በየትኛውም መመዘኛ አገር ገንቢ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚህም ነው በንፁኃን ደም እጅን መለቃለቅ እንደ ቀላል ነገር እየታየ ያለው፡፡ በአንዳንድ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ላይ የሚታየው የጀብደኝነት አባዜ ዋናው መስንዔ፣ ለዘመኑ የሚመጥን አስተሳሰብ ካለመታጠቅ የመነጨ ነው፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ በውይይትና በድርድር ከመፍታት ይልቅ፣ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት የዴሞክራቶች ሳይሆን የአምባገነኖች መለያ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ከበስተጀርባ የሚገፋ ሥውር ኃይል ተላላኪነት ነው፡፡ 21ኛው ክፍለ ዘመን የራሱን አጀንዳ ቀርፆ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት፣ ከምንም ነገር በላይ ማስቀደም ያለበት ሕዝብን ነው፡፡ ሕዝብ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት እንደ መሆኑ መጠን፣ ወደ ግጭትና ጦርነት የሚከተው ሳይሆን የዳበረ ቴክኖሎጂ የሚያጎናፅፈውና ወደ ዕድገት የሚያሸጋግረው ነው የሚፈልገው፡፡ ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ እንኳን አገር ለመምራት ለመንደርም አይታሰብም፡፡

ይህ ዘመን የቴክኖሎጂ ግስጋሴ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚታይበት በመሆኑ፣ መረጃ ከአንዱ ወደ ሌላው በብርሃን ፍጥነት ይተላለፋል፡፡ መረጃው የሚደርሰው የኅብረተሰብ ክፍል ያለው ንቃተ ህሊና ዝቅተኛ ከሆነ ደግሞ፣ የሚወስደው ዕርምጃ ዘግናኝ ስለሚሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሥፍራዎች በንፁኃን ላይ ግድያዎች የተፈጸሙትና ጥቃቶች የተሰነዘሩት፣ በሐሰተኛ መረጃዎች ሳቢያ ነው፡፡ በአደባባይ ሰውን የሚያህል ሰብዓዊ ፍጡር ቀጥቅጦ ገድሎ ዘቅዝቆ መስቀል ደረጃ የተደረሰው በደቦ ፍርድ ነው፡፡ የደቦ ፍርድ የሚከናወነው የንቃተ ህሊና ደረጃቸው ዝቅተኛ በሆኑ ሰዎች አማካይነት ነው፡፡ እነዚህን ወገኖች አስተምሮ ማብቃት? ወይስ ለሌላ ዙር ጥፋት አንቀሳቅሶ ሕዝብና አገር ማተራመስ ይበጃል? በዚህ ጉዳይ ዋነኞቹ ተጠያቂዎች ከማንም በላይ እናውቃለን የሚሉ ኃይሎች ናቸው፡፡ ይህንን ትውልድ በማይጠየቅበት ጥፋት መቀጣጫ የሚያደርጉና ላልተገባ ድርጊት የሚጠቀሙበት አውቀናል የሚሉ፣ ነገር ግን 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አስተሳሰብ የሌላቸው ናቸው፡፡ ሕፃናትና ታዳጊዎችን ሳይቀር በጥላቻና በበቀለኝነት እየኮተኮቱ ነውጠኛ ማድረግ ያሳፍራል፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ መሽገው አገር ለማተራመስና ሕዝብን ደም ለማቃባት ሐሰተኛ ወሬዎችን የሚፈበርኩ ኃይሎች፣ አስተሳሰባቸውም ሆነ ድርጊታቸው ለዚህ ሥልጡን ዘመን የሚመጥን አይደለም፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በሠለጠነ መንገድ ነው፡፡ ይህ ሥልጡን መንገድ የሚከናወነው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ብቻ ነው፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በሳይንሳዊ አስተሳሰብ የሚመራ በመሆኑ ለውይይትና ለድርድር ክፍት ነው፡፡ ለሕግ የበላይነት መስፈን ትልቅ ግምት ይሰጣል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ስለሚያስከብር፣ የተለያዩ ሐሳቦች እንዲናኙ ዕድሉን ያመቻቻል፡፡ ከአሳዳጅነትና ከተሳዳጅነት የተላቀቀ የእኩልነት ምኅዳር እንዲኖር ተግቶ ይሠራል፡፡ ጥያቄዎች በሥርዓት ቀርበው በአግባቡ ምላሽ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ ከመጠላለፍ ይልቅ ተባብሮ መሥራትን ያስቀድማል፡፡ ለግላዊና ለቡድናዊ ጥቅም ሳይሆን ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ጠበብ ካለ አካባቢያዊ አስተሳሰብ በመውጣት፣ ለአገር ብሎም ለዓለም የሚጠቅም ተሞክሮ ያስተላልፋል፡፡ አሁን በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚታየው በዚህ ቁመና ላይ ለመገኘት በጣም ብዙ ርቀት ይቀራል፡፡ በምግብ ራሱን ያልቻለ፣ የታረዘ፣ ለእግሩ መጫሚያ የሌለው፣ ሕክምና ለማግኘት ፈተና የሚያይ፣ በአጠቃላይ ከድህነት ወለል በታች የሚሰቃይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ይዞ አገር ማመስ ጤነኝነት አይደለም፡፡ ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ፆታን፣ ወይም ሌላ መሰል ልዩነቶችን በማራገብ ትንንሽ አጀንዳዎች ላይ ተጥዶ ውሎ ማደር ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር ይጣላል፡፡ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍልን በብቃት ከማድረግ ይልቅ፣ በብሔር ወይም በእምነት ትስስር ማደላደል ተለምዷል፡፡ ብቃትንና ጥረትን ሳይሆን ማንነትን ማጉላት የዘመኑ ፋሽን ሆኗል፡፡ 21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ጋር መጣረስ አይበጅም፡፡

ሰው በሰብዓዊ ፍጡርነቱ ብቻ ከማናቸውም ጥቃት መጠበቅ ሲገባው፣ በማንነቱ እየተለየ የሚጠቃ ወይም ከለላ የሚያገኝ ከሆነ ያሳፍራል፡፡ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት ብቻ በመቧደን አገር መገንባት አይቻልም፡፡ በማይክሮሶፍት፣ በአፕል፣ በፌስቡክ፣ ወይም በመሳሰሉት የዓለም ታላላቅ ኩባንያዎች ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች ከዓለም ዙሪያ የተገኙ የምጡቅ አዕምሮ ባለቤቶች ናቸው፡፡ አፍሪካን ጨምሮ ከተለያዩ ሥፍራዎች ተሰደው በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሩ ምሁራን፣ አንቱ ተብለው ተከብረው የሚኖሩት በዕውቀታቸው ነው፡፡ ዘመኑን የሚመጥን ሥራ ሳያከናውኑ መከበር አይኖርም፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች አበክረው ማሰብ ያለባቸው፣ ለዚህ ዘመን ከማይመጥን ኋላቀር ድርጊት ውስጥ በቶሎ እንዴት እንደሚወጡ ነው፡፡ በባህል፣ በትምህርት፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ ግስጋሴ ወጣቱን ማነፅ ሲገባቸው ሐሰተኛ ወሬ በማሠራጨት ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማፋጀት ማሴር የለየለት ኋላቀርነት ነው፡፡ ለዕድገት የሚበጁ ሐሳቦችን ማፍለቅ እየተቻለ፣ የውድመት ጎዳናዎች ላይ መውረግረግ ከንቱነት ነው፡፡ ዘመኑን ከማይመጥኑ ድርጊቶች ውስጥ በፍጥነት መውጣት ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...